ኢትዮጵያችን ለኢትዮጵያነት በብዙ ታላላቅ ገድሎች ውስጥ አልፋለች። ካለፉት 400 ዓመታት ወዲህ እንኳን ያለውን የፀረ ወራሪ ታሪኳን ብናይ፣ ፖርቱጋሎች መጡ በዘዴ ተመለሱ፤ ግብፆች መጡ በተደጋጋሚ ድል ተነሱ ፤ ቱርኮች ወረሩን የሃፍረት ጽዋ ጠጡ፤ ኢጣሊያ ገባች፤ ከአንዴም ሁለቴ ወርራ አፍራ ወጣች…የመጡት ተመ ችቷቸ ው አንድ አስርት ዓመት ያህል እንኳን በአገራችን ምድር አልቆዩም ፤ ይከጅላሉ ፤ ይወርራሉ፤ ይመታሉ፤ ይወጣሉ።
ነገር ግን፣ እርስ በርሳችን ኢትዮጵያን ሳንጠላ ሹመትና መልክዓ-ምድራዊ የበላይነት ወድደን ብዙ ተደካክመናል፤ ይህንንም ታሪካችን ያስገነዝበናል። አሁን ግን የተለየ ሆነ፤ ሰው አገሩን ሳይሆን ዘሩን መረጠ፤ ወንዝ ድንበር ባይኖረውም፣ ወንዙን ሳይሆን ሽንቱን ተጠማ። አመልክቶ ወደዚህ ምድር የመጣ ይመስል በመልክዓ-ምድራዊ ስፋት ወይ በቁጥር ብዛት አለያም በኃይሉ ትምክህት ራሱን ቆለለ። ይህን የተቀበሉ ሞኞች ደግሞ አጨፋፈራቸው ለየቅል ነው፡፡
የሰውን ልጅ አመጣጥ ፈርጅ ትተው፣ ልዩነታችንን ለማስፋት አንዱን የመጣኸው ከውሃ ነው፤” የሚሉት ብሒል ለማን ይጠቅማል፤ ወንዝስ ያሻግራልን? የትኛው ዘር ነው፤ ከአረም የመጣው? የትኛውስ ነው፣ ከሰማይ ዱብ ያለው? የትኛውስ ነው ከአፈር የወጣው? እንዲህስ ማለት ምን ያህል እንደሚያስኬደን እግረ መንገዳቸውን ቢያብራሩልን ምንኛ መልካም ነበር። ይኼስ ነገር (የአንትሮፖሎጂ ተማሪም ባልሆን) የሥነ ፍጥረትንና ሰው የመሆንን ህግ ማፋለስስ አይሆንምን? (If the initial integer is wrong the result won’t be right unless wrongness is right.) እንዲሉ መምህሮቼ።
በዩኒቨርሲቲ መምህርነት፣ በመጣጥፎቹ “ተነባቢነት” እንዲሁም በጥናትና ምርምሩ፣ “ፕሮፌሰርነትን የተቀዳጀ” ሰው እንዴት ፣ የሥነ-ተፈጥሮን የትመጣ፣ ይክዳል? ይህንን እውነት ነው ብሎ መናገርም “የተረት አባት” ያደርግ እንደሆነ እንጂ ጠቢብነት ሲያልፍም አይነካካው፤ አያደርገውም ። እንዲህም እንደሆነ ብንቀበል እንኳን “ያ- ዘር” ኦሮሞ ብቻ ፣ አማራ ብቻ ፣ ጉራጌ ብቻ አይሆንም፤ ሰው ብቻ ነው፤ ሰው ከሆነ እኔን ነው፤ እኔን ከሆነ “እሳቸውን” ነው። እንዲህነቱን ግን ለልዩነት ማሳያ ማድረግ ደግሞ ያሳለፉትን ሁሉ የትምህርት ዘመን በዜሮ ማባዛት ነው።
እኒህ በዕድሜና በቀለም አምባ በመቆየት ያረጁ ታላላቆች ምን ሊያስተምሩን ፈልገው ይሆን? ቀናነት የጎደለው ፤ መረዳታቸውን ከማስረዳት ነጥሎ የሚያቆም ትምህርት የሚደሰኩሩብን። እውነት ነው፤ በዕውቀት ዓምባ ሰው የሚያምንበትን ሃሳብ በምክንያት አስደግፎ የመሞገት ነጻነት እንዳለው ይታወቃል ፤ ይህንን እኔም አምናለሁ። ግን ተጠየቃዊነታቸውን ምን ሰለበውና እምነትን ከእይታና ከቀኖና ነጥለው፣ ፖለቲካ አደረጉት? ሲወርድ ደግሞ ዘር አደረጉት። “ለስንት ያሰብኩት ፈረስ በግ ተራ ፣ ተገኘ”፤ ማለት ይሄኔ ነው።
አንዳንድ ሰው ሲነግሩት ብቻ ሳይሆን ሲናገርም የራሱ ነገር ለራሱ አይገባውም ይባላል ። የጀመረውን በቅጡ አይጨርስም ፤ ንግግሩ አንድነት የለውም ፤ የሐሳብ ፍስሰት የለውም፤ እርስ በእርሱ አይደጋገፍም። ስለዚህ ሲናገር ከማስረዳት ይልቅ እንኳን ከሌለ ቅድም-አያቱ ይበደርለትና ይኼኛውን ትውልድ ይከስሰዋል፤ ያፈናቅለዋል፤ በዚህ ቢያቆም መልካም ነበር፤ ይኸው አልበቃ ብሎት ደሙን በጭካኔ ያፈሰዋል ። በዚህም የክፉ ሃሳቡን ልክነት ለማረጋገጥ ይዳክራል። የዚህነቱን ልክነት እንዴት ያረጋግጥልን ይሆን፤ ይህንን ነገር ራሱስ አምኖበት ይሆን ያደረገው ወይስ በደመ-ነፍስ የተከናወነ ድርጊት ይሆን?
ከእነዚህ ታላላቅ “አዋቂዎች” የምን ጠብቀው ትልቅ እውቀትና ማሰባሰብን እንጂ በታኝና ከሳሽ የሆኑ ትውልድ አሳናሽ ትርክቶችን አይደለም ። ለእኔ ኦሮሞ የሆነ የሐገሬ ሰው፤ ለሰው ሳይሆን በቤቱ ለሚያልፍ የቀን ይሁን የሌት አውሬ /እንስሳ ጠጥቶት እንዲያልፍ ወተት ከደጃፉ የሚያስቀምጥ የዋህና ቀና ህዝብ እንጂ ሰውን ያህል የከበረ ብጤውን በጠራራ ፀሐይ የሚገድል አይደለም ፤ ስለዚህ በኦሮሞው ወንድም ሥም ቋንቋውን የምትናገሩ ክፉዎች ስሙን አታጠልሹት።
ለእኔ አማራ የተባለ በእርግጥም አማርኛ ተናጋሪው ህዝብ በሞቴ ብሎ የሚበላውን ከእጁ ለአላፊ አግዳሚው የሚያቋድስ “እህልን ከሰው ካልበሉት አውሬነት ነው፤” የሚልና ለእንግዳ መደቡን ትቶ እርሱ “ላምነት” ላይ የሚተኛ ቀና ህዝብ ነውና ጨካኝ የሰው ባህል አስነዋሪ፣ ማንነት ደፋሪ ፤ የራሱን ጫኝ፣ የሰው አባካኝ አድርጋችሁ አትንገሩኝ። ይህንን ህዝብ፣ ይህንን የአማራ ሰው ከአዲሳባ ወጣ ብላችሁ ደብረ-ብርሃንና ደብረ-ሲና ፣ ላይ ሳይተርፈው አጉርሶ ሳይሞቀው አልብሶ ሲያሳድር ማየትና ለእግሩ ጫማ ሲናፍቀው አለና፣ ወጥታችሁ እዩልኝ ።
ሲዳማውን መጤ-ጠል (Zenophobic) ለማድረግ በስሙ ሰው ገድላችሁ ሜዳ ላይ ጥላችሁ፤ ጨካኝ ነው፤ የምትሉኝ ሰዎች እኔ የማውቀው ሲዳማ፣ ውሃ ፣ ለጠማው ወተት የሚያጠጣ ፣ ለመሸበት ቢያጣ ቢያጣ ሐሹባውን (ከደረቀ የኮባ ቅጠል የተዘጋጀ ርብራብ ነው) ጎዝጉዞ ጨርቅ ጥሎ የሚያስተኛ ልበ-ርህሩህ ህዝብ መሆኑን ነው። ሲዳማውን አትንኩብኝ ፤ ኦሮሞውን አታሳንሱብኝ ፣ አማራውን ግፈኛ አታድርጉብኝ፤ ማንኛውንም የኢትዮጵያ ሰው እንደ ዜጋ አንዱ በሌላው ላይ ቂም የሚይዝ፣ አጉራ ዘለልና ጨካኝ አድርጋችሁ አትሳሉብኝ ።
ባሳለፍኩት አጭር የሚባል እድሜ አሁን ካልኳቸው ልዩ ልዩ ኢትዮጵያውያን ዜጎቼና ወገኖቼ ጋር አብሬ ኖሪያለሁ፤ ከፊሎቹ አሳድገውኛል፤ አንዳንዶቹ የሥራ አጋሮቼ ሌሎቹ ደግሞ የአምልኮ ቤተኞቼ ሆነው አውቃቸዋለሁ። የአብዛኞቹ ባህሪ ያስተማረኝ ግን ሰሞኑን የታየውን ጭካኔ አይደለም ፤ በዚህ መልካቸውም አላውቃቸውም ።
ይሁንናም ውጣ ውረዳችንን ለመመዝገብ፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ፣ ካሴት ናት። እየሆነ ያለውንና እየተደረገባት ያለውን ሁሉ እየቀረጸች ነው። ነገ ታሪክና ትውልድ በጥፋታችን የሚያየውንና የሚመዝነውን፣ የሚያቀልልና የሚያከብረውን በሥርዓት እየመዘገበች ነው። ስለዚህ ሁላችንም በዚህ የታሪክ ህትመት ውስጥ ተቀርፀን ማለፋችንን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም ።
የገረመኝን ነገር ግን ሳላነሳ ብቀር ነገሬን ሙሉ አያደርገውም፤ እነዚያ ታላላቆቼ ያልኳቸው ከዓለም አቀፍና ከሐገር አቀፍ ዩኒቨርሲቲ ዶክቶራልና ፖስት ዶክቶራል ዲግሪ የወሰዱ “የቀለም ጉምቱዎች”- የዕድሜ “ባለጠጎች” ፤ ከሐገሬ ድግር ጨባጭ ባላገርና አርሷአደር (ብዙው ያልተማረ ነው፤ ተብሎ ይታሰባልና ) ከሚያስበው ሩቅ አሳቢነትና ፍቅር ያነሰ ውዴታና በጥላቻ እውቀት የጨቀየ ማንነት ስላሳዩኝ፣ ያሳዘነኝን ያክል እንኳንስ ኦሮሞና ጉራጌ፣ ስልጤና ወላይታ ፣ ሲዳማና ኮሬ ሊለይባቸው በቤቱ (በቤተ -እምነቱ) ወንድም ሴትም የለም፤ ሁሉም አንድ ናቸው፤ ከሚባልበት የክርስትና ህይወት የወጡ ወንድሞቼ የወገንተኛነት ቀሚስ አጥልቀው፣ የዘር ጋቢ አጣፍተው ፣ የጥላቻ ቡልኮ ደርበው፣ ከጸቡ ውስጥ ገብተው ዱላ ሲያቀብሉ ሳያቸው ፣ እጅግ አዝኛለሁ።
ከዚህ ቀደም ብየዋለሁ፤ አሁንም እደግመዋለሁ፤ እናንት፣ በእምነት የመስቀሉ ተከታዮች ፣ በፖለቲካው የክርስቶስ ተቃዋሚ ወታደሮች፣ የቤተ እምነቱ ቁማርተኞች፤ ህሊናችሁን ከክፋት ጥንስስ፣ አንደበታችሁን ከጥላቻ መርዝ፣ እጃችሁን ደም ከማፍሰስና ከማስፈሰስ አሁን ካላስቆማችሁት አበሣችን እየቀጠለ ውድመቱ እየገዘፈ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ይህ አካሄዳችሁ፣ ፍጻሜያችሁን በምድርም በሰማይም፣ እንደሚያበላሸው ለመናገር ነብይ መሆን አያስፈልግም ።
እርሱ ከዘርም ከቋንቋም ከነገድም ፤ ከወገን ጠርቼ የእኔ ካህናት አድርጌያችኋለሁ አለ እንጂ፤ የዘር ግድግዳ አጥር አናፂዎች፣ ጨፈቃ አቀባዮች እንድትሆኑ ሾሜያችኋለሁ እንዳላላችሁ ግልጽ ነው ። ልጆቻችሁ ነገ፣ የሚያፍሩበትን ነውር ዛሬ አትፈጽሙ፤ አታስፈጽሙ። ሙስሊም ወንድሞቻችን “ሳይሰገድብህ ስገድ”፤ ይላሉ። ትውልድ ሳያፍርባችሁ እራሳችሁ እፈሩና አቁሙ!!
ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከክፉ የሚጠብቅ፣ ልዕልናዋን በእኩልነት ለማሳደግ የሚተጋ ሰው ወደ መንበሩ ሲመጣ ያዩ ምንዱባን ሲደሰቱ፣ የህዝቡ ደስታ ደስታቸው ያልሆነ፣ በልዩነቱ ውስጥ ጆሮ ቆርቋሪ ፀብ ማምጣት የፈለጉ፣ የቆርቆሮ ድቤ መምታት የሚያስደስታቸው ወገኖች ከየጎሬያቸው በመውጣት የብዙ ጎጆዎችን ጣራ ሲያፈርሱ፣ የንግድ ማእከሎችን ሲያጋዩ፣ በሰው ስቃይ ጮቤ ሲረግጡ ታይተዋል። ይህ በምንም መለኪያ ጤነኛ አካሄድ አይደለም ። በደረስኩበት እውቀት ይህን የአእምሮ ሁከት (Mental disorder) ብዬዋለሁ።
ቀደም ባሉት ንግግሮቼ ወቅት፣ ስለ ሃብታም አገርና ሃብታም ህዝብ አንስቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። አገሪቱ ደሃ ህዝብ ይዛ ሃብታም አገር እንደማትሆን ሁሉ፤ ራሷም ደሃ ሆና ሃብታም ክልሎች አይኖሯትም። አንዳንዶች የመልክዓ ምድራቸውን ስፋትና የህዝብ ቁጥራቸውን ብዛት በማየት እኛ ለራሳችን በቂ ነን፤ ሌላው ከተወገደልን ሃብታም እንሆናለን ብለው ይደሰኩራሉ፤ አንዳንዶች ሃይል ስላለን ማንም አይችለንም ብለው ይኩራራሉ፤ እውነት እንነጋገር ከተባለ የአንዱ ኢትጵያዊ ሃብታምነት በሌላው ድህነት ላይ ከቆመ ዘለቄታ የሌለውን ያክል ብቻውን የተነጠለ ሀብታምነት ኖሮት ሌላውን አደህይቼና አንገላትቼ እኖራለሁ የሚል “ክልልም” አይኖርም።
የአንዳችን እጣ ከሌላኛችን ጋር በእጅጉ ተሳስሯል፤ የአንዳችን እድገት ከሌላኛችን ስባት ጋር በእጅጉ ተቆራኝቷል። እንኳንስ እኛ ኢትዮጵያውያን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እጣ ፈንታ እርስ በእርስ የተሳሰረ ነው። በመለያየታችን እንኮሰምናለን እንጂ አናተርፍም ፤ በመለያየታችን እንጫጫለን እንጂ አንዳንድ ሐሳበ-ገልቱዎች እንደሚሉት አንዳችንን ትቶ አንዳችን አያበለጽገንም ። ሰው እኮ አንዱ ከሌላው ጋር የተዋደደ፣ እርስ በእርሱ የተሸመነ ጥበብ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ነጻነታችን ሊያጠፋን ካልዳዳው በስተቀር የታሪካችን ግምድ በመነጣጠል የሚያምርበት አይደለም ። በፊትም አልነበረምና!
እኛ ፣ ስንደመር ስንያያዝ እንጂ ስንቀናነስ አያምርብንምና። በመደመር የምናጣው ማንነት ካለ ውሉን እየለያችሁ አስተምሩን፤ በመተባበር የሚቀርብንን ብልሃት ንገሩን፤ ምከሩን። በእኔ “ዶክተር ባልሆንኩት” ብላቴና እይታ እንዲህ አያለሁ። በእኔ በዮናታን ገጽ ላይ የደሚቱ እጆች ሙያ ውጤት የሆነው ጨጨብሳ ይንፀባረቃል፤ በጋምቤላው ኦማት፤ ልብ ውስጥ የሐረሪዋ ዘይነብ ሙሸበክ ውል ይላል፤ በከሌቻ ዓይኖች ላይ የወላይታዋ ዓይነቴ ሙሶ ይሯሯጣል፤ በጴጥሮስ እጆች ላይ የኤርጎጌ አታካና ለጉርሻ ተዘጋጅቷል፤ የትርሐስ ጣፋጭ አንባሻ በሸዌው ጋዲሴ ነጭ- ጠላ ይሻመዳል፤ በሙዘይን ደምስር ውስጥ የዳንቺሌ ቡርሳሜ እየሰረገ ነው ወዘተ…።
እኛ፣ በምንበላው፣ በምንጠጣው፣ በምንለብሰው፣ በምናከብረው፣ በምንጮኸው፣ በዝማሬያችን፣ በዘፈናችን ፣ በሙሾ ድርደራችንና ረገዳችን ውስጥ ተወራራሾች ነን ፤ ልክ እንደቀልቀሎ ስልቻ ፣ ስልቻ ቀልቀሎ ነው!! …. ምናልባት – ምናልባት አሮስቶውንም ገዝተህ ፣ ላዛኛውንም አዝዘህ መብላት ትችላለህና ይሄ አተራረክህ አይሰራም ብለህ የምትሞግተኝ ካለህ፣ በአሮስቶውና ላዛኛው ውስጥ “ንግድና ትርፍ” ሲኖር በጨጨብሳውና በቡርሳሜው ፣ በዶሮ ወጡ ውስጥ የእኔነት ፍቅር ተጨምሮበታልና ሁለቱ አይወዳደሩም።
የ60ዎቹ ዓመተ ምህረት ፖለቲከኞቻችንና ”ታላላቆቻችን” አካሄድ በእኔ አረዳድ የትም አያደርስንም፤ ከኦሮምኛ አንድ ተረት በአማርኛ ልበል (ድሮም ስንዋዋስና ስንደመር ነው፤ የሚያምርብንና የምንበለፅገው) “ ካጎነባበስህ የት ጋ፣ እንደምትመታኝ አውቂያለሁ” ይላሉ፤ አበው ኦሮሙማዎች። በዚህ አገባብ የእኛ ታላላቆች ከአነጋገራቸውና አካሄዳቸው፣ ለእነርሱ ብቻ የምትስማማ አገር ሳይሆን ክልል፣ ክልልም ብቻ ሳይሆን ጎጥ ለማንገስ፤ የሚያስችል ስልት እየፈጠሩ ነው፤ ግን አይሰራም፤ ምነው ካላችሁኝ የብሄር ነገር ብሄሩ ላይ ሳይቆም ሲቀር ያለፈው የአኗኗርና አስተዳደር ተመክሯችን አሳይቶናልና ።
የወለጋው ልጅ ሸዋ መጥቶ እንዲያስተዳድር፣ የጅማው አርሲ ሄዶ እንዲመራ፣ የባሌው ቦረና እንዲገዛ አይፈቅድም፤ የባሌው ለባሌ፤ የአርሲው ለአርሲ፣ የወለጋው ለወለጋና ሌላውም እንዲሁ ነው። በመዋቅር ደረጃም ሲሰራበት የቆየው ይኸው ነው። ከዚህም ሌላ የመንዲ ልጅ ደምቢ ዶሎ አይታሰብም ፤ የኤጄርሳው ኮፈሌ አይመጣም፤ ይህ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት የታየ ክፉ “ጦስ” ነው። ይህንን ማቆም ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉት “ታላላቆች” በተከበረው አካዳሚያዊው መስክ ላይ መጥተው ወደፊት የማያራምድ፤ ባለህበት እርገጥ የሆነ ምናልባትም ወደኋላ የሚያስኬድ የተዛነፈ ትርክት እያሰሙን ነው።
ይኼ እንዳይሆን ሀገራዊ ራዕይ ይቀረጽ ሲባሉ፣ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ይላሉ። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያለነውን ሰዎች ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን “የመሳፍንታዊው አስተሳሰብ” ሊመሩን ለምን ፈለጉ፤ ስንል ለምናነሳው ጥያቄ የሚሰጡን መልስ ውሃ የማያነሳ ነው። ነጻነት፣ እና ዕውቀት ህብረትንና አንድነትን ከናደ ባይማሩትስ !! ነጻነታችንን በቅጡ እንደመጠቀም ያለ ብልህነት የለምና ። ታላላቆች ሆይ! የሚበጀውንና የሚያሻግረንን በእውነትና በፍቅር ንገሩን፤ አስተምሩን፤ ካለዚያ ፍቅርንና አንድነትን ከዚህም የሚመነጨውን ጣፋጭ ኃይል ፣ ዝቅ ብላችሁ ለመማር ተዘጋጁ፤ ይልቅስ ለሰላም አብረን እንትጋ።
እኔ የምትታየኝ ኢትዮጵያ፣ ከድንግዝግዝ ውስጥ ዘርፋማ ቀሚሷ እየተዘናፈለ ወደላቀ ብርሃን የምትወጣ ባለግርማ እናት ሆና ስትሔድ ነው። ይህን ድንግርግር ያለ እና ድንግዝግዝ ብርሃን ያለጥርጥር እናልፈዋለን እንጂ፣ በክፋት ትርክት ተውጣ ፣ አትቀርም፤ እኛም አንቀርም ። ስለ ሐገሬ ኢትዮጵያም መናገሬን የማቆመው እስትንፋሴ ሲቆም ብቻ ነው!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር ፣ ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ