ይሄ ሕይወት የሚሉት ጣጣ ካልቸገረ በቀር እዚያው ሞልቶ እዚያው አይፈላም፤ እያዘገመ ዳገት ያወጣል ፤ እያንደረደረ ቁልቁለት ያስኬዳል:: ልቡ ለዚህ ያልተዘጋጀ ሰው፣ “ዳገት እርሙ ሜዳ ወንድሙ” ይሆንና ተስፋ ይቆርጣል ፤ ሁሉም በፍርርቅ እንደሚሄድ መገንዘብ አለበት::
ይህን ጽንሰ ሐሳብ በሀገር ደረጃ ስናየው ብዙ ዳገቶችን ጥቂት ቁልቁለቶችን ሄደናል:: በተለይ የቀደመው ትውልድ ያለፈባቸው ጎዳናዎች ከፍታና ዝቅታ ብዙ ያስተማሩት ነገሮች አሉት:: በዳገቱ ላይ ምን አየን ቁልቁለቱንስ ስንወርድ ምን ታዘብን:: ይኼ መልስ ከእያንዳንዱ እንደያንዳንዱ አስተሳሰብና ተርዕየ (የዕይታ አድማስና አረዳድ) የተለያየ እንደሚሆን ግልጽ ነው::
የትኛውም ጉዞ ፣ የትኛውም ዕርምጃ በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ መንገዶችና አካሄዶች የተቀነበበ ነው:: ሃሳቡን ወደ ቤተሰብ ብናወርደው ሁሌ ሞልቶለት ነገር ተሳክቶለት ደስታ ሰፍኖበት ፍስሐ ተትረፍርፎለት የሚኖር የለም:: ሁሉም እንደየብጤቱ ትንሽ ችግር ፣ ትንሽ ቁንጥጫ፣ ትንሽ ህመም ፣ ትንሽ እስር፣ ትንሽ ሞት፣ ትንሽ ሃዘንና ተቃራኒው ነገር ጎበኘዋል:: ይኼ ብቻ አይደለም ፤ እጅግ የደላቸው በሚመስሉን በኑሯቸው የሞላላቸው ናቸው ብለን በምናስብባቸው ቤቶች ያለው ጭንቀትና ስጋት መካከለኛ ወይም ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባለው ቤት ካለው ጭንቀት ሃሳብ የበዛ ነው:: እንዲያውም “ትልቅ ቤት ትልቅ ችግር አለ”፤ ብሎ ያለኝን ወዳጄን አልረሳውም:: ታዲያ የደስታውን ያህል ማለቴ ነው፤ ማንም ቤት ዳገት ብቻ እንደሌለ ሁሉ ቁልቁለትም ብቻ የለም::
ቁልቁለት ላይ አካላትህን መንገዱ ሲሸከምልህ ዳገት ላይ ሰውነትህን የምትሸከመው አንተ ነህና ይከብድሃል፤ ትዝላለህ፤ ታለከልካለህ ፤ ቁልቁለት ላይ ሲሆን አቅም ትሰበስባለህ እንጂ አታባክንም፤ ጅል ካልሆንክ:: በህይወት ውጣ ውረድም ውስጥ እውነቱ እንዲሁ ነው::
የሰውነት ሸክም ሰው የመሆን ጣጣ ነው፤ ትፈራለህ፤ ትጠራጠራለህ ፤ ትሰጋለህ:: እደርስ ይሆን ወይስ ከመንገድ ይመሽብኝ ይሆን አውሬ ይገጥመኝ ይሆን ወይስ ሽፍታ ያጋጥመኝ ይሆን እያልክ ትሰጋለህ:: አንዳንዴ ነገር እንደስጋትህ ላይሆን እንደሚችል ሁሉ የጠበቅከው ሲሆንም አትደናገጥም፤ ወይ መላ ትመታለህ ወይ በመላው ትወድቅበታለህ::
ጉዳዩን ከፍ ሳናደርገው በፊት በጓደኛነት እስቲ ደግሞ እንየው፤ ጓደኝነት ወዳጅነት አይደለም ፤ ወዳጆችህ ብዙ ሲሆኑ የሚችሉትን ያህል ጓደኞችህ ግን የተመረጡና የተወሰኑ ናቸው:: ጓደኞች እንደራሴነት አላቸው፤ ስላንተ በደግም ሆነ በክፉ በሚነገርበት ስፍራ ካሉ እውነተኛውን ምስል ይነግራሉ፤ ይጠብቁሃል ፤ ሲከፋህ ገጽህን አይተው ወይም ድምፅህን ሰምተው ብቻ ያውቃሉ፤ ሳትጠራቸው ያለህበት ስፍራ ይመጣሉ፤ ሳትነግራቸው ችግርህን ይረዳሉ፤ ለመፍትሔው አብረውህ ይተጋሉ::
ጓደኝነት አንዳንዴ በቁልቁለት መንገድ ብቻ መሄድ ፤ ዳገትም አለው፤ አንዳንዱ ጥቅሙ የተነካበት ፣ ጥቃት የደረሰበት ሲመስለው ለማፈግፈግና ለመውቀስ፤ ለመራገምና ለማውገዝ ፈጣን ነው፤ ያኔ ጓደኝነት ዳገት ይሆናል:: የተረገመው እንኳን ይቅር ቢል ረጋሚው እንቅልፍ ስለሌለው ያኮርፋል ይቆጣል::
አንድ ምሳሌ ጀባ ልበላችሁ፡ ሁለት ሴት ጓደኛሞች አሉ:: አንደኛዋ ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እንደሚወዳት የምታውቀው ሰው በሥራ ዓለም ውስጥ ቆይቶ ውጭ ሀገር ደርሶ ሲመለስ ምናልባት ባገኛት ብሎ ስልክ ሲደውል ጓደኛዋ ስልክ ታነሳለች:: ታዋራውና ላገኛት እንደምፈልግ ንገሪያትና እዚህ እዚህ ስፍራ በዚህ ሰዓት እንድትመጣ ንገሪልኝ ፤ ከይቅርታ ጋር ብሏት ይሰናበታታል::
ይችን ግሩም አጋጣሚ ያገኘችው አጅሬ የሆዷን በሆዷ አድርጋ ከሻወር ለወጣችው ተፈላጊዋ ሰው ስልኬ ጮሆ ነበረ፤ ማነው የደወለው ትላታለች:: የተሳሳተ ቁጥር ነው፤ “ጀሚላ አለች ወይ፤ ሲለኝ የምትባል የለችም” አልኩት:: ጅንጀና ብጤ አማረውና መቀባጠር ሲጀምር “አፍህን አትክፈት” ብዬ ዘጋሁበት ፤ ትላታለች::
እንደዘበት ታልፈዋች:: አንቺ ህልሜን ሳልነግርሽ ቀረሁ:: ትላንት ከኤርሚስ ጋር ወንዝ ስንሻገር አየሁና ገርሞኝ ከየት መጣ፤ አልኩኝ:: አይገርምም?” ስትላት ሰግጠጥ አለች:: ያንቺ ኤርሚስ ደግሞ ሜዳው እያለለት የቀን ብርሃን ሌሊት አልጋሽ ላይ ይመጣል? ጅል በይው ትላታለች ፤ ፍቅሯን አለመቀነሷ እየገረማትና የስልኩ መገጣጠም ገርሟት::
ከዚያም አጅሪት በተባለው ቀንና ሰዓት በተባለው ስፍራ ዝንጥ ብላ ትገኝና የሞቀ ሰላምታ ትሰጠዋለች:: ጽጌረዳስ ይላታል:: ጽጌ ምን ፈልጎ ነው፤ አልመጣም በይው ብላ ልካኝ ነው፤እሷን ተዋት፤ አሁን እኛ እራት እንብላና ተጨዋውተን እንለያያለን፤ ትለዋለች:: ግርር ቢለውም ይሁን ብሎ እራት አዝዘው እየበሉ ሳለ እርሷን ከራሷ ወንድም ጋር እራት እዚው ሆቴል እንዲበሉ አመቻችታ ፣ እራት በልተው ሊወጡ ሲሉ በርቀት ታሳየዋለች::
“ጽጌረዳ እጮኛ አላት ማለት ነው? “
“ባል በለው…እ…አታየውም እንዴ እንዴት እንደሚሳሳቁ…”
“ከባልና ሚስትነት ይልቅ ግን ወንድማዊ …ይመስላል ፣ ልበል….”
አጠገቡ ያለችውን ሴት አየና ፣ ቀጥሎ ወንዱን አየው:: ጠይምነታቸው የዓይናቸው ሽፋል፣ ሳቁ…ቁጭ አጠገቡ ያለችውን ሴት ነው የሚመስለው:: እና ካንቺ ጋር ዝምድና አለው እንዴ ባል ተብየው፣….አላት::
ኧረ እንደውም የት ሳውቀው!….
ይመስላል ፤ አየሽ እንዲህ ዓይነት ድራማዎች ደስ ይሉኛል:: እጄን ታጥቤ ልምጣ ብሎ ተነስቶ ሄደ:: አጅሪት መሐረቧን አውጥታ ችፍ ያለባትን ላብ ጠራረገች:: ቡዳ ነገር ነው፤ አለች ለራሷ::
አጅሬ እጁን ታጥቦ ሲመለስ በዚያው ወደተጠቆሙት ዘንድ ጎራ ብሎ፣ ሰላምታ ለእርሷ ያቀርብላታል:: ስታየው ውሃ ትሆናለች:: “ከየት ተከሰትክ ፤ መቼ መጣህ? በሃገር አለህ ? ምነው ድምፅህ ጠፋ ኪያዬ…. አንድ ቀን አገኝህ ይሆን እያልኩ እኮ አስብህ ነበረ፤ ኤርሚ! ያልከው::
ይህን የሰማው አጅሬ የልጁን ዝምድና አልተጠራጠረም:: እርሷን እንዳቀፈ ወደ ወንበሩ አቅጣጫ እያሳየ ስልክ ደውዬ ስቀጥርሽ እኮ አልመጣም በይው ብለሽኝ ….ጓደኛሽ ልታጽናናኝ መጥታ ብሎ ቀና ሲል አጅሪትን ከቦታው አጣት:: ወዴት ሄደች?
ማን ?
ሉሊት!
ሉሊት፣ “አልመጣም ብላሃለች፤ በይው” አለችህ ? ደግሞ በስቃዬ ለመደሰት አንተን አጠገቤ ላይ ይዛ ነው፤ አልመጣም ብላሃለች የምታሰኘው:: ሆ! ጭካኔ! እኔ እኮ ድምፅህ ብቻ ይበቃኝ ነበረ:: ምን አደርግኋትና የልጅነት ጓደኛዬ እንዲህ አደረገች:: በቃ ተዋት፤ ናና አብረን እንቀመጥ፤ ስትለው ወንድሟ ብድግ ብሎ “ይቅርታ፤ እኔ ልሂድ?” ብሎ ተነሳ:: አላግደረደሩትም:: እርሱም ፈጠን ብሎ ወጣ:: ጓደኝነት ዳገት ላይ ተገመተ:: መካካድ ይሉት ሰበዝ ከውድ የልጅነት ፍቅር ውስጥ ተሸሽጎ ገብቶ ነጠላቸው:: ራስ ወዳድነት የሚባል ሴንጢ ሜዳማ የተባለውን ጓደኝነት፤ ቆረጠውና የማይሞከር አቀበት አደረገው::
ኤርሚያስና ጽጌረዳ ከዚያ በኋላ ምን እንደሆኑ አልነገሩኝም፤ አንድ ነገር ግን አውቃለሁ:: የጽጌረዳና ሉሊት ጓደኛነት ክፉ አቀበት ላይ ወድቆ ቀረ:: ጓደኝነት በተቃራኒ ጾታ ፍቅር እስኪፈተን ድረስ በብዙ ዳገቶች ላይ ተፈትኗል፤ ብዙ አልፏል፤ ይህኛውን ፈተና ግን ማለፍ አልቻለም፤ ተረታና ወደቀ::
ዳገት በሀገር ደረጃ ሲመጣም እንዲሁ ነው:: በተለይ የእኛ ሀገር በአሁን ወቅት የወደቀችበት ፈተና በእውነተኛ ልጆችና እውነተኛ ባልሆኑ ልጆቿ መካከል እንበለው ወይስ እኛ እናውቅልሻለን በሚሉ የገዛ ልጆቿ ውጥረት ዳገት ላይ ወድቋል:: ክፉው ነገር ወድቆ መቅረት ነው፤ እየተንፏቀቀም ቢሆን ግን መቀጠል አለበት::
አሁን ሃገሪቱ ከፍተኛ ዳገት ላይ ነች:: ዳገቱ ደግሞ ድንጋያማና ጭንጫማ፣ ግቻው የበዛበት ፣ ለአካሄድና አወጣጥ የማያመች አቀበት ላይ ነው:: ስለዚህ ነው፤ ድሮ አባቶች እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥማቸው፡-
“ሜዳ ላይ መፈንጨት የሰነፍ ልማድ ነው፤
ገመገሙን ወጥተን አቀበት ስንጀምር ሁሉም የሚታይ ነው፤
ወገቡ ላይ ስንደርስ ጎበዝ ይገመታል፤
እነሜዳ ወንድሙ “ሲያንዛርጡ” ይታያል::” ይሉ ነበር::
በጨለማውና አስቸጋሪው ወቅት ፣ የሌሉ ባስፈሪውና በድቅድቁ ወራት ያልነበሩ ሁሉ ብርሃን ሲሆን ብርሃን ለማዳፈን ይሯሯጣሉ:: “አለን”፣ ማለታቸው ባልከፋ በጠፋው ብርሃን የሚጠፋው አንድ ወገን ብቻ እንደሆነ ካሰቡ ግን ችግር ነው:: እሳት ቢነሳ የሚያጠፋው የሁሉን ማሳ፤ ጎርፍ ቢነሳ የሚጠርገው የሁሉን አፈር ነው:: ታላቁ የአባይ ወንዝ ለዚህ በቂ ምስክር ነው:: ከቶውንም ካላስተዋሉ በማጥፋት ስትራቴጂ አስገባሪ መሆን አይቻልም፤ አጥፊነትና ጸብ የትም አለ:: አስቸጋሪው ፍቅርና ትዕግስት ነው:: ትዕግስት ደግሞ መከራውን አውቆ ዝምብሎ በፍቅር መጠበቅ ውስጥ ያለ ጨዋነት እንጂ ጊዜ እስኪያገኙና ብድር እስኪመልሱ የማድፈጫ ዋሻ ወይም ስላች አይደለም::
ሃገራችን በዳገት ላይ ነች፤ ያውም በብርቱ ዳገት ላይ:: ስለዚህ ይህንን የምስቅልቅል ዳገት እንድታልፍ ስርዓት ያለው፤ የተቀናጀ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ፣ ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስልት መቀየስና የዳገቱን መከራ መቀነስ ተገቢ ነው:: ዳገት ዳገቱን እያዩ ማቃሰትም ፤ አይቻልም ብሎ መቀመጥም ተገቢ አይደለም::
አባትየው ማዶ ዘመድ ቤት ሄደህ እቃ አምጣልኝ ብሎ የላከውን ልጅ ደጅ ላይ ሲወጣ ያገኘውና ፤ “ልጄ ከመቼው ሄደህ መጣህ” ቢለው፣ “አስቤ አስቤ ደከመኝና ተውኩት ” አለ፤ እንደተባለው እንዳይሆንብን ነገር በማሳደር ስትራቴጂ የእኛ ሃሳብ እስኪሳካ ድረስ መቆየት የትም አያስኬደንም:: ማጣፊያው ሲያጥራቸው ወደእኛ ሃሳብ ይመጣሉ፤ ለእኛ ዓላማ ይገብራሉ ተብሎ መጠበቅ ለሃገርም ለራስም አይበጅም:: የሃገርን ምጧን ማባባስ ሳይሆን ማስተንፈስ፤ ማግዘፍ ሳይሆን ማቃለል ከሁሉም ልጆቿ ይጠበቃል::
ሃገር የመሪ ልጆቿ የብቻ ቤት አይደለችም፤ የሁሉም ልጆቿ ነች:: ሁሉም ግን እንደፈለጉ ወደራሳቸው ሃሳብ ሊጎትቷት አይገባም:: ወደ አንድ አግባቢና ማዕከላዊ አስተሳሳሪ ሃሳብ መምጣት መቻል አለባቸው:: ወደ ማዕከላዊው ሃሳብ ለመምጣት ከራሳቸው ይቅርብን የሚሉትና የሚተዉት ነገር ሊኖር ይገባል:: የኔ ሃሳብ ብቻ ገዢ ነው ፤ የኔ ሃሳብ የነገር ሁሉ የማእዘን ድንጋይ ነው፤ ከዚህ ማእዘን አልለቅም ማለት ፣ የፈለግሁትን በፈለግኩት ማስገደጃ መንገድ አመጣለሁ ብሎ መገበዝ ነው:: (Conflict is politics by any means) ይላሉ ፈረንጆች:: ስለሀገር በውኑ የሚያስብ ኃይል አቀበቱን ቀናሽ፣ ጠመዝማዛውን መንገድ አሳናሽ እንጂ ያሳለፈውን መንገድ እየቆጠረ፣ የቀድሞ ጀብድ “እየፎከረ” የሚመላለስ ችግር አባባሽ መሆን የለበትም::
ያንን ለአንድ ወቅት የተከፈለ መስዋእትነት በድል የደመደመው ኃይል፣ ራሱን በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንዳለፈ የራስ ኃይል እንጂ ከሩቅ የመጣ ወራሪ ጠላትን እንዳንበረከከ ሲነግረን ሊኖር አይገባም:: በዚያም በዚህም በኩል ያለቀው ወገን የራስ ነው፤ ስለዚህ ያለፈውን ትተንና ለታሪክ ምስክርነት አስረክበን በአዲስ ሃሳብና በአዲስ መንገድ መነሳት እና የሀገርን የለውጥ ጉዞ አቀበት መቀነስ የተገባ ነው::
አምናለሁ፤ ሁሉም ኃይሎች ወደህሊናቸው መጥተው ከፓርቲ መርህም ሆነ ከፓርቲ ስትራቴጂ ፈቀቅ ብለው ሃገራቸውን በማስቀደም ለሰላሟ ለመቆም ቃልኪዳን የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አምናለሁ:: እባካችሁ፤ ለሰላም በመትጋት ውስጥ የሚገኘው ድል የጋራ ነው:: ከሚጎሰም የጦርነት ነጋሪትና “ የማንም አይችለኝም”፤ ፉከራ ውስጥ ሃገር የምታተርፈው ፍሬ የለም:: አምናለሁ፤ ዳገቱን ስንጨርስ ቁልቁለቱ ይጀምራል፤ የቀደመውን ዳገት ስንጨርስ ቁልቁለትና ሜዳ ቢኖርም ሌሎች ዳገቶች አሉና አብረን እንወጣቸዋለን:: እጅ ለእጅ ተያይዘን በህብረት እንጓዝ!!
አሪፍ የመደማመጥ ሳምንት ይሁንላችሁ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ