በርካታ ባለሃብቶች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርናው ዘርፉ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፤ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚጠበቅባቸውን ያህል አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው ለማለት አያስደፍርም።ክልሉ በተለይም ማንጎ እና ቀርከሃ በማምረት ቢታወቅም፤ ማንጎም በበሽታ በመጠቃቱ አርሶ አደሩን በሚገባው ልክ እየጠቀመ አይደለም።እነዚህንና ባለፈው ዓመት በክልሉ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር የፈጠረውን የምርት እጥረት የማካካስ ስራው ምን እንደሚመስል ከክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፤ ባለፈው አመት የነበረው የግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሳ፤ የግብርና እንቅስቃሴ የ2010/11 ዓ.ም የመኸር እርሻ ምርት 70 በመቶ በላይ ተሳክቷል።አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፍን አቅደን 800 ሺ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ተችሏል።34 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ታቅዶ 22 ሚሊዮን ኩንታል ተገኝቷል።አርሶ አደሩ የሰብል ምርት ምግብ ፍጆታውን መሸፈን ችሏል።መስኖ ላይ የተመዘገበው ግን ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው።የታቀደው 109 ሺ ሄክታር ለመሸፈን ነበር።መሸፈን የተቻለው ግን 33 ሺ ሄክታር ነው።
በእንስሳት ዘርፉ እንስሳት ህክምና ለመስጠት ካሰብነው መካከል 80 በመቶ አሳክተናል።ሆኖም በዘርፉ የእንስሳት መድሃኒት እጥረት አጋጥሞ ነበረ።እርባታው ላይም በተለይ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብና በአሳ እርባታ ጥሩ አፈጻም ቢመዘገብም፤ በእርባታው በኩል ክልላችን ካለው ሃብት አኳያ እድገቱ በጣም አዝጋሚ ነው።ምክንያቱ ደግሞ የማህበረሰቡ የእንስሳት አረባብ ዘዴ ኋላ ቀር መሆን ነው።በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ ያለው የገንዲ በሽታም አርሶ አደሩ ላይ ስጋት በማሳደር እንዳያረባ አድርጎታል።በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አገልግሎት በሚፈለግባቸው ልክ በማቅረብ በኩል ውስንነት አለ።በመሆኑም እንስሳት እርባታ ላይ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ የግብርናው ዘርፍ ነው።
የተፈጥሮ ሃብትን ማልማት ውስጥ ከሚካተተው መካከልም የደን ልማት አንዱ ነው።ባለፈው ዓመት እቅዳችን የነበረውም 41 ሚሊዮን ችግኝ አፍልተን በክረምቱ ለመትከል ነበር።የፈላው 38 ሚሊዮን ችግኝ ነው።በተፋሰስ ዘርፍ 39 ሺ ሄክታር መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለመስራት ታቅዶ የተከናወነው 24 ሺ ሄክታር ነው።አፈጻጸሙ እንደ መስኖ ስራው ዝቅተኛ ነው።ከተለመዱት ችግሮች ባሻገር የጸጥታ ችግር በአፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በክልላችን ጥቅጥቅ ደን አለ።ግን በተለያየ መንገድ እየወደመ ነው።አንዳንድ ባለሃብቶች ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ወደ እርሻ ሲገቡ የሚወድም ደን ቀላል አይደለም።አርሶ አደሩ ካለበት ባህላዊ አኗኗር ዘዴ ደን ላይ ጥገኛ አድርጎታል።ደን ቆርጦ ለማገዶ የመጠቀም፣ ለገበያ የማቅረብ ሁኔታ ይስተዋላል።ይህንን ለማካካስ ችግኝ በማፍላት በመንግስት እየተተገበሩ ያሉ ስራዎች አሉ።በመሆኑም ግንዛቤ ፈጠራ በስፋት መሰራት አለበት።የሚተላለፉ የእርሻ መሬቶች የደንን ጉዳይ ማዕከል በማድረግ መሆን አለበት።ደን የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑ በአመራር ደረጃ ጭምር የግንዛቤ ችግር አለ።ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖርም ባለው ልክ የህብረተሰቡን ኑሮ አልቀየረም።
በክልሉ ሰፊ የቀርከሃ ሃብትም አለ።400 ሺ ሄክታር ይሸፍናል ተብሎ ይታሰባል።ሃብቱን ወደ ገቢ ቀይሮ ህዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ገና አልተሰራም ማለት ይቻላል።ቀርከሃ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል።ህዝቡ ከለመደው ባህላዊ አጠቃቀም አልተላቀቀም።ትኩረት የሚሻ ነው።
በዘንድሮ ክረምት በዘር ለመሸፈን ያቀድነው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ነው።እስካሁን ባለው አፈጻጸምም 860 ሺ ሄክታር በዘር ተሸፍኗል።አፈጻጸሙም 75 በመቶ ነው።ከዚህም 78 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ አቅደናል።ይህ ቶሎ የሚደርሱ እንደ ሽንብራ ያሉትን ሰብሎች አያካትትም።በዚህ አተገባበር ያለፈውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማካካስ እንችላለን።
ግን አሁንም ስጋት አለ።በተለይም በመተከል ዞን አካባቢ ዘር በሚጀመርበት ወቅት የተፈጠረ የጸጥታ ችግር ስራውን አስተጓጉሎታል።አብዛኞቹ ባለሃብቶች ወደ እርሻ ስራ በጊዜ ስላልገቡ ባለሃብቶች ሊያመርቱት የሚገባው ምርት አልተመረተም።ይህ አካባቢ ከክልሉ አጠቃላይ ምርት 50 በመቶ የሚመረትበት ነው።አጋጣሚ ችግሩ የተፈጠረበት ዳንጉር ወረዳ ሰፊ የእርሻ ሃብት አለ።ሰው ለቅቆ ስለወጣና እርሻ በጊዜ አለመታረሱ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።ይህንን ለማካካስ ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተቀናጀ መንገድ የመስኖ እርሻ ስራ ተጀምሯል።በዚህም 67 ሺ ሄክታር መሬት ይታረሳል።የመስኖ ምርታማነትን በመጨመር ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማግኘት አቅደናል።
ባለሃብቶች እንዲመለሱ ከባለፈው ክረምት ጀምሮ ጥረት ተደርጓል። መተከል አካባቢ ፈጥኖ ስላልተረጋጋ አብዛኞቹ ባለሃብቶች በጊዜው አልተመለሱም።ከተመለሱ በኋላ መዘራት የነበረባቸው ሰብሎች መዘራት ያለበት ጊዜ በማለፉ የተፈጠረ ክፍተት አለ።ውሃ ገብ በሆኑ መሬቶች ባለሃብቶች ጭምር እንዲያለሙ ማድረግ ካልተቻለ የባለፈው ዘመን ምርት በሚፈለገው መጠን ላይካካስ ይችላል።በመሆኑም መስኖ ስራ በዚህ ዓመት ለክልላችን የሞት የሽረት ጉዳይ ነው።በመስኖ ሁለት ጊዜ አንዴ ደግሞ በመኸር ማምረት ካልተቻለ ምርት በገቢያችንና በምግብ ፍጆታ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።
አዲስ ዘመን፤ ባለሃብቶችን ወደእርሻ ስራቸው ለመመለስ በተገቢው መንገድ ተተግብሯል ማለት ይቻላል?
አቶ ሙሳ፤ ባለሃብቶች ሙሉ ለሙሉ አልወጡም።የወጡትን የመመለስ ስራም ተሰርቷል።በዘር ጊዜ የወጡት መተከል ላይ ዳንጉርና ማንዱር ወረዳ ላይ ያሉ ናቸው።ኮማንድ ፖስቱን አይተው እና መረጋጋቱንም በመመልከት ራሳቸው ወደ ስራቸው ተመልሰዋል።አብዛኞቹ ተመልሰዋል።ግን የሚቀሩ አሉ።
አዲስ ዘመን፤ የ2011 ዓ.ም የመስኖ አፈጻጸም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው
አቶ ሙሳ፤ የ2011 ዓ.ም የመስኖ አፈጻጸምን አነስተኛ ያደረገው አለመረጋጋቱ ነው።በእዚህ ክልል የጸጥታ ችግር የጀመረው ሰኔ ወር አካባቢ ነው።በተወሰነ ደረጃ መኸር ምርት ላይ የፈጠረው ችግርም ነበረ።ችግሩ በመስከረም ወርም ተቀጣጥሎ በመቀጠሉ የመስኖ እርሻን ማካሄድ አልተቻለም።በእዚህ ምክንያትም ወደስድስት ወረዳዎች የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ አልነበረም።በአመራር ደረጃም ትኩረት ተደርጎ የነበረው ጸጥታን ማረጋጋት፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ አካባቢው የመመለስና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማስፈን ላይ ነበረ።
ከእዚህ በተጨማሪ ግን እድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢሆንም አዝጋሚ ነው።ምክንያቱ በተለይ የመስኖ ስራ ማህበረሰቡ ጋር እንደባህል አድርጎ የማልማት ጉዳይ ገና ምክንያቱ ደግሞ፤ ባመረቱት ልክ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ፣ አመራሩና ባለሙያው በበቂ ሁኔታ ድጋፍ ባለማድረጋቸው ነው።
አዲስ ዘመን፤ የእንስሳት ዘርፍ ካለበት ችግር እንዲወጣ ምን እየተተገበረ ነው?
አቶ ሙሳ፤ የገንዲ በሽታ በተለይም ወደ ሰባት ወረዳዎች ላይ ችግሩ ይበዛል።ከበሽታው ለመላቀቅ የተጀመሩ ስራዎች አሉ።በአንድ በኩል በፌዴራል ደረጃ የገንዲ በሽታ የቆላ ዝንብ መከላከያ ተቋቁሟል።ጥሩ አስተዋጽኦም እያበረከተ ነው።የክልሉ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው።አንዳንድ አካባቢዎች የመድሃኒት ርጭት የተከናወነባቸው አካባቢዎች ችግሩ ቀንሷል።ለገንዲና ለሌሎች የእንስሳት በሽታዎች በቅርቡ ክትባት ይሰጣል።በተሰጠን ዕድል በቅርቡ ለስልጠና ባለሙያ ወደ ኬንያ ልከናል።ዘንድሮ እርባታ ላይ ትኩረት ሰጥተናል።እንደአገርም በተለይ እንስሳት ላይ የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ነው።ግን የተጀመሩ ትግበራዎችና ድጋፍና ክትትል ተጠናክረው ከቀጠሉ ከችግሩ መውጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፤ በዘርፉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምን ይመስላል?
አቶ ሙሳ፤ በማህበረሰቡ ደረጃ የመጠቀም ፍላጎት አለ።ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ በአርሶ አደሩ ዘንድ ችግር ነበረ።አሁን ግን ግንዛቤውም ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው።የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል። ትልቅ ችግር የሆነው አቅርቦት ላይ ነው።የማዳበሪያ አቅርቦት ቢሻሻልም የዋጋ መወደድና የምርጥ ዘር አቅርቦት መዘግየትን አርሶ አደሩ እንደችግር ያነሳል።ይህ ትክክል ቅሬታ ነው።ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የሚዘገየው ከውጭ ስለሚገባ ነው።ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ቴክኖሎጂዎች አገር ውስጥ መመረት ካልተቻሉ በምንዛሬ ከውጭ የሚገቡበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፤ በግብርናው ዘርፉ በ2011 ዓ.ም የተፈጠረ የስራ ዕድል ምን ያህል ነው?
አቶ ሙሳ፤ ባለፈው ዓመት በቡድን፣ በማህበርና በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ለአራት ሺ 800 ወጣቶች የስራ ዕድል ተጥሯል።ዘንድሮ ወደ ስድስት ሺ 500 የስራ ዕድል በተለይም በእንስሳት፣ በመስኖ እና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለመስራት አቅደናል።
አዲስ ዘመን፤ የማንጎ በሽታ ከገጠመው በሽታ ለማላቀቅ ከወሬ በዘለለ ምን አይነት ትግበራ ታቅዷል?
አቶ ሙሳ፤ ማንጎም የክልሉ አርሶ አደር ለምግብ ፍጆታ የሚጠቀምበትና የገቢ ምንጩም ነው።የተከሰተው የማንጎ በሽታ ምርቱን ቀንሶታል።ከበሽታው መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተጀመሩ ስራዎች አሉ ግን የማንጎ በሽታን ለመከላከል የሚሰራው ስራም አመርቂ አይደለም፣ የተከሰተውን መጤ በሽታም ማዳን አልተቻለም ብሎ መውሰድ ይቻላል።አፈጻጸሙ በሁሉም ዘርፍ ተደምሮ በመካከለኛ ደረጃ ይቀመጣል።
ለመከላከል ትግበራው የተለያዩ አካላትን ቅንጅት ይጠይቃል።በሽታው በንፋስ የሚተላለፍ በመሆኑ የተቀናጀ ትግበራ ያስፈልገዋል።አበቃቀሉ የተለያየ ቦታ ስለሆነ ችግሩን ለመከላከል አስቸጋሪ ነው።በባህላዊ መንገድ የሚመረት በመሆኑም ቁመታቸው ረጃጅም ነው።በዘመናዊ መንገድ የበቀሉና አጫጭር ቢሆኑ ኖሮ በርጭት ለመከላከል ይቻል ነበር።አገር ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችም ምላሻቸው ደካማ ነው።በተለይ ሰብል ላይ የሚመራመሩ ተቋማት ትኩረት አልሰጡትም።ለትግበራ የተቀመጠ አቅጣጫ አለን።
በበሽታው የተጠቁትን ማንጎዎች ግንድ እየቆረጥን ወደሌላው እንዳይተላለፍ ለመስራት ታቅዷል።በኬሚካል ርጭት ለማድረግ ተጽእኖውን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ውይይት ለማድረግ አቅደናል።በአንድ ክልል አቅም ብቻ ችግሩ አይፈታም።በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል።በተለይም ግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርናና እርሻ ምርምር ማዕከላት፣ ቋሚና አመታዊ ሰብሎች ላይ ከሚመራመሩ ተቋማት መፍትሄ እንፈልጋለን።እስካሁን የተደረጉ ሙከራዎችም ያን ያህል ውጤት አላስገኙም።
አዲስ ዘመን፤ የክልል ግብርና ባግባቡ ከተሰራበት ለአገር ኢኮኖሚ ምን አይነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ?
አቶ ሙሳ፤ በአብዛኛው ለም የሆነ ሰፊ መሬት አለ።በክልል ደረጃ ጥቅም ላይ ከዋለ በአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።በክልሉ የተሰማሩ 528 ባለሃብቶች መካከል ግማሾቹ በትክክል ስራ ውስጥ ቢገቡ ከአገር ፍጆታ ተርፈው ወደ ውጭ አገር መላክ የሚቻል ምርት ይገኛል።ስለዚህ ሃላፊነት በተሞላበት፣ ባግባቡና በብልሃት የሚለማ ከሆነ በሰፋፊ እና በአነስተኛ አርሶ አደሮች ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፤ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ሙሳ፤ እኔም አመሰግናሁ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት24/2012
ዘላለም ግዛው