የኑሮ ውድነት፣ የሸቀጥና የምርት ዋጋ እንዲሁም የቤት ኪራይ ንረት የሀገራችንን ህብረተሰብ እያማረረ ነው። እለት ከእለት እያሻቀበ ያለው የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ጫናው የሚበረታው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢሆንም እንደ ሀገር ችግሩን እንዴት እንግታው? በጊዜያዊነትና በዘላቂነትስ ሀገራችን ከችግሩ እንዴት ትውጣ? የሚሉት ጉዳዮች መላው የሀገሪቷ ህብረተሰብ፣ የመንግስት፣ የኢኮኖሚ ምሁራንና ሌሎች በጉዳዩ ላይ ሚና ያላቸው አካላት መነጋገሪያ ሆኗል።
የዋጋ ንረት መነሻ ገፊ ምክንያቶች
በዋነኝነት ለዋጋ ንረት መፈጠር ሁለት ዋና ዋና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች ሲኖሩ እነዚህም በፍላጎት ግፊት (demand push inflation) የመነጨ የዋጋ ንረት እና በማምረቻ ዋጋ መጨመር ግፊት (supply cost inflation) የመነጨ የዋጋ ንረት በመባል ይታወቃሉ።እነዚህ ሁለቱ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ገፊ ምክንያቶች ሲሆኑ አጠቃላይ ለዋጋ ንረት አስተዋፆኦ ያበረክታሉ። በፍላጎት መመጨር የሚፈጠር የዋጋ ንረት (Demand push inflation) በዋነኝት የሚፈጠረውም ተጠቃሚዎች የተመረቱትን ሸቀጦች እና አገልግሎቶች የመጠቀም ዝንባሌያቸው ከአቅርቦት ጋር ሳይጣጣም ሲቀር የሚፈጠር ነዉ። ሁለተኛው በፍላጎት መጨመር ለሚያጋጥም የዋጋ ንረት ምክንያት የአንድ አገር ፖሊሲ ሲሆን ይህም ሊፈጠር የሚችለው መንግስት ወጪ ሲጨምር ወይንም ታክስ ሲቀንስ ነው።
ሌላኛው ለክሰተቱ መፈጠር ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ሰርጭት መኖር በፍላጎት ግፊት የመነጨ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል። የገንዘብ አቅርቦት ማለት በካሽ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የብድር አይነቶችን ያጠቃልላል። የገንዘብ አቅርቦት ሲጨምር የዶላርን ዋጋ ይቀንሰዋል፤ ዶላር ከውጭ አገራት ገንዘቦች ጋር ያለው ግብይት ሲቀንስ ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች ዋጋ ይጨምራል፣ ይሄውም አጠቃላይ የዋጋ ንረት በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል።
በሀገራችን ለተከሰተው የዋጋ ንረት መንስኤዎች
የፋብሪካ ባለቤቶች፣ የቸርቻሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ቢታመንም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመተባበር ህገ-ወጥነትን የመከላከል ሚናው ዝቅተኛ መሆን ለዋጋ ንረት አስተዋጽኦ አበርክቷል። መንግስት ልዩ የዋጋ ድጋፍ ወይም ድጎማ በማድረግ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባቸው የፓልም ዘይት፣ስኳርና ስንዴ በየሰፈሩና በየመንገዱ ዳር በህገወጥ ነጋዴዎች/ቸርቻሪዎች ሲሸጥ እየተመለከተ እንዳላዩ ማለፍና አለፍ ሲልም ለህገወጦች ተባባሪ መሆን ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በግብይት ሂደቱ የደላላ ጣልቃ ገብነት፣ ምርትን በክምችት መያዝ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ውድድር/ ዋጋ መወሰን/፣ ያለደረሰኝ ግብይት ማካሄድ እና ፎርጅድ ደረሰኝ የመያዝ እንዲሁም ደረሰኝ ሲጠየቁ አንሸጥም የማለት፣ የመግዣ ዋጋ አለማሳየትና የመሸጫ ዋጋን አለመለጠፍ፣ የህገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት፣ የዩኒየኖችና የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የአቅም፣ የክህሎትና የአሠራር ውስንነት እንዲሁም የስነ-ምግባር ችግር የሚታይባቸው መሆኑ፣ ያለንግድ ፈቃድ በመኪና ላይ የአየር በአየር የመቀባበል ሥራ መስፋፋቱ፣ የተጭበረበሩ የንግድ ሰነዶችን መጠቀም በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
የዋጋ ንረት ኢኮኖሚያዊ አንድምታ አለውን?
በጽሁፌ መግቢያ እንደጠቀስኩት ለአንድ ሀገር የዋጋ ንረት በዋነኝነት ሁለት አይነት ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም ከፍላጎት መጨመር የመነጨ የዋጋ ንረት(demand push inflation) እና የማምረቻ ዋጋ መጨመር(cost push inflation)ናቸው።በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ስንመዝነው በሀገራችን የተከሰተው የዋጋ ንረት እዚህ ደረጃ ሊደርስ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አመክንዮ የለውም ወደሚለው ድምዳሜ ያደርሰናል። ምክንያቱም በዱቄት ፋብሪካዎች፣በዳቦ ቤቶች፣በዱቄት አምራቾች ማህበር፣በመንግስት አስፈጻሚ አካላት፣በፓልም የምግብ ዘይት፣በነዳጅ ዘይት፣በሰብል ምርቶች እና አትክልትና ፍራፍሬ እና በፍጆታ ምርቶች ላይ ኢ-ምክንያታዊ የዋጋ ጭማሬ መኖሩ ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።
መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ድጎማ አድርጎ ከውጪ ከሚያስገባቸው ምርቶች መካከል የዳቦ ስንዴ አንዱ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ 39 የዱቄት ፋብሪካዎች፣113 ዳቦ ቤቶችዎች፣እና 8 ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር የሚከተሉት ችግሮች ታይተዋል።
የዱቄት ፋብሪካዎች ጥራቱን ያልጠበቀ ስንዴ ቀላቅለው በመፍጨት መንግስት በድጎማ በሚያቀርበው የማዳበሪያ ከረጢት በመቀየር ትስስር ላልተደረገላቸው ዳቦ ቤቶች ጭምር መሸጥ፣ የድጎማውን የስንዴ ዱቄት በራሳቸው የተለየ (ስፔሻል) ዱቄት ማዳበሪያ ከረጢት በማሸግ ለገበያ በማቅረብ እስከ 2000 ብር መሸጥ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የድጎማ ስንዴ ትስስር ላልተፈጠረላቸው ነጋዴዎች አሳልፎ የመሸጥ ተግባር ታይቶባቸዋል።
የዱቄት ፋብሪካዎች ማህበር አመራሮች የፋብሪካ ባለቤቶችን መብት በማስከበር ላይ ብቻ መታጠር የዱቄት ፋብሪካዎች ግዴታቸውን እንዲያከብሩ አለማድረግ፣የድጎማውን ስንዴ ጥራት ከሌለው የሀገር ውስጥ ስንዴ ጋር ቀላቅለው የሚፈጩትን፣ትስስር ከተፈጠረላቸው ውጪ የሚሸጡትን፣ከረጢት ቀይረው ልዩ ዱቄት ብለው በውድ ዋጋ የሚሸጡትን በዝምታ ማለፍ፣ለአባላት መብትና ጥቅም እንጂ ለህዝብ ሰቆቃ አለመጨነቅ ህግ አክብረውና የህብረተሰቡን ፍላጎት ጠብቀው እንዲሰሩ አለማድረግ፣የቁጥጥር ሥራ ሲጀመር መንግስት ከእሳት ማጥፋት ይውጣ በገፍ ስንዴ ያቅርብ ወደ ሚል ኢ-ምክንያታዊ አመለካከት ታይቶባቸዋል።
የዋጋ ንረት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?
መንግስት ህብረተሰቡን ከኑሮ ውድነት ለመታደግ በሚያደረገው ርብርብ ያለአግባብ ዋጋ በሚጨምሩ፣ ምርት አከማችተው በሚይዙ፣አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ላይ በሚያደረገው ቁጥጥርና በሚወሰደው ህግን የማስከበር ሥራ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ፋና ወጊ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።የሕብረት ስራ ማህበራትም ከገበሬ ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠርና የክምችትን መጠን በመጨመር ለህብረተሰቡ በተመጣጠኝ ዋጋ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው።
ሀገራችን የምትከተለው የኢኮኖሚ ስርዓት የነፃ ኢኮኖሚ ስርዓት ነው። በዚህ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ደግሞ የግል ባለሃብቱ በነፃ የገበያ ውድድር ውስጥ በጥራት፣በአይነትና በዋጋ የተሻለ ምረትና አገልግሎት በአማራጭነትና በተወዳዳሪነት ይዞ በመቅረብ የሸማቾችን ፍላጎት በማርካት ኢኮኖሚውን ጤናማ በሆነ መንገድ ለማሳድግ እድል የሚሰጥ መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና ነፃ ገበያ ነፃ ዝርፊያ እሰከሚመስል ድረስ በሀገራችን የዋጋ ንረት ጀንበር ጠልቃ ምሽት በነጋ ቁጥር እየጨመረና እየተበባሰ የዜጎችን የመግዛት አቅምና የመኖር ህልውና እየተፈታተነው ይገኛል።
በየትኛውም ሀገር ቢሆን መንግስት ጣልቃ የማይገባበት የገበያ ኢኮኖሚ የለም። መጠኑ ይለያይ እንጂ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ የሚከተሉ የበለጸጉትም ሆኑ ታዳጊ ሀገራት የገበያ ጉድለት ሲያጋጥማቸው መንግስት ጣልቃ ገብቶ ጉድለቱን የሚሞላበት አሰራር አለ። ኢትዮጵያም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ልትሆን አትችልም። መንግስት በሃገራችን እየታዩ ያሉትን የገበያ ጉድለቶች በጥንቃቄ አጥንቶ ዘለቄታዊና በአጭር ጊዜ ጣልቃ ገብነት ሊፈቱ የሚችሉበትን በመለየት ጉድለቱን ለመቅርፍ የሚያስችሉ ስልቶችን ልምድ ካካበቱ ሀገራት በመማርና ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ጣልቃ ገብነቱን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ የገበያ ማረጋጋት ስራ መስራት ይኖርበታል።
የትርፍ ህዳግ በማስቀመጥ፣በአቋራጭ ለመክበር ሲሉ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው ዋጋ በመጨመር ሸማቹንና ገበያውን እያተራመሱ ያሉትን ራስ ወዳድና ስግብግብ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶችን ወደ ህጋዊ ስርዓቱ በማስገባት ወይንም ከንግድ ስርዓቱ ጠራርጎ በማስወጣት በአንፃሩ ህጋዊ መስመሩን ተከትለው የሚሰሩ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶችን በማበረታታት መንግስት የአመራር ሚናውን በብቃት መወጣት አለበት።
ተስፋዬ ታደሰ
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2012