ባለፉት ጥቂት ዓመታት በነበረው የፀጥታ አለመረጋጋት ምክንያት በኢንቨስትመንቶች ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዱ ነው። የክልሉ መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸው ኢንቨስትመንቶች መልሰው እንዲያገግሙ እና አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የተለያየ ጥረት እያደረገ ይገኛል። እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይ እና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደምሰው ባቾሬ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ደምሰው፡- በክልሉ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው ከለውጡ በፊት የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ነው።ከለውጡ በፊት በነበረው ጊዜ ላይ በክልላችን ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ነበር። ፍሰቱም ከፍተኛ ነበር።ለውጡ ሲጀምር ግን ከለውጡ ጋር በተያያዘ ኢንቨስትመንት ላይ ያነጣጠሩ ችግሮች ነበሩ። ከዚህም ጋር በተያያዘ በክልላችን ላይ በጣም ብዙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ሰፊ ጉዳት ደርሷል። በርካታ ሠራተኞችም ተፈናቅለዋል። በጣም ውጤታማ በነበሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ንብረት ተዘርፏል። ብዙ ፕሮጀክቶች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ተገደዋል።በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
ከ2010 በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥም ችግሩ ቀጥሎ ነበር። በተለይም ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ.ም ላይ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ መሰረት አድርጎ የነበረውን ብጥብጥ ተከትሎ በሲዳማ ዞን በነበሩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። ከሐምሌ 11/2011ዓ.ም ወዲህ መንግሥት ነገሮችን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ሰፊ ጥረትና ርብርብ አድርጓል። ካደረጋቸው ርብርቦች አንዱ ባለሃብቶች ተመልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነው። አንዳንዱ ባለሃብት ንብረቱ ወድሞበትም ችግር ገጥሞትም ተመልሰው ወደ ሥራ የመግባት ፍላጎት ያሳዩ ባለሃብቶች ነበሩ። ተመልሰው ወደዚያው እንዲገቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ላይ ብዙ ጥረት ተደርጎ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ኢንቨስትመንቱ ተመልሶ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ተመልሷል።
ቢያንስ የያዙት መሬት ላይ መልሰው ልማት ማልማት እንዲችሉ እድል አግኝተዋል። ለአብነት ያህል ጉራጌ ዞን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ አብዛኞቹ ኢንቨስተሮች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። በተመሳሳይ ከፋ ዞን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ቢያንስ ሥራቸውን እንዲሰሩና ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል መንግሥት ብዙ ሥራ ሰርቷል። በአሁኑ ወቅት ሁኔታው ተቀይሮ ኢንቨስተሮቹ ሥራቸውን ጀምረዋል። በተመሳሳይ በሲዳማም ባለሃብቱ ወደ ሥራው እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ሥራ በመስራትና የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር የተሻለ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል። አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችም ወደ ክልላችን እየመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨ ስትመንቶች ቁጥር ምን ያህል ናቸው። የወደመው የንብረት መጠንስ?
ደምሰው፡- በ2010 እና በ2011ዓ.ም 70 የሚሆኑ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሪፖርት ተደርጓል።ነገር ግን ጉዳት የደረሰባቸው ነገር ግን ሪፖርት ያላደረጉ ኢንቨስተሮች እንዳሉ መረጃዎች እየደረሱን ነው።አጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለመለየት ሁለት ዙር ላይ ሥራ ተሰርቷል። የመጀመሪያ ዙር ላይ በቀጥታ በዞን ካለው መዋቅር ጋር የትኛው ፕሮጀክቶች ላይ ነው ጉዳት የደረሰው የሚለውን መረጃ በመውሰድ ባለሃብቶችን በማግኘት መረጃ ተወስዷል። እሱን መነሻ አድርገን ከወሰድነው 70 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ሪፖርት ተደርገዋል።
ይህ በቂ ባለመሆኑ የክልሉ መንግሥት የጠራ መረጃ ለማግኘት ምን ያህል ፕሮጀክቶች ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል የሚለውን የገንዘብ ትመና ጭምር ለይታችሁ እንድታቀርቡልን ብሎ ባለፈው ነሐሴ ወር መጨ ረሻ አካባቢ ባስተላለፈው መልዕክት መሰረት ሁለት ቡድን ተቋቁሞ ታች ካለው የዞን አስተዳደር፣ ዞን ግብርና፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱ ከሚገኝበት ወረዳ ጋር በጋራ በመሆን የማጣራት እና ግምት የመተመን ሥራ ለመስራት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገን ለሰዎች ስምሪት ተሰጥቷቸው አንደኛው ቡድን ሄዶ የጋሞ፣ የጎፋ ዞን፣ የሲዳማ፣ የዳውሮ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶችን መረጃ የማሰባሰብ የመስክ ሥራ አጠናቆ መጥቷል።
ባለሃብቶች ከጉዳቱ በፊት ምን ይመስሉ እንደነበርና አሁን ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም የነበራቸውን የንብረት ሁኔታ፣ ስንት ሰራተኛ እንደነበራቸው፣ የአፈጻጸም ደረጃቸው በምን ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር የሚሉ መረጃዎች ከነሐሴ እስከ መስከረም ወር ውስጥ ባሉት ጊዜያት መረጃዎችን የማደራጀት ሥራ አልቋል።የመስክ ሥራውን የሚሰራ ቡድንም አጠናቆ መጥቶ መረጃውን የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ነው።ሁለተኛው ቡድን የ42 ፕሮጀክቶችን መረጃዎችን የማደራጀት ሥራ ሰርቶ አጠናቋል።በዞኖች ያለውን ሥራ አጠናቆ ሲመጣ ጉዳት የደረሰባቸውን ፕሮጀክቶችን ብዛትና የንብረት መጠን ማወቅ ይቻላል።መረጃው ተሰብስቦ ሲመጣ የገንዘቡንም መጠን ጭምር ማወቅ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ጉዳት የደረሰባቸው ኢንቨስት መንት ፕሮጀክቶችን የማጣራት ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ምን ለማድረግ ታስቧል ?
አቶ ደምሰው፡- በኢንቨስትመንቶቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ባለሃብቶች አንዱና ዋነኛው መንግሥት ሰላምን በማረጋገጥ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ሥራቸውን የሚጀምሩበትን ሁኔታ የክልሉ መንግሥት እንዲያመቻች ነው ትልቁ ጥያቄ የነበረው። ይህ ጥያቄ ተመልሶላቸዋል። በተወሰኑ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር በአብዛኞቹ ቦታዎች የጸጥታ ችግር ተፈቷል።ቀጥሎ ከጥናት በኋላ የጥናቱን ውጤት ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን።ሪፖርቱን ሰብስበን በገንዘብ ተምነን የባለሃብቱን ጉዳት መጠን ይህን ያህል ነው የሚለውን ግምት እናቀርባለን።ከዚያ በኋላ የክልሉ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ የክልሉ መንግሥት ነው የሚያውቀው።የእኛ ሥራ ሪፖርት ማቅረብ ነው፡፡
የክልሉ መንግሥት አገልግሎት አሰጣጡም ላይ ጉድለት አለ።ባለሃብቱ ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘ ስላልሆነ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የበለጠ ኢንቨስትመንት መሳብ አለበት የሚል አቋም ስላለው ከክልሉ የተለያዩ ሴክተሮች ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ፣ ከርዕሰ መስተዳድር ቢሮ የተውጣጣ አንድ ቡድን አሁን ጥናት እያካሄደ ነው።ታች ያለውን ነገር አይቶ ተመልሷል።
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ ቀምሮ ለማቅረብ ሥራ ላይ ነው።ይህ ሥራ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።ለካቢኔ ይቀርባል።ርዕሰ መስተዳድሩም የማስተካከያ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ተብሎ የጠበቃል።እንደዚህ ሲሆን በነበረው ሁኔታ የተጎዱትም በሥራ ላይ ያሉትም የተሻለ አገልግሎት በማግኘት የተሻለ ኢንቨስትመንት በሀገራችን ይካሄዳል ብለን እናስባለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የክልል ኢንቨስትመንት እያንሰራራ መሆኑን ቢገልጹም፤ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንቨስተሮች ዛሬም ከሥራ ውጪ ስለመሆናቸው መረጃዎች አሉኝ።በክልሉ የነበሩ ኢንቨስተሮች ከሥራ ውጪ ሆነው በተቀመጡበት ኢንቨስትመንት እያንሰራራ ነው ብሎ መናገር ይቻላል?
አቶ ደምሰው፡- በእርግጥ አንተም እንዳልከው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው አንዳንዶቹ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው።ማንሰራራት ያልጀመሩ አንዳንድ ባለሃብቶች እንዳሉ ምንም መካድ አይቻልም።ይህ ሀቅ ነው። ለመስኖ ሥራ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሮ፣ ዘመናዊ መጋዘኖችንና የሠራተኛ መኖሪያን ሰርተው፤ መሰረተ ልማት ካሟሉ በኋላ እንዳልነበረ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች አሉ።ሰው እንዲህ አይነት ጥፋት ይፈጽማል ብለህ ለማመን የሚከብዱ ውድመቶች ተፈጽመዋል።ንብረታቸው የተዘረፉ፣ ኢንቨስትመንቱ ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው አሉ።እነዚህ ባለሃብቶች ለምን በዚህ ወቅት አላንሰራራም ብለህ ብትጠይቀ ትንሽ ይከብዳል።ይህ ጊዜ የሚፈልግ ነው።
ስለነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከፌዴራል መንግሥቱና ከክልል መንግሥታት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።ከፌዴራል መንግሥቱና ከክልሉ እያደረገው ያለውን ውይይት ተከትሎ ሊያንሰራራ ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል።እንደነዚህ አይነት ድርጅቶች መኖራቸውን መርሳት የለብንም።ነገር ግን አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል።የማንሰራራት ሁኔታ አለ።ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ የመምጣት ፍላጎትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ሰሞኑን እንኳ በርካታ ባለሃብቶች ናቸው መጥተው እያነጋገሩን ያሉት።በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። የሀገር ውስጥም እንዲሁ።ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የተሻለ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተያዘው በጀት ዓመት ምን የህል ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ደምሰው፡- በበጀት ዓመቱ የሁለት ነጥብ 52 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው 330 አዳዲስ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እቅድ ተይዟል።ከነዚህ ውስጥ 96ቱ በግብርና ዘርፍ፣ 112ቱ በአገልግሎት ዘርፍ፣ 122ቱ ደግሞ በኢንዱስትሪ ዘርፎች ይሰማራሉ ተብሎ ነው የታሰበው። ኢንቨስትመንቶቹ ለ11ሺህ 262 ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲያውም ይህን እቅድ ስናቅድ የክልሉን መንግሥት አቋም ሳናውቅ ነው ያቀድነው።የክልሉ መንግሥት እቅድ ካቀድን በኋላ ነው ቁርጠኝነቱን የገለጸው። የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ክትትል እያደረገ ስላለ ከ330 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ያስገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ግብ ለማሳካት ምንምቹ ሁኔታ አለ?
አቶ ደምሰው፡- በዚህ ዓመት በጣም ምቹ ሁኔታ ይኖራል ብለን እንጠብቃለን:: የክልሉ መንግሥት ቁጥር አንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ኢንቨስትመንት ነው የሚል አቋም ይዟል። በሀገራችን ሊሰራ የሚችል ሰፊ የሰው ኃይል አለ።ነገር ግን ለዚያ ኃይል የተመቻቸ የሥራ እድል የለም። በዚህም ምክንያት ወጣቱ በሀገራችን አለመረጋጋቶችና ረብሻዎች ምክንያት እየሆነ ነው።ስለዚህ ይህንን ወጣት ወደ ሥራ ማስገባት አለበት የሚል አቋም ስላለውና ከሁሉም የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሁሉ በላይ የሥራ እድል ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የታመነው የግሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። መንግሥት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ በልዩ ሁኔታ የሥራ እድል እፈጥራለሁ የሚል እምነት አለው።
መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቷል።በተግባርም ያሳያቸው ነገሮች አሉ።ለምሳሌ የዓመቱን ሥራ ስንጀምር የመጀመሪያው ኢንቨስትመንት ውስጥ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው ተብሎ፤ የሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ ተወስዶ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ማነቆዎች ተለይተው ለነዚህ መፍትሄ መሰጠት አለበት የሚል አቋም ይዟል።ስለዚህ ማነቆ የሆኑ አሰራሮች ይሻሻላሉ የሚል ግምት ይኖረኛል።እነዚህ ሲሻሻሉ እቅዳችንን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ ይኖራል።የክልሉ መንግሥት በበጀት፣ በፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስ፣ ኢንቨስትመንትን በመገምገምና በመደገፍ ልዩ ትኩረት አድርጎ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ።ስለዚህ የተሻለ የእቅድ አፈጻጸም ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ምን ያህል ኢንቨ ስተሮች ወደ ሥራ ገብተዋል?
አቶ ደምሰው፡- በግብርና 24 አቅደን 11 ገብተዋል።በአገልግሎት 26 ታቅዶ 40 ገብተዋል ፡፡በኢንዱስትሪ 30 ታቅዶ 24 ገብተዋል።በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ 80 አቅደን 73 ወደ ሥራ ገብተዋል።620 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይመዘገባል ብለን አቅደን ወደ 710 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ሥራ ገብተዋል።የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በጀት ድልደላና ሌሎች ሥራዎች የሚሰሩበት ስለሆነ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዝቅ ያለ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በ2010 እና በ2011 በኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሰው ጥቃት ከባድ እንደነበር ገልጸዋል።አሁን ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይደርሱ ጥበቃ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ደምሰው፡- ከጥበቃ ጋር በተያያዘ የጸጥታው ዘርፍ መልስ ቢሰጥብ መልካም ነው።ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ለእኛ የሰጠው የቤት ሥራ አለ።የአካባቢው ህዝብ በኢንቨስትመንት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ያልቻለውና እየተባበረ ያለው ህብረተሰቡ ጋር የግንዛቤ ችግር ስላለ ነው የሚል እሳቤ ተይዟል።ስለዚህ የግንዛቤ ክፍተት መሞላት አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል።ስለዚህ የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን ለመስራት እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው።በጀትም ተይዞለታል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ለጸጥታ ስጋት በሆኖ አካባቢዎች፤ ወይም በርካታ ኢንቨስትመንት ላለባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ ሰጥተን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰራል።ስለዚህ እዚህ አካባቢ አዕምሮ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ጤናማ ከሆነ የጸጥታ ችግር አይፈጠርም። ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት ችግር ባለባቸው ቦታዎች ላይ ጸጥታ እስኪረጋጋ ብሎ ያወጀው ኮማንድ ፖስት አለ።በክልሉም በተለያዩ አካባቢዎች ኮማንድ ፖስት አለ።በተጨማሪም የጸጥታ መዋቅሩም መደበኛ ሥራውን አጠናክሮ እየሰራ ስለሆነ ያ ችግር ይደገማል የሚል እምነት የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2012
መላኩ ኤሮሴ