ወ/ሮ ፍቅርተ ጥበቡ በጆሮ ህመም ክፉኛ ተሰቃይተው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በህግ አማካሪነት ፣ በህግ ባለሙያነትና በጥብቅና የሚሰሩት ወይዘሮ ፍቅርተ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ የመስማት ችግር ነበረባቸው፡፡ ግራ ጆሯቸው ፈሳሽ ያመነጭ ነበር፤ ከዚህም ለመፈወስ ባህላዊ ህክምናዎችን ተከታትለዋል፡፡
ሆስፒታል ሄደውም አምፒሲሊን እና አሞክሳሲሊን እየተሰጣቸው መታከማቸውን ጠቅሰው፣ ፈሳሹ ለጊዜው እየቆመና እያገረሸ ለ21 ዓመት መሰቃ የታቸውን ያስውሳሉ፡፡” የመስማት ችግሬ እየተባባሰ የግራው ተዘጋ፡፡ የቀኙ የተወሰነ ቢሰማም ማየት የተሳነኝም ስለሆንኩ ህይወት እየከበደኝ መጥቶ ነበር “ ይላሉ፡፡
በ1998 ዓ.ም በቤተ ዛታ ሆስፒታል የመስማት መጠኑ ተለክቶ የግራው እንደማይሰማ ተነግሯቸው ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው ይነ ገራቸውና ሁለቱም ጆሯቸው ቀዶ ህክምና ይደረ ግላቸዋል፤ በዚህም ፈሳሹ ቆመ፤ የመስማት ችግሩም ተፈታ፡፡ ይህ መረጃ የደረሳቸው ሦስት ዐይነ ስውራንም መታከማቸውን ይናገራሉ፡፡
የኤቲጂቲ የኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር አርጋው ታመነም “ከልጅነቴ ጀምሮ ሁለቱንም ጆሮዎቼ እያመመኝ ቀረብ ካላልኩ ወይ ጮክ ብለው ካላወሩኝ በቀር አይሰማኝም ነበር ይላሉ፡፡ በኦቶሪኖ ልዩ የአንገት በላይ ክሊኒክ በ1992 ዓ.ም ሁለቱንም ጆሮዋቸውን በቀዶ ህክምና መታከማቸውን እና ለ15 ቀናትም መድሃኒት መውሰዳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ድነው በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን ድርጅት መሥርተው እየሠሩ ናቸው፡፡
ዶ/ር ኢስሐቅ በድሪ የኦቶሪኖ ልዩ የአንገት በላይ ክሊኒክ ሃላፊ እና የአንገት በላይ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንትም ናቸው፡፡ በክሊኒኩ ላለፉት ሃያ ዓመታት የጆሮ ህክምና ሰጥተዋል፡፡ ከአንገት በላይ ህክምና ማህበርም መስርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የአንገት በላይ ህክምና ክፍል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲከፈትም አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
የኢትዮ አሜሪካ ሂሪንግ ፕሮጀክት በቅርቡ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የአንገት በላይ ህክምና የአቅም ግንባታ ሴሚናር ላይ አስተባባሪ የነበሩት ዶር ኢስሃቅ፣ በጀርመን የጆሮ ህክምና ተምረዋል ፤ በቀዶ ህክምና ባለሙያነት እና በሃላፊነትም እንዲሁም በማስተምርም ሰርተዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ኢስሐቅ ማብራሪያ ፤የጆሮ ህመም በህጻንነት ሊከሰት በሚችል ኢንፌክሽን እና የጆሮ ታምቡር በሚደርስበት መቀደድ ሳቢያ ይከሰታል፤ህመሙ የመስማት ችሎታን እስከመቀነስ ይደርሳል፡፡ ሌላው የጤና ችግር ታምቡሩ ቦታውን በመልቀቅ የጆሮ የውስጥ አጥንቶችን እየበላ የሚቦረቡረው ነው፡፡ ሁለቱም ግን በቀዶ ጥገና መስተካከል ይችላሉ፡፡
ሌላው ቲምፓሎክሮሲስ ነው፡፡ ይህ በሽታ ብዙ ጊዜ ሲቆይ የመስማት ችሎታን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ጆሮ ውስጥ እንደ ጄሶ ይጋገራል፡፡ ይህም በውጪ ሀገር ቀዶ ህክምና ሊደረግ አይችልም ፤ ይህ በሽታ በአውሮፓም በአሜሪካም የሚታወቀው አይድንም በሚል ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን ህክምና እየተደረገ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በሀገራችን ባለን ዕውቀት በመጠቀም ችግሩን በመፍታት መዳን እንደሚቻል እያሳየን ነው። ህንዶችና አሜሪካኖችም ይህንን ከኛ መማር ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የጆሮ ህመም በከፍተኛ ደረጃ ቢታይም የቀዶ ህክምና ጥበቡ ያላቸው ደግሞ በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡
የጆሮ ህክምና አገልግሎቱን ለማዳረስና አገልግሎቱን በብቃት ለማግኘት የግዴታ ገንዘብ ኖሮ ውጪ ሀገር ሄዶ መታከም አስፈላጊ መሆን የለበትም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ይሄንን ህክምና ማግኘት አለበት፡፡ ለእዚህ ደግሞ አቅም ግንባታ ላይ መስራት ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው ህክምናው ብዙ ዕውቀት የህክምና መሣሪያዎችንና ወጪዎችን ይጠይቃል። አንዳልኩት በቅድሚያ ይሄንን ለመሥራት የአቅም ግንባታ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃና ጥራት ያለው የጆሮ ቀዶ ህክምና ሥልጠና ለመስጠት ያሉን ተቋሞች አቅም አይፈቅድም። እኛ የግል ክሊኒክ ውስጥ እየሠራን ያለን ባለሙያዎች በውጪ ሰልጥነን በዲያስፖራነት ሀገራችን ተመልሰን ክሊኒክ ከፍተን እየሠራን ህዝቡን እያገለገልን ነው፡፡
“ጆሮ ውስብስብ የውስጥ አካል በመሆኑ በማይክሮስኮፕ የሚሠራ ቀዶ ህክምና ተጀምሯል፤ ብዙ ወጪና ስልጠና የሚጠይቅና ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው። ጆሮ መስሚያ አካል ብቻ ሳይሆን አጠገቡ አንጎል እና ደምስሮች አሉ፤ በመሆኑም ህክምናው ጥንቃቄን ይፈልጋል››ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ዶ/ር ኢስሐቅ እንደሚሉት፤ወጣቶችን በማስተማር ተተኪ ማፍራት የግድ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉት የጆሮ ቀዶ ህክምና ሀኪሞች በውጪ ሀገር ካሉ ሀኪሞች ጋር በመተባበር እየሰሩ ናቸው ፡፡
በአሜሪካ ኦልዲስ ዩኒቨርሲቲ እያስተማሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር ሚስስ ኢልያን በውጪ ሆነው የግል የእርዳታ ድርጅት መሥርተው በትርፍ ጊዜያቸው ከእኛ ጋር በመሆን እየተመላለሱ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ፕሮግራም ቀርፀናል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ኢስሃቅ ገለጻ፤ሰሞኑን የጆሮ ቀዶ ህክምና 3ኛው ዓለም አቀፍ ሰሚናር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በሰሚናሩ ሦስት ከአንገት በላይ የግል ህክምና ክሊኒኮች ሥራቸውን ዘግተው አብረው ቆይተዋል፡፡ ከየክልሉ ሀኪሞች መጥተዋል፤ ከሩዋንዳም የመጡ አሉ፤ ህንዳዊ ፕሮፌሰርም ነበሩ፤ ባለው ዕውቀትና ተግዳሮት ላይ ውይይት ተደርጓል። ከውጪ የመጡትም ልምዳቸውን አካፍለዋል፤ ከእኛ የሚቀስሙትን ልምድ ወስደዋል፡፡
ከመቀሌ፣ ከሀዋሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባና ሀረር ሳይቀር ከሌሎችም እየመለመልን ባለሙያ በሌለበት ቦታ እያሰለጠንና እየመደብን ተቋሞቻችን እርስ በርሳቸው እየተረዳዱ የውጪ ሀኪሞች ሲመጡ ዕውቀታቸውን አካፍለው እንዲሄዱ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ኢስሃቅ ገለጻ፤ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን በማደራጀት የአንገት በላይ ህክምና ትምህርት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ በመቀሌ ከአንገት በላይ ስፔሻላይዜሽን ተከፍቷል፤ ጥቁር አንበሳና ጳውሎስ ሆስፒታልም ትምህርቱ እየተሰጠ ነው፡፡ ወደፊትም ሌሎች እንዲከፈቱ ይፈለጋል፡፡ ዶ/ር ፅዮን የምትባል የሐረር ተወላጅ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ጀምራለች፡፡ ለሐሮማያ ለጅማ ማይክሮስኮፖች ለሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ዕቃዎችን ተልከዋል፡፡
በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የአንገት በላይ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ኃይለማርያም ታፈሰ ህንድን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገሮች ከመጡ የአንገት በላይ ህክምና ባለሙያዎች ልምዳቸውን ተጋርተናል፤ ሠርተን የማናቃቸውን በቀጥታ የጆሮ ቀዶ ህክምና ሲሰራም በቪዲዮ ተከታትለናል ይላሉ ፡፡
ረጅም ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ከውጪ በማምጣት በሀገር ውስጥ ወደ 36 ለሚደርሱ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት መቻሉን ጠቅሰው፣ መንግሥትም ሥልጠናውን በትኩረት በመስጠት በሆስፒታሎች የጆሮ ህክምና የሚሠጥበትን ሁኔታ ማስፋፋት እንደሚጠበቅበት ይገልጻሉ፡፡
በሀገሪቱ እንዳለ ከሚገለጸው የጆሮ ታማሚ አንጻር ሲታይ በቂ የጆሮ ህክምና ባለሙያዎች ለማፍራት የግሉ ዘርፍ የያዘውን ጥረት ማጠናከር መንግስትም ህክምናው የሚሰጥበትን መንገድ ማስፋፋት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 23/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ