የፈረንጆቹ 2018 ዓመት የመጨረሻው ቀን ላይ እንገኛለን፡፡ ነገ በሚጠናቀቀው የ2018 አመት ላይ በርካታ ክስተቶች ታዝበናል፡፡ ከዚህም ውስጥ የአሜሪካና የሰሜን ኮርያ ውይይት፣ የሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ውይይት እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ድንገተኛ ግድያ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ከተሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከነዚህ ሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ በ2018 ትልቅ ትኩረት ስባ ቆይታለች፡፡
ቢቢሲ በድረ-ገፁ በዓመቱ ታሪክ የሰሩ አፍሪካውያን እነማናቸው ሲል አንድ ዘገባ ሰርቶ ነበር፡፡ ዘገባው ሰፊ ሽፋን የሰጠው ደግሞ ለኢትዮጵያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነው፡፡ የ42 ዓመቱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር “የአፍሪካ ወጣቱ መሪ” ሲል የገለፃቸው ዘገባው በተለይ ቤተመንግስት ያለፈቃድ ለመግባት የሞከሩ ወታደሮችን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አሰርተው በሰላም መሸኘታቸውን አንስቷል፡፡ በሌሎች ዓለማት እንደዚህ ያለው የወታደሮች እንቅስቃሴ በመንግስት ግልበጣ የሚጠናቀቅ ነበር ያለው ዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሁኔታዎቹን ማረጋጋት የቻሉበት መንገድ አስገራሚ ነው ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ካመጡት ለውጥ በተጨማሪ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሊጠገን አይችልም ተብሎ የነበረውንና ለሁለት አስርተ ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ወደ ሰላም በመቀየር ዓለምን አስደንቀዋል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማስጀመር “ፀሀይን ከምእራብ በኩል እንድትወጣ እንደማድረግ ነው” ሲልም ቢቢሲ የሁኔታውን አይታመኔነት ዘግቧል፡፡ የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰምሮ ድንበሮች ተከፍተው የአየር ትራንስፖትና የስልክ ግንኙነት መጀመራቸው ዓለምን አጀብ አሰኝቷል፡፡
ዓለምን ማስደነቅ በዚህ ያላበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር የካቢኔያቸውን ግማሽ በሴቶች በማደራጀት፣ ቁልፍ የመንግስት ኃላፊነቶችን የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ለሴቶች በመስጠት ታሪክ መስራታቸውን ቀጥለዋል ሲል ቢቢሲ በዘገባው ያሰፈረው በዚሁ አመት ነው፡፡ ወደ ስልጣን ከመጡ ዓመት እንኳን ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት ይከብዳል የተባሉ ጉዳዮችን በማሳካት ተወዳዳሪ የላቸውም ሲል አሞካሽቷቸዋል፡፡ ቀደም ሲል አገሪቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በመረጃ ነፃነትና ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር በነበራት አለመግባባት በርካታ ቅሬታዎች ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ይቀርቡባት እንደነበርም ዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን አንስቶ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በመፍታት፣ በስደት ላይ የነበሩ ተቃዋሚዎችንም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ታግደው የነበሩ ሚድያዎችንና ድረገፆችንም በመክፈት ታሪክ ሰርተዋል፡፡
ሌላው የቢቢሲን ቀልብ የሳበው አፍሪካዊ ክስተት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣናቸው ወርደው በሴሪል ራማፎሳ መተካት ነው፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት በአገራቸው ያመጧቸውን ለውጦችም ዘገባው አካቷል፡፡ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የአፍሪካ አገራትን በአንድ ድምፅ ያስቆጣው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ሌላኛው ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር፡፡ ትራምፕ በንግግራቸው የአፍሪካ አገራትን እንደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች መጥቀሳቸው በወቅቱ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ትችት አሰንዝሮባቸው ነበር፡፡ ባለቤታቸው ሜላኒያ በዚያው ሰሞን በ4 የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት እንዲያደርጉ በማድረግ የደረሰባቸውን ወቀሳ ለማለሳለስ መሞከራቸውም ከአመቱ አይረሴ ታሪኮች መካከል ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 በዓለም ዙሪያ ከ63 በላይ ጋዜጠኞች መገደላቸውን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Sans Frontières – RSF) የተባለው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ይፋ አድርጓል፡፡ አሟሟቱ ያስነሳው ዓለም አቀፍ ውዝግብ አሁንም ድረስ ያልበረደውን ሳዑዲ አረቢያዊውን ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂን ጨምሮ በዚህ ዓመት ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሆን ተብሎ ታስቦ በተፈፀመ ጥቃት እንደተገደሉ የተቋሙ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ተቋሙ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ጋዜጠኞቹ የተገደሉት ሙያዊ ተግባራቸውን እያከናወኑ በነበሩባቸው ጊዜያት ነው፡፡ ከጋዜጠኞቹ በተጨማሪም በሙያቸው ጋዜጠኛ ያልሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ሕይወታቸው እንዳለፈና አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም ከ80 እንደሚበልጥ ገልጿል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት የ15 በመቶ ጭማሬ እንዳሳየና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የተጋረጠ ከባድ አደጋ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አስር ዓመታት በዓለም ዙሪያ የተገደሉት ጋዜጠኞች ቁጥር ከ700 በላይ እንደደረሰም ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ዋነኛውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸጊያ ማዕከሏን በቋሚነት ለመዝጋትና የሚሳይል ሙከራ ጣቢያዎቿን ለማፈራረስ ዝግጁ መሆኗን በመሪዋ ኪም ጆንግ-ኡን በኩል መግለጿ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላም አዲስ ተስፋን እንዲሰንቅ የማድረጉ ዜና የተሰማው በ2018 ላይ ነው፡፡
የሁለቱ ኮሪያዎች መሪዎች በፒዮንግያንግ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው 150ሺ ሰሜን ኮሪያውያን በተገኙበት በ‹‹ሜይ ደይ (May Day)›› ስቴዲየም ባደረጉት ንግግር፣ ውይይታቸው ለቀጠናው ሰላም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተበት አጋጣሚ እንደሆነ ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡
ቀደም ሲል በተደረጉ ውይይቶች የኮሪያ ልሳነ ምድር ከኑክሌር ጦር መሳሪያ የፀዳ ሰላማዊ ቀጠና እንዲሆን ለማድረግ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ-ኢን፣ ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ቀጠናውን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ እንደተሻገሩም ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙን፤ ለአምስት ሺ ዓመታት ያህል አብረን ኖረናል፤ለ70 ዓመታት ደግሞ ተለያይተናል፡፡ አሁን በጋራ የምንኖርበት ጊዜ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሌላኛው በተጠናቀቀው እኤአ 2018 ላይ ትልቅ መነጋገሪያ ዜና የነበረው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ውይይቱ “እምነት የተሞላበት ፣ቀጥተኛና ውጤታማ ነበር” ሲሉ አሞካሽተውታል። በስምምነቱ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የጦር መሳሪያ ፉክክር ለማቆም እንዲሁም ሰሜን ኮሪያም የሚሳይል ሙከራ የምታደርግበትን ክልል ለማጥፋት ቃል ገብተዋል። የኮሪያን ሰርጥ ከኑክሌር መሳሪያ ነፃ ማድረግም በስምምነታቸው ውስጥ ተካቷል። በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በተለይም ዜጎችን በግዞት መልክ የሚደረግን የጉልበት ብዝበዛን አስመልክተው ጉዳዩን ከኪም ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት አንስተዋል።
ኪም የኮሪያን ሰርጥ ከኑክሌር ነፃ ለማድረግ እንደማያመነቱ በንግግራቸው አረጋግጠዋል፤ ይህ ጉዳይ አሜሪካም አጥብቃ ስትሻው የነበረ ጉዳይ ነው። ሁለቱ አገራት ወደፊት ለሚመሰርቱት አዲስ ግንኙነት እንደሚተባበሩና አሜሪካም ለሰሜን ኮሪያ ደህንነት ዋስትና እሰጣለሁ ማለቷ ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የሰሜን ኮሪያው መሪ ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ የሚገኙ ሁለት ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ከአገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፉት እኤአ በ2018 በመጨረሻው ወር ላይ ነው፡፡ ይህ ውሳኔያቸውም አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትን እንዳበሳጨና አንዳንድ የአሜሪካ አጋሮችንም እንዳስደነገጠ ተዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ቡድን በመሸነፉ ወታደሮቹ እንዲወጡ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በበኩላቸው ወታደሮቹን ከሶሪያ የማስወጣት ስራው በመጭው ጥር ወር አጋማሽ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔያቸውን ለቱርኩ አቻቸው ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በስልክ እንደነገሯቸውም ስማቸውን ያልገለፁ የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አገራቸው መመለስ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ከአማካ ሪዎቻቸውና ከአሜሪካ ወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ትንታኔ በተፃራሪ የቆመ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ አሸባሪው እስላማዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስላልከሰመና የሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴም አስተማማኝ በሆነ መልኩ ስላልተገታ ወታደሮቹን ማስወጣት ተገቢ ውሳኔ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ሲናገሩ ነበር፡፡ አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ፕሬዚዳንቱ ስለውሳኔያቸው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
የአሜሪካ ሴናተር እና በአንድ ወቅት እጩ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ማኬን እና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ትልቁ ያረፉት በዚሁ እኤአ 2018 ላይ ነው፡፡ የአሜሪካ ሴናተር እና በአንድ ወቅት እጩ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ማኬን በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ማኬን ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ የአንጎል እጢ ህመም ተገኝቶባቸው ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል። ቤተሰቦቻቸው ማኬን የህክምና ክትትላቸውን በማቆማቸው ህይወታቸው አልፏል።ጆን ማኬን ለስድስት ጊዜ በሴናተርነት ተመርጠው ያገለገሉ ሲሆን፥ በ2008 ፐሬዚዳንታዊ ምርጫም ሪፐብሊካኖችን ወክለው ተወዳድረው ነበር።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ትልቁ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።ጆርጅ ቡሽ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የባለቤታቸውን መሞት ተከትሎ በፓርኪንሰንስ ህመም ምክንያት በፅኑ ታመው በሆስፒታል ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቷል።በዚሁ ህመም ሳቢያም ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ አቅቷቸው፣ በሰው ድጋፍና በተሽከርካሪ ወንበር ታግዘው መንቀሳቀስ ከጀመሩ አመታት አልፏቸዋል።
ሰለሆነም በዚሁ በሽታ በፅኑ በመታመማቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ነው የተገለፀው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1964 ወደ ፖለቲካ የተቀላቀሉት ታላቁ ቡሽ፣ በነዳጅ ንግድ ላይ በመሰማራት በ40 ዓመታቸው ሚሊነር ለመሆን በቅተዋል።ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 1989 እስከ 1993 አሜሪካን የመሩ 41ኛው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ነበሩ።ከባራክ ኦባማ ቀደም ብለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ አባትም ናቸው።
በፈረንጆች 2018 ዓመት ብቻ 2 ሺ 200 ስደተኞች በሜድትራንያን ባህር መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ በዚህ የፈረንጆች ዓመት 113 ሺ ያልተመዘገቡ ስደተኞች ወደ አውሮፓ አገራት መግባታቸውንም ነው የገለጸው፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ሲነፃፀር በ59 ሺ የቀነሰ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር ግን አሁንም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሞቱት 4 ሺ 503 ስደተኞች የሜድትራንያን ባህር የ2 ሺ 200 ስደተኞች ህይወት በመቅጠፍ 50 ከመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የ629 ስደተኞች ህይወት ያለፈበት የሰኔ ወር ከፍተኛ የሞት ቁጥር ያስተናገደ ወር ሆኖ ነው የተመዘገበው ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
መርድ ክፍሉ