የውጭ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ዓይናቸውን ከሚያሳርፉባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያአንዷ ናት፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተነቃቃ የመጣው ኢንቨስትመንት በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንዳለ እሙን ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተከሰተው አለመረጋጋት ለኢንቨስትመንቱ ስጋት እንደሚሆን ባይጠረጠርም ይህ ዘርፍ ዛሬም ቢሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኝት ታቅዶ ሰባት መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ይገልጻሉ። በዚህም የዕቅዱን 70 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ ቁጥራቸው አንድ መቶ የሚጠጋ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ወስጥ መግባታቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡
የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ምንም እንኳን ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አበርክቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉበትም ጠቅሰዋል፡፡ በዋናነትም የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዘርፉን ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም ችግር በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ ላይ ጋሬጣ እየሆነ መምጣቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን የሀገራችን የሰላም ሁኔታ በኢንቨስትመንቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ነው ማለት ባይቻልም ችግሩ በረዘመ ቁጥር ግን ኢንቨስትመንቱን እየጎዳው እንደሚሄድ አቶ መኮንን ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የሩብ ዓመቱ ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የሰላም ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሰላምና ደህንነት ለኢንቨስትመንት ማደግና መስፋት የማይተካ ሚና እንዳለው የሚናገሩት አቶ መኮንን፣ በሀገራችን የተስተዋለው አለመረጋጋት በአንዳንድ ቦታዎች በኢንቨስትመንት ሥራው ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ክስተት ወደፊትም ቢሆን የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በማበላሸት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢንቨስትመንት በዋነኛነት በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር በመቀነስ የላቀ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት አቶ መኮንን፣ ከዚህ አንጻር በተለይም ወጣቱ ሰላሙን በማስጠበቅ የእድሉ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል። ለዘርፉ መስፋፋት እያንዳንዱ ዜጋ የየራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ዳይሬክተሩ መክረዋል፡፡
የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዕቅድና በጀት ዝግጅትና የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙላቱ ዱጎ በበኩላቸው፣ የሩብ ዓመቱን የኢንቨስትመንት አፈጻጸም ሲገልጹ በክልሉ 448 ፕሮጀክቶችን ለመሳብ ታቅዶ 124 ፕሮጀክቶችን ብቻ ለመሳብ መቻሉን ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ዳያስፖራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ሲሆን በእርሻ ፣በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግና ጥቂቶቹም በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
ኃላፊው ከሰላም ጋር በተያያዘ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ጥፋት እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ከሥራ መስተጓጎላቸውን አስታውሰው፣ አሁን ግን አብዛኛዎቹ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ላይ የሚደርስ ጥፋት ዘርፉን መቀላቀል የሚፈልጉ ሌሎች ባለሀብቶችን ፍላጎት እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
ከሪፎርሙ ወዲህ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ሰላም ሲረጋገጥ የባለሀብቱ ፍሰት የበለጠ ይጨምራል ብለዋል፡፡ የሀገራችን ተጠቃሚነት የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም ያለ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ ስለማይቻል ሕብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ሰላሙን በማስጠበቅ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ እስተዚያው በበኩላቸው በሩብ ዓመቱ ለ750 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ811 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የዕቅዱን 108 በመቶ ማሳካት እንዳስቻለ ነው የጠቀሱት፡፡ አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በአጠቃላይ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የአዲስ አበባ ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከተገመተው በላይ ቢጨምርም የመሬት የብድርና የኃይል አቅርቦት ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ በክልሎች ያለው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ባለመሆኑ ባለሀብቱም ሆነ ሰራተኛው አዲስ አበባን ተመራጭ በማድረጉ የኢንቨስትመንቱ ፍሰት ለመጨመሩ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በመላ ሀገሪቱ ተመጣጣኝ ዕድገት እንዳይኖር የሚያደርግ ክስተት ነው፡፡
ኢንቨስትመንት በባሕሪው የተረጋጋ ኢኮኖሚና ሰላምን ይፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሰላም በሌለበት ኢንቨስትመንትም ሆነ የስራ ዕድል መፍጠር እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ሰላምና ኢንቨስትመንት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ወጣቱ ኢኮኖሚ አመንጪ የሆኑ ተቋማትን በመንከባከብ የራሱንም ሆነ የሀገሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በሰላም እጦት ምክንያት ከሚስተጓጎሉ ኢንቨስትመንቶች ጀርባ የበርካታ ዜጎች ጉሮሮ እንደሚዘጋ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በተያዘው ዓመት መንግስት ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲያቅድ በርካታ የሰው ኃይልን ይሸከምልኛል ያለው የኢንቨስትመንቱን ዘርፍ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ዘርፉን በመንከባከብ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
ኢያሱ መሰለ