ከማሳ ዝግጅት እስከ ግብዓት አቅርቦት፤ ከግብዓት አጠቃቀም እስከ ተስማሚ የዝናብ ሁኔታ የሚገለጸው የ2011/12 የአማራ ክልል የሰብል ልማት ስራ፤ ተገቢውን ግብዓት ተጠቅሞ በወቅቱ በመዝራት የአርሶአደሮች ትጋት የታየበት ነው፡፡ ይሄም በግል ማሳም ሆነ በኩታ ገጠም እርሻዎች ላይ ያሉ ሰብሎች ቁመና ያማረ፤ የተሻለ ውጤት እንዲጠበቅ ያደረገም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ የአንበጣ መንጋ፣ የግሪሳ ወፍና ሌሎችም የሰብልን ምርታመነት የሚጎዱ ፈታኝ ሁነቶች ተከስተው አልፈዋል፡፡ ዛሬም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የአደጋ ጥላውን ዘርግቷል፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በምርት ዘመኑ በክልሉ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋስ ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
እቅድና ሂደት
በ2011/12 የምርት ዘመን ወደ 4 ነጥብ 46 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በማልማት 120 ሚሊዬን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል፡፡ እቅዱን ለማሳካትም ከፈጻሚ አካላት ጋር ከውይይት ጀምሮ እቅዱን የጋራ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ለባለሙያዎችና አርሷደሮች ስልጠና የመስጠት ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡ ለምርት እድገቱ ወሳኝ የሆኑ እንደ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አይነት ግብዓቶችም በወቅቱና በሚፈለገው አግባብ ለአርሷደሩ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡
ከግብዓት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከዓመት ዓመት መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አምና 4 ነጥብ 49 ሚሊዬን ኩንታል ማዳበሪያ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ ወደ 5 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ይህም የዘንድሮው የማዳበሪያ አጠቃቀም ከዓምናው አንጻር ሲታይ ወደ 500 ሺ ኩንታል ጭማሪ ማሳየቱ ብቻ ሳይሆን፤ አርሶ አደሩ በፈለገው አግባብ ግብዓቶችን አግኝቶ እንዲዘራ እድል የተፈጠረለት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ባለው ሁኔታም አራት ሚሊዬን 387 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል፡፡ የተዘራው ሰብልም የመሰብሰብ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ እርምጃዎች
ምርት የማምረት ሂደት አርሶና ዘርቶ ቁጭ የሚባልበት ሳይሆን፤ የማሳ ክትትል ማድረግን የሚጠይቅ ስራ ነው። በዚህም አርሶአደሩ በየጊዜው በሚያደርገው አሰሳ በማሳው ላይ የሚከሰቱ ነገሮችን እየለየ በወቅቱ እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፣ አረም ሲከሰት የማረምና በጸረ አረም መድሃኒት የመገልገል እርምጃን ይወስዳል፡፡ ዋግና መሰል በሽታዎች ተከስተው ሲያይ በተመሳሳይ በባለሙያዎች ጭምር በመታገዝ መድሃኒት በመርጨት የመከላከል ስራ ያከናውናል፡፡ እስካሁንም በአረምም ሆነ በዋግ ላይ የታዩ ችግሮችን አርሷደሩ በዚህ አግባብ ሲከላከል ቆይቷል፡፡
ከዚህ ውጪ በክልሉ የተከሰተውን የበረሃ አምበጣና የግሪሳ ወፍ የመከላከል ሰፊ ስራ ተከናውኗል፡፡ ለምሳሌ፣ በምስራቅ አማራ በተለይም በአፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ ተከስቶ ነበር፡፡ ይሄን ከመከላከል አኳያ አንበጣው ወደ ክልሉ እንዳይገባ ጭምር አፋር ክልል ድረስ በመሄድ የመከላከል ስራ ተከናውኗል፤ እንቁላል የሚጥልበትን ቦታ የመለየትና የመከላከል፤ ወደ ክልሉ በገባባቸው ወረዳዎች ላይም ህብረተሰቡን በማስተባበር በባህላዊ መንገድና በአውሮፕላን ጭምር በመታገዝ የመድሃኒት ርጭት በማካሄድ መከላከል ተችሏል፡፡ የተከሰተው መንጋ በርከት ያለ ቢሆንም አሁን ላይ የአንበጣ መንጋውን መቆጣጠር ተችሏል፤ ምናልባት ሌላ የሚከሰት ካለ በሚልም የማሰስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ማህበረሰብ ዞን ከተከሰተው የግሪሳ ወፍ ጋር በተያያዘም ክትትል በማድረግ የመከላከል ስራ የተሰራ ሲሆን፤ የአውሮፕላን ርጭት ስራ ተሰርቶ መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የአንበጣ መንጋውም ሆነ የግሪሳ ወፍ ክስተቱ በደረሱ ሰብሎች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ሰብሎችን በህብረት የመሰብሰብ ተግባራትም ተከናውኗል፡፡ ክስተቱ ምን ያክል ጉዳት አድርሷል የሚለውን ለመለየትም በየቀበሌው የተጽዕኖ ግምገማ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
የሰብሎች ወቅታዊ ቁመናና ስጋቶች
በአሁኑ ወቅትም በማሳ ላይ ያለው ሰብል የተቀመጠውን እቅድ ስለማሳካት አለማሳካቱ ለመገመት የመጀመሪያ ዙር የምርት ግምገማ እየተሰራ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይም እቅዱ ይሳካል የሚል ግምት ተወስዷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምቹ የዝናብ ሁኔታ የነበረ መሆኑ፣ አርሷደሩ ግብዓት ተጠቅሞ በወቅቱ መዝራቱ፣ ከሰብል በሽታም ሆነ ተባይ ጋር ተያይዞ የተከናወኑ ተግባራት እና ዝግጅትን ጀምሮ የተሰሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በክልሉ በየግልም ሆነ በኩታ ገጠም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ያለው የሰብል እድገት ሁኔታ የተሻለና እቅዱን ሊያሳካ በሚያስችል አቋም ላይ መሆኑ ለስኬታማነቱ ማሳዎች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም የሚጠበቀውን ውጤት ከማግኘት አኳያ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናም መኖሩ ስጋት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ያለወቅቱ የሚጥለው ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡ ይህ ከተከሰተ ደግሞ በሰብል ላይ ሙሉ በሙሉ ነው ጉዳት የሚያደርሰው፡፡ በመሆኑም ጉዳት እንዳያደርስ ለአርሶ አደሩ ቀድሞ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ሰብሎች በደረሱበት አካባቢ አርሷደሩ ተቀናጅቶ ምርቱን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጭምር በምርት መሰብሰብ ሂደቱ ላይ ከአርሶአደሩ ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
መልዕክት
የሰብል ምርት ውጤት የሚለካው ማሳ ላይ ባለው ቁመና ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰብልን በመሰብሰብና በማከማቸት ሂደት የሚፈጠሩ ብክነቶች ለምርታማነት የራሳቸው አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ በመሆኑም የምርት ስብሰባና ክምችት ሂደቱ ትልቅ ትኩረትና ጥንቃቄን የሚፈልግ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራር ለዚህ ስራ ትኩረት ሰጥቶ የማስተባበር ስራውን መስራት አለበት፡፡ ባለሙያውም ከአርሶአደሩ ጎን ሆኖ የሙያ ምክርና እገዛ መስጠት አለበት፡፡
ለምሳሌ፣ በአጨዳ ወቅት ዝናብ ስላለ ብቻ እርጥቡንም ደረቁንም የመሰብሰብ ሳይሆን ለአጨዳ የደረሰውን ለይቶ የመሰብሰብ፣ ሲከምር ዝናብ በማያስገባ፣ ጎርፍ በማይነካውና ምስጥም በማይበላው መልኩ ሊሆን እንደሚገባው ማስገንዘብና ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አርሶ አደሩም ምርቱ የራሱ መሆኑን አስቦና ባለሙያ የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ ያለውን ጉልበት በማስተባበር ሰብሉን መሰብሰብ አለበት፡፡ በዚህ መልኩ አመራሩ፣ ባለሙያውና አርሶአደሩ ተቀናጅተው መስራት ከቻሉ ይደርሳል የሚባለውን ጉዳት መቀነስ፤ የሚጠበቀውን ውጤትም ማሳካት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 22/2012
ወንድወሰን ሽመልስ