“የህይወት ጉዞ ሲከብድህ አንተ ክብደት ጨምረህ መንገድህን ቀጥል።” ይህ የቆየ አባባል ነው። በሌላ አባባል ችግር ሲገጥምህ ችግሩን ለማስቸገር በሃይልም በጥበብም በርታ እንጂ ችግሩ እንዲያሸንፍህ እድል አትስጠው። ይህንን አውቀውበት፣ ጉዟቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ብዙው ሰው ነገር ይምታታበታል፤ ከጉዞው ተደነቃቅፎ ይቀራል።
ለመሆኑ ይህን የመቻል ጥበብና ብልሃት ከየት እናገኘዋለን። ከዘራችን ነው? ከጅስማችን? በእድል የምናገኘው ነው? ወይስ ለማሸነፍ ከተዘጋጀ ብርቱ ፈቃድ ነው? ከየት ነው?
እስቲ የአፍሪካ ተምሳሌቱን፣ ኔልሰን ማንዴላን እንይ። በወቅቱ የነበረውን የዘር መድልዎ፣ ወይም የአፓርታይድ አገዛዝ፣ ሲታገል ተይዞ ለ27 ዓመታት በህንድ ውቅያኖስ ውስጥ ባለችው የሮበን ደሴት ጠባብ እስር ቤት ውስጥ፣ ከከባድ ሥራ ጋር የወህኒ (እስር) ቆይታውን አብቅቶ ነው፤ በኋላ ላይ በሀገሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሪ ለመሆን የቻለው። የእስሩ ዘመን ሰቆቃ በቃላት ከመግለጽ በላይ የሚዘገንን፣ መፈጠርን የሚያሰጠላና አሳሪዎቹን በስልጣን ዘመኑ ክፉኛ ሊያስቀጣቸው የሚችል ግፍ ነው፤ የፈፀሙበት። ይሁንናም ክፉዎችን በክፋታቸው የጠላሁትንና የታገልኳቸውን ያህል ተመሳሳይ በደል ከፈፀምኩባቸው፣ እኔ ከእነርሱ የተሻልኩ መሆኔን በምን አሳያቸዋለሁ? ሲል መናገሩ ይታወሳል።
ለማከል ያህል አንድ ቀን፣ የክብር- ዘቦቹን፣ እስቲ እንደማንኛውም ደቡብ አፍሪካዊ ወደ አንድ ካፌ ውስጥ ጎራ እንበልና፤ ምግብ እንመገብ ሲል ይጠይቃቸዋል። አጃቢዎቹም ተስማምተው፣ ከቤተመንግስት አብረውት ይወጣሉ። በድንገትም የገቡበት ካፌ ውስጥ ነጮቹም ጥቁሮችም ደቡብ አፍሪካውያን ይመገቡ ነበርና አንድም የታገልኩት ለዚህ ነበር ብሎ፣ በዚህ ተደስቶ ሳያበቃ ፣ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ራቅ ብሎ ተቀምጦ የነበረን “አንድ ነጭ” እባክህ አብረን እንብላ፣ ሲል ማንዴላ ይጋብዘዋል።
ያ፣ ነጭም ሲፈራ ሲቸር ይመጣና አብሯቸው ይመገባል። ከጠባቂዎቹ አንዱ ተመግበው ከወጡ በኋላ “ማዲባ፣ (የማንዴለ ሌላው ስም ነው) ሰውየው እኮ ማእዱ ላይ እጆቹ ይንቀጠቀጡ ነበረ፤ አልተረጋጋም፤ ለምን እንዲበላ ግድ አልከው?” ሲል ይጠይቃል። ስወጣ በደንብ ሰላም ያላልኩት የበለጠ እንዳይፈራ ብዬ ነው። ያ፣ ሰው ለምን እንደዚህ እንደሆነ አታውቁም፤ ግን ምክንያት አለው። በሮበን ደሴት እስር ላይ በነበርኩ ጊዜ ክፉኛ ያሰቃየኝ የነበረና የጉልበት ሥራውን እየሰራሁ እንኳን ይደበድበኝ የነበረ ሰው ነው፤ እንዲሁም አሞኛል ፤ ውሃ ስጠኝ ስለው ሽንቱን ፊቴ ላይ ይሸና የነበረ ሰው ነው። ይኼ ሰው የሥርዓቱ ውጤት እንጂ በራሱ ያከናወነው አንዳች ነገር የለም፤ እኔ ደግሞ፣ የታገልኩት ከነጭም ከጥቁርም ኢ-ሰብዓዊነት ጋር ስለሆነ ነው፤ በፍቅር የጋበዝኩት። አስገራሚ አጋጣሚ ነው።
ምናልባትም ሊይዙት የመጡ መስሎት አለመበርገጉም መልካም ነው። የሰው ልጅ ጊዜውና ሁኔታው ስለፈቀደለት ብቻ በማንም ላይ ግፍ ሊፈጽም አይገባውም። መቼና በምን ዓይነት ብድሩ እንደሚከፈለው አያውቅም ። ማንዴላን የመሰለ መልአክ አከል ሰው ገጥሟቸው ነው እንጂ፤ የብዙዎቹ ግፍ የሚያኗኑር አልነበረም። ለዓለምና ለአፍሪካችን አርዓያነት ያለው ተግባር ፈጽሞ ነው፤ ያለፈው። ጠላቶቹን የሚያስገርሙ ወዳጆቹ አድርጎ ያለፈ መሪ ነው፤ ማንዴላ።
ወደ አሜሪካ ጎራ ስንል ደግሞ፣ አብርሃም ሊንከንን እናገኘዋለን፣ ተስፋ በሚያስቆርጥና አድካሚ በሆነ ህይወት ውስጥ ያለፈ ንግዱ ኪሳራ ላይ የወደቀና ስምንት ጊዜ ለፓርላማ ወንበር ተወዳድሮ ያልተሳካለት ሰው ነበረ፤ አሜሪካን በነውጥ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ፣ (1861-1864 ዓ.ም) ሌሎች ተስፋ ሲቆርጡና ሃገሪቱ ለአመራር አትመችም ብለው ሲያፈገፍጉ፣ ባለፉት ምርጫዎች መውደቁ ተስፋ ሳያስቆርጠው ግን፣ አሜሪካንን “ከኮንፌዴራሊስቶች እና የባሪያ አሳዳሪዎች” ነጻ ለማውጣት በመታገል የሃገሩ የክፉ ቀን መሪ ለመሆን በመብቃት አሜሪካን ፌዴራላዊና አንድነት ያላት ሐገር እንድትሆን፣ ብቻ ሳይሆን ጥቁሮች ባለመብት የሆኑባትና ባርነትን በአዋጅ ያስከለከለች ሐገር እንድትሆን መሰረት ጥሎ ሁል ጊዜ ስሙ በክብር የሚወሳ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅቷል።
እንዲያውም አንድ እውቅ አባባል አለችው፤ “ስለነጻነት በብርቱ እየተሟገትኩ ባለባሪያ ከሆንኩኝ ምኑን ነጻ ሰው ሆንኩ?” ይል ነበረ። ይህንንም ሲያብራራው በእኔ እጅ ሲሆን ማናቸውንም የአገዛዝ መንገድ (ጭካኔ በተሞላበትም መንገድ ቢሆን) ቅዱስ ነው እያልኩኝ፣ ሌሎች ሲያስተዳድሩ መልካምም ቢሆን ካጣጣልኩኝ የገዛ እምነቴ እስረኛ እንጂ ለሌሎች ግድ የሌለኝ ግብዝ ነኝ፤ ማለት ነው፤ ይል ነበረ። ታዲያ ፣ አንድ ምሽት ቲያትር ሲያይ ባለበት ነው፤ አንድ በነጭ የበላይነት የሚያምን ስም-የለሽ የባለባሪያዎች ቅጥረኛ የሆነ፣ ዘረኛ ነፍሰ ገዳይ ድንገት ወደ መድረክ ወጥቶ፤ በቀጥታ ፊት ለፊት በተቀመጠው፣ ሊንከን ላይ በመተኮስ ገደለው። የአብርሐም ሊንከንን ዓላማ ግን ማስቆም ስላልቻለ አሜሪካ ከ1865 ዓ.ም ወዲህ ፌዴራላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ሃገርና የነፃነት አርዓያ ሆና ቀጥላለች።
በልጅነት ህይወታቸው ከቶውንም አሁን ላሉበት ስፍራ ይደርሳሉ ተብለው የማይጠበቁ፣ በተጎሳቆለ፣ በተጣለና በአሳዛኝ ህይወት ውስጥ ያለፉ በርካታ ሰዎችን ህይወት ልንገልፅላችሁ እንችላለን። አሁን በቅርቡ ከሁለት ጊዜ የስልጣን ዘመን ቆይታ በኋላ ለታወቀው የቀድሞ የኤሲሚላን እንዲሁም የላይቤሪያ ብሄራዊ የእግርኳስ ቡድን ተጫዋች ለነበረው ጆርጅ ዊሃ ስልጣናቸውን በምርጫ የለቀቁት ላይቤሪያዊቷ ጆሴፍ ሰርሊፍ በልጅነታቸው፤ ከአንዴም ሁለቴ ህሊናውን ባጣ ጎረምሳ ተደፍረዋል፤ በአንባገነኖቹ የሀገራቸው መሪዎች፣ ተደቁሰዋል፤ ይህ ግን ውሎ አድሮ በጽናት በመቆም፣ ሃገራቸውን በፕሬዚዳንትነት ከማገልገልና በሰላም ከመምራት አላገዳቸውም።
ታዋቂዋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ኦፕራህ ዌንፍሬይ የተጣሉና የተረሱ ጥቁር ሴት አሜሪካውያን ምሳሌ ናት። የልጅነት ጎስቋላው ህይወቷ ወደ ታዋቂነት ማማ ከመምጣት አላገዳትም። ዓለም የሰጠቻትን አስቀያሚ ገጽ ትታ ጥሩውን ማንበብ የቻለች፣ ኑሮ በቡጢ ስትመታት ጡጫውን ችላ ወደ ላይ ለመመንጠቅ ያላቅማማች ብርቱ ሴት ናት። እርሷም በአንድ “አዋራጅ” (ምንም እንኳን ውርደቱ የእርሱ ቢሆንም) የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባት ነበረ። ያንን ሰቀቀን ግን አልፋ፣ በዓለም ዙሪያ የተገፉና ትምህርታቸውን በልዩ ልዩ እንቅፋት ሳቢያ የተጓጎለባቸው ወጣት ሴቶችን የሚደግፍ ተቋም በመመስረት እያገለገለች ጭምር ነው። በአሁን ሰዓት ያላት ሐብት ከ2 ቢሊየን ተኩል ዶላር በላይ የሚገመት ነው፤ በመደፈሯና ከድሃ ቤተሰብ በመወለዷ ድህነቷ ላይ አልቆመችም፤ አልተስተጓጎለችም።
እነዚህ ከላይ የተገለፁት ሰዎች ከባዱን “ፈተናቸውን ራሱን በመፈተን” ገፍቶ እንዳልጣላቸው፣ ማሳያዎች ሆነዋል። ብዙ ሰዎች ግን ችግር ከፊታቸው ሲደቀን አንድም ወደ ኋላ ያፈገፍጋሉ፤ አለበለዚያም ተስፋ ቆርጠው ያልተገባ እርምጃ ይወስዳሉ። ወደ መጠጥ፣ ጫት፣ ዕጽና ወደ ተደባዳቢነትና ሃይል ወደ መጠቀም የሚዞሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በአሜሪካ 16000 ሰዎች፣ በ2010 ዓመተምህረት ራሳቸውን አጥፍተዋል። በሚተዋቸውም ማስታወሻዎች ላይ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ለማለፍ አቅም ማጣታቸውንና ለወሰዱት እርምጃም በቅደም ተከተል፡-
• የትዳር አጋሮቻቸው ስላስቸገሯቸው፣
• ዘመዶቻቸው ሊረዷቸውና ሊያግዟቸው ስላልቻሉ ወይም ስላልፈለጉ፣
• የሥራ አለቆቻቸው ስለበደሏቸውና በንቀት ስላዩዋቸው፣
• አብሮአደግ ጓደኞቻቸው ቃላቸውን ስላጠፉባቸው እና የሥራቸውን ባህሪ አድካሚነትና አሰልቺነት እንደ ምክንያት ወይም ሰበብ አቅርበዋል ወይም ገልጠውታል።
ይሁንናም እነዚህ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች፣ እነርሱ ያለፉባቸውን መንገዶች ሌሎች ሰዎች እንዳለፉባቸው እና እንደተጋፈጧቸው አያውቁም፤ ወይም አይጠይቁም። ግን በራሳቸው ላይ እርምጃ በመውሰድ ዳግም የማያገኙትን ህይወት ይቀጥፋሉ ወይም የአኗኗር ዘይቤያቸውን ያበላሻሉ።
በነገራችን ላይ ታዋቂዋ ሰባኪ፣ ጆይስ ሜየር፣ በልጅነቷ በተደጋጋሚ በወሲብ የመደፈር አደጋ ገጥሟታል፤ ያውም፣ በሰካራሙ የገዛ አባቷ ነበረ ጥቃቱ የሚፈፀምባት። ግን ለራሷ ብቻ አይደለም፤ ለዓለም ሁሉ በሚተርፍ የእምነትና የሥነልቡና ሃይል ለሌሎች መድኃኒት ሆና እየኖረች ነው። ዛሬም፣ በ67ኛው የእድሜ ዘመኗ አሁንም የሚገጥሟትን የጤና እክልና የዘለፋ ውርጅብኝ እየተቀበለች ህይወቷን እየመራችና ሌሎችን እየገራች ነው። ድንቅ ሰብዕና ነው!!
በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ህጻናት በአሜሪካ ውስጥ የቤት ውስጥ የኃይልና የወሲብ ጥቃት ይፈፀምባቸዋል። ከዚህ በሶስት እጥፍ የሚቆጠሩ ወጣቶች ደግሞ፣ ሊወጡባቸው እንደማይችሉ በሚገምቷቸው የህይወት አዘቅት ውስጥ ሆነው እየተርመጠመጡ ነው። ለዚህ ነው፤ ይህን ትምህርት ማካፈል ያስፈለገው። ማንም ታላቅ ሰው ወደ ታላቅነቱ ለመድረስ ሲነሳ ነገር ሁሉ፣ እንደ ሶፍት ጨርቅ ምቹ ሆኖለት፣ በለሳላሳ ፍራሽ ላይ ተንፈላስሶ አልደረሰም። በአስቸጋሪና ገዳዳ መንገዶች ላይ እየተረማመደ ነው፤ እንጂ።
በራሴ ቤተሰብ አስተዳደግ ውስጥ ሁሉ ሞልቶ ተርፎልን፣ የእንጀራ ጠርዝ እጄን ቆረጠው፣ ጥቁር ወተት አማረኝ፤ ነጭ ቁራ አምጡልኝ ፤ አንበሳ አስጋልቡኝ ብዬ አላደግኩም። እንዲያውም በተቃራኒው “ይቺን ጥፋት ከደገምክ ለጅብ እሰጥሃለሁ፣…… “አኩራፊ ልጅ እራቱ ቁርሱ ይሆናል፤…. “ይቺን ወተት አሁን ካልጠጣህ “አዱሬ” (ኦሮምኛ ድመት መሆኑን ልብ ይሏል) ጥሪበት…. ተብዬ ተቀናቃኝ ተዘጋጅቶልኝ ነው፤ ያደግሁት። በህይወታችን ውስጥ አስተዳደጋችን ምን ቢያምር እንኳን ችግራችን ግን ከመረረ ልንጋፈጠው የምንነሳው በትጋት መሆን አለበት። አብዛኛውን ጊዜ፣ ሳይደላው ያደገ ደግሞ ለህይወት የሚሰጠው ዋጋ ምርጥ እና ከፍ ያለ ነው፤ መሆን ያለበት። በተስፋ መቁረጥ ደመና ውስጥ የሚንሳፈፍ ከሆነ የሚጨብጠው ጉም ነው፤ የትም አይደርስም።
ገና ልጅ እያለሁ እንዳባቴ መምህር መሆን ነበር፤ የሚያምረኝ። ለአስተማሪነት ራሴን ሳዘጋጅ ግን ማስተማር እንደማልችልና ለዚያ እንዳልተጠራሁ ገመትኩኝና ተውኩት። ትንሽ ቆይቼ ነጋዴ ሆንኩ፤ ሸቀጤ በስጦታ አለቀና አቋረጥኩኝ። ከዚያም ሌላ፣ ሌላ ንግድ ሞከርኩና ዱቤ የወሰዱት ሰዎች በአስገራሚ ሁኔታ ለተጨማሪ ዱቤ እንጂ የቀደመውን ለመክፈል እንደማይመጡ ሳውቅ እርግፍ አድርጌ ተውኩት።
ከእናንተ መካከል እንኳንስ በተስጧችሁ፣ በሰለጠናችሁት ትምህርት መስራት የቻላችሁ ስንቶች ናችሁ? ትዳራችሁ ጭቃ ውስጥ እንደገባ የመኪና ጎማ እዛው እዛው የሚሽከረከርባችሁስ? ልጆቻችሁ ሰጭ ለመሆን በሚገባቸው እድሜ ሳይሆኑ የቀሩባችሁስ? የማይወጣ እቁብ የሚጥል ባል ያላችሁ፣ ባሎቻችሁ በአልኮል መጠጥ ሽንቁር ጋን የሆኑባችሁ….. አኩራፊ ዘመድ ቤት ውስጥ ያላችሁ፣ በእዚህ መሐል ልባችሁ የሚቆስልባችሁ ትኖራላችሁ። ትንንሽ የሚመስሉ ውስጥን የሚያነፍሩ የግንኙነታችሁን ሰንሰለት ያሰለሰሉ ጉዳዮች ያሉባችሁ አላችሁ ብዬ አስባለሁ።
እናስ…ምን ለማድረግ አሰባችሁ ችግሩን እያያችሁት መብሰልሰል ነው ወይስ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ፈተናችሁን መፈተን ነው፤ የምታስቡት። ወይስ ጨለማው ላይ በማፍጠጥ ብርሃን እንዲሆንላችሁ ነው፤ የምታዩት? ወይስ ድንጋዩን ከድንጋይ በማጋጨት የብርሃን ብልጭታ መፍጠር ነው፤ የምታስቡት….? ምርጫችሁ መሆን ያለበት ፈተናውን ራሱን መፈተን ( “ተ” ን ጠበቅ አድርጋችሁ አንብቧት) ነው። አስቸጋሪውን ነገር ማስቸገር እንጂ እርጥብ እንጨት አልነድ ብሏት እንደምትተክዝ ምስኪን እናት መቆዘም የለባችሁም።
እናም፣ ህይወት አዎንታዊ ገጽታ እንዳላት ማሰብ አለባችሁ። እኔ ግን ከመምህርነቴም ባሻገር 2ኛና ሶስተኛ ዲግሪ መስራት የምችልበት አቅም እንዳለኝ አውቂያለሁ፤ ጥብቅ ቁጥጥር ካለበት ቤተሰብ ውስጥ ወጥቼ በፍቅር መኖር ተለማምጃለሁ፤ ኑሮ ስትጎሽመኝ መላ መምታት አውቄበታለሁ፤ የገጠመኝን የህይወት እንቅፋት መጥረግ ችዬበታለሁ።
• ለዚህም የነበርኩባቸው ጎረቤቶቼ አኗኗር ምቹ ነበርና ስለዓለም ተስፋ እንዲያድርብኝ ሆኛለሁ።
• የሚወዱኝ ሰዎች ሁሌ ሊደግፉኝ ዝግጁዎች መሆናቸውን አውቂያለሁ።
• በትምህርቴ ሰነፍ አልነበርኩምና አልወደቅኩም።
• በማህበራዊ ምሳሌነት የማያቸው መልካም ሰዎች ነበሩ።
• እጅግ ደስ የተሰኘሁባቸው አጋጣሚዎች በህይወት ውስጥ እንደነበሩ አምናለሁ፤ እንጂ በገጠመኝ ሃዘን ተጀምሮ በሃዘን የሚደመደም ህይወት አላስተናግድም ብዬ ለራሴ ነግሬዋለሁ። ለሐዘን አልተፈጠርኩማ! ምን በወጣኝና እየቆዘምኩ አምላኬን የሐዘን አምላክ አደርገዋለሁ።
• እርምጃዎቼ ይፍጠኑም ይዘግዩ ወደ ፊት እጓዝ ነበር እንጂ፤ አልቆምኩም።
• እርሱ የደስታዬ ምክንያት፣ የመጽናናቴ ጉልበት፣ የፍስሐዬ ምልክት፣ የአቀበቴ መደገፊያ፣ የፈተናዬ መሻገሪያ፣ የብልሃት ጓደኛዬ…..አድርጌ ጌታዬ እና አምላኬን አምነዋለሁኝ !! ብዬ መነሳት ብዙ ጊዜ ችዬበታለሁ።
ወድቀው የቀሩ ሰዎችን ሳስብ እኔ ወደመጣሁበት ደረጃ ያመጣኝን ጠንካራ መንፈስ አላገኙትም ነበረ ብዬ አስባለሁ። በተለይ በቤታችን ውስጥ በአካልም በመንፈስም ውጊያ የሚጋጩንን ክፉ አጋጣሚዎችን ተቀብለን የምናስተናግድበት መንገድ ማንነታችንን እየቀረፀ ለተሻለ ማንነት እንዲያበቃን እንጂ እንዲጥለን እድል ፈንታ አንስጠው።
በአካባቢያችን ያለውን ማህበረሰብ ሚና አሳንሰን ማየት አይገባንም። እነርሱ የእኛ ዋርካዎች ናቸው። ወላጆቻችን፣ ዘመዶቻችን፣ እህትና ወንድሞቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ መምህሮቻችን፣ በጥቅሉም ማህበረሰቡ በህይወታችን ላይ ብርቱ ሚና አላቸው። ዛሬ የሆንነውን መሆን እንድንሆን የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋልና፤ በቸልታ አንያቸው።
ህይወት ከባድ ናት፤ ልንጋፈጠው የሚገባን ገጽ በውስጧ አለ። ህይወት ከፍለ ጥራዝ ያለው መጽሐፍን ብታክል ፈተናው አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥም ገጽ እንጂ በፈተና የተሞላ የጨለማ ንባብ አለመሆኑን ማወቅ ይገባናል። የፈተና ገጹ እንዳይገጥመን ስንል መጽሐፉን አሽቀንጥረን አንጥለውም፤ ብቻችንንም አንጋፈጠውም። በአጠገባችን ካሉ ሰዎች ጋር በመሆን እርስ በእርሳችን በመደጋገፍና በመነጋገር ግን መከራችንን ማቅለል እንችላለን። (መልካም ጓደኛችሁን በማሰብ ከጎናችሁ ያለውን ሰው፣ አለህ/ ሽልኝና ላመሰግንህ እወዳለሁ፤ ተባባሉ)
መልካም የወዳጅነት ሳምንት ይሁንላ ችሁ!!
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ