የኢትዮጵያ መንግስትና አሊባባ ግሩፕ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አለም አቀፍ የንግድ ማእከል ለመገንባት ከሰሞኑ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ማእከሉ ሲገነባ በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደተለያዩ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ሲፈፅሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጀስቲክ አገልግሎትና የሰለጠነ ባለሙያ ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተጠቁሟል።
በአሊባባና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተመሰረተው ይህ አዲስ አጋርነት በእስያ ቻይናና ማሌዢያ፣ በአውሮፓ ቤልጂየም እንዲሁም በአፍሪካ ሩዋንዳ ተመስርተው ስኬታማ ከሆኑት ማእከላት በመነሳት የተመሰረተ ነው። ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከሩዋንዳ ቀጥሎ በኤሌክትሮኒክ የታገዘ አለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማእከል ያላት ሁለተኛዋ አፍሪካዊ ሃገር እንደሚያደርጋትም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በኤሌክትሮኒክ የታገዘ አለም አቀፍ ንግድ ለኢትዮጵያ በሚያስገኘው ጠቀሜታና ለዚህ አይነቱ የንግድ ስርዓት ኢትዮጵያ ምን ያህል ዝግጁ ናት? በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የኢንተርናሽናል አይ ሲቲ ሶሊዩሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ጋሻው ሽባባው ጋር ያረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አለም አቀፍ ንግድ ምንነትና ከመደበኛው የንግድ ስርዓት ያለው ልዩነት
በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አለም አቀፍ ንግድ በአሁኑ ወቅት ያለውን የማንዋል ወይም የወረቀት የገንዘብ ፍሰት ወደ ዲጂታል አለም በመቀየር የሚንቀሳቀስና የተለያዩ ክፍያዎች የሚፈፀሙበት የንግድ ስርዓት ሲሆን፣ ተደራሽነቱም በሁሉም አለም ተቀባይነት ያለው ነው። ለአብነት ኢትዮጵያ በግብይት ወቅት ጥሬ ገንዘብ የምትጠቀም ከሆነ በዲጂታል የገንዘብ ስርዓት ውስጥ መግባት አትችልም። ይሁንና የዲጂታል ስርዓትን የምትጠቀም ከሆነ የብር መጠኑ ተቀይሮ እቃዎችንና አገልግሎቶችን መሸጥና መግዛት ያስችላታል።
በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አለም አቀፍ የንግድ ስርአትና ከመደበኛው የንግድ ስርአት በብዙ መልኩ ይለያል። በውጪው አለም አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው ገንዘብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እንዲህ አይነቱ ዲጂታል ንግድ የወረቀት ገንዘብን ከማስቀረቱም ባሻገር የግብይት ስርአቱን በተለይም ቢሮክራሲ የበዛባቸውን የንግድ ስርአቶችን የሚያስቀርና ቀጥተኛ የሚያደርግ ነው። በንግድ ሂደት ውስጥ በመሃል ያሉ ደላላ እና የመሳሰሉትን/ኤጀንቶችን/ በማስቀረት በአነስተኛ ዋጋ ከፍተኛ እቃ ወይም አገልግሎት ለማግኘት ያግዛል።
ይሁን እንጂ በተለመደው የማንዋል አለም አቀፍ የንግድ ስርአት ሂደት በመሃል ላሉ ኤጀንቶች ሁሉ የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ይጠበቃል።በዚህ የንግድ ስርአት ሂደቱ ረጅም ስለሚሆን የእቃዎችና አገልግሎቶች ጥራትም እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። በዚህም ምክንያት ለእቃዎችና አገልግሎቶች የሚደረገው ክፍያ ከፍተኛ ይሆናል።ይሁንና በዚህ የዲጂታል ግብይት ስርአት ቀጥታ እቃዎችንና አገልግሎቶችን መግዛት የሚቻል በመሆኑ የሚፈለገውን እቃና አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋና ጥራት ለማግኘት ያስችላል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ንግድን ለማስኬድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ?
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የንግድ ስርአትን ለማስኬድ የሚያበቃ የኔትዎርክ መሰረተ ልማት የለም። በሃገሪቱ የሚገኙ ባንኮችም በኔትዎርክ መቆራረጥ ምክንያት ብዙ ጊዜ ሲቸገሩ ይታያል። ይሁንና ይህ የንግድ ስርአት ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ባለው ሁኔታ አይጠበቅም። የሚሰጠውን የኢንተርኔት አገልግሎትም ማሻሻል ይኖርበታል።
የኔትዎርክ መሰረተ ልማቱን ማስተካከል የማይቻል ከሆነም የንግድ ስርአቱን ለማስኬድ እጅግ አዳጋች ያደርገዋል። የኢንተርኔት ኔትዎርክ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ወደሃገር ውስጥ የሚገቡ ከሆነና በኢትዮቴሌኮም በኩልም ከኔትዎርክ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን መፍታት ከተቻለ የንግድ ስርአቱን ማስጀመር ይቻላል።
በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አለም አቀፍ ንግድ ተግዳሮቶች
በዲጂታል አለም ውስጥ የሰዎችን አካውንት በተለያዩ መንገዶች በመዝረፍና ወደራሳቸው አልያም ወደ ሌላ አካውንት በማዞር የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ያልተፈቀደላቸው በርካታ የኮምፒዩተር ጠላፊዎች አሉ። ይህም የዚህ ንግድ ስርአት ዋነኛው ተግዳሮት ሆኖ ይጠቀሳል።
እነዚህ የኮምፒዩተር ጠላፊዎች ሁለት አይነት ናቸው፤አንደኛው በትላልቅ ድርጅቶችና ኢንተርፕራይዞች ደረጃ የተደራጁ የኮምፒውተር ጠላፊዎች /hackers/ ናቸው።እነዚህ ጠላፊዎች የኮምፒዩተር የመጠቀሚያ ስምና የይለፍ ቃል ሳይኖራቸው ሲስተም ፈጥረው አልያም የራሳቸውን እውቀትና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በቀጥታ በነዚህ ድርጅቶችና ኢንተርፕራይዞች አካውንቶች ውስጥ በመግባት ገንዘብ፣ሚስጥርና ሌሎችንም ፋይሎች ይመዘብራሉ።
ሁለተኛው የመጠቀሚያ ስምና የይለፍ ቃል እንዲሁም የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ናቸው።እነዚህ ህገወጦች ማንም ሳይፈቅድላቸው /crackers/ ለአካውንቱ ባለቤት ሶፍትዌሮችን በማቅረብና የይለፍ ቃል እንዲያስገባ በማድረግ ወደ ድርጅቶቹና ኢንተርፕራይዞቹ አካውንት የሚገቡ ይገባሉ።
መፍትሄዎች
በኤሌክትሮኒክ ለታገዘ የንግድ ስርአት ችግሮች የሶፍትዌርና ሃርድ ዌር መፍትሄዎች አሉ።ለአብነትም የባንክና የቴሌ ሲስተም ከሆነ የተፈቀደለት አካል ብቻ ሊጠቀምበት የሚችልበትና ያልተፈቀደለትን የሚከለክሉ ስርአቶችን /firewall system/ መጠቀም ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ መረጃዎች ከላኪው ወደ ተቀባዩ እንዲደርሱ በሚደረግበት ወቅት መረጃው እንዳይታይ ወይም ትርጉም እንዳይሰጥ አድርገው የሚቀይሩ እንደ ፕሪንቶግራፊ/printography/ የመሳሰሉ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይቻላል። የኮምፒውተሮችን ደህንነት የሚጠብቁ ፍቃድ ያገኙ ሶፍትዌሮችንም መጠቀም ይመረጣል።
በዚህ አይነቱ የዲጂታል ንግድ ውስጥ ሲገባ ትልቁ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉት ያልተፈቀደላቸው ተጠቃሚዎች/ unauthorized users/ ናቸው። ከሶፍትዌሩ በተጨማሪ እነርሱን መጠበቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ መንገዶችን መከተል ይገባል።እነዚህን መንገዶች የሚያውቁ የሰለጠኑ ባለሙያዎችንም ማፍራት ያስፈልጋል።ይህን በማድረግ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንኳን ባይቻል መቀነስ ግን ይቻላል።የቅድመ መከላከልና ድረ መከላከልን ታሳቢ ያደረጉ የሶፍትዌር መፍትሄዎችንም ማመቻቸት ይገባል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 23/2012
አስናቀ ፀጋዬ