በበጀት አመቱ ከመንግስት ዋና ዋና የልማት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ንጹህ የመጠጥ ውሀን ተደራሽነት ማስፋፋት አንዱ እንደሆነ ተቀምጧል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርም የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማስፈጸም ዝግጅት አጠናቋል። በቅርቡም ፕሮጀክቶቹ የሚጀምሩ ሲሆን፤ በአጠቃላይም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደሚሰራ ተገልጿል።
በሚኒስቴሩ የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮምሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ እንደሚገልጹት፤ በአሁኑ ወቅት እንደሀገር ያለው የውሃ አቅርቦት 75 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ደርሷል። አቅርቦቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በገጠርና በከተማ ተብሎ በመጠን የተለያየ ነው። በገጠር በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ 25 ሊትር፤ ለአንድ ቀን፤ ለአንድ ሰው ለማዳረስ፤ እንዲሁም በከተማ በአጭር ርቀት ቢቻል በግቢ ውስጥ እንደየከተሞቹ እድገትና ልዩነት ከ40 እስከመቶ ሊትር ማዳረስን ታሳቢ በማድረግ ነው።
በዚህ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት የገጠሩን 78 ነጥብ ሰባት በመቶ ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የከተማው ስድሳ አምስት ነጥብ አምስት በመቶ ደርሷል። የከተማው ዝቅ ያለበት ምክንያት እቅዱ ሲቀየስ ትልልቆቹ ከተሞች ያገኙ የነበረው ከሀያ እስከ ሰላሳ ሊትር ብቻ በመሆኑ በአዲሱ መስፈርት እነዚህ ሁሉ እንደተጠቃሚ መቆጠር ስላማይችሉ እንደአዲስ በመያዛቸው ነበር። የገጠሩ ግን በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 15 ሊትር የነበረው በሁለተኛው ወደሀያ አምስት ቢከለስም ሰፊ ክፍተት አልነበረውም። በከተማ ያለው ሽፋን ስድሳ አምስት በመቶ ደርሷል ማለት ግን 35 በመቶ ህዝብ ውሃ አያገኝም ማለት ሳይሆን የተቀመጠውን ደረጃ የማያሟላ የውሃ አቅርቦት አለ ማለት ነው።
በሀገሪቱ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ የሚከናወኑት በዋን ዋሽ ፕሮግራም ስር ነው። ዋን ዋሽ ፕሮግራም እንደ እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ሁሉም ከውሃ አቅርቦት ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ አካላቶች ተቀናጅተው መስራት አለባቸው በሚል እሳቤ ዋሽ ኢንፕሊመንቴሽን ፍሬም ወርክ አዘጋጅቶ እየተገበረ ይገኛል። በዚህም ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ጤና ሚኒስቴር፤ ትምህርት ሚኒቴር፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብርና ሌሎችም በጋራ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በአንድ እቅድ ከተማከለ አንድ በጀት አንድ ሪፖርት በመያዝ በአንድነት እየሰሩ ይገኛሉ።
ይሄ እንዳለ ሆኖ፤ በከተማ ውሃ አቅርቦት በኩል እንደአዲስ አበባ፤ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ አዋሳ ያሉ ትልልቅ ከተሞች አይካተቱም። ምክንያቱም፤ እነዚህ ትልልቅ ከተሞች ራሳቸውን ማስተዳደር አለባቸው ስለሚባል ነው። በ“ዋን ዋሽ” የሚካተቱት መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች ናቸው። እነዚህም መካከለኛ ከሀያ እስከመቶ ሺህ ነዋሪ ያላቸው ሲሆን፤ እነዚህ በብድር ክልል ተበድሮ የሚሰራላቸው ስምንት ናቸው።
አነስተኛ የሚባሉት ደግሞ ከሀያ ሺህ በታች ነዋሪ ያላቸው ሲሆኑ፤ መክፈል ስለማይችሉ እንደገጠር ውሃ በድጎማ የሚሰራላቸው 62 ትንንሽ ከተሞች ናቸው። እነዚህም እንዴት አትራፊ ሆነው እንደሚቀጥሉና ሌሎች ጥናቶችም አብረው የሚካሄዱላቸው ይሆናል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የዝግጅት ስራ ስለሚሰራ የዘጠኙ ግንባታ ብቻ ዘንድሮ የሚጀመር ሲሆን አብዛኛውን ግን በቀጣዮቹ በሶስት አመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተቀምጧል።
በገጠር ውሃ አቅርቦት ረገድም በመጪው አምስት አመት ሶስት ሺህ 724 አዳዲስ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ይገነባሉ። አንድ ሺህ 630 የሚደርሱ ደግሞ ተሰርተው ግን በተለያየ ምክንያት አገልግሎት አቁመው የነበሩ እድሳት ይደረግላቸዋል። በተያዘው በጀት አመትም በ309 ወረዳዎች ላይ ስራው ይጀመራል። በተጨማሪ፤ አንዳንዶቹ የውሃ አቅርቦት ግንባታዎች ጠንከር ያለ ድርቅ ሲመጣ ይደርቃሉ። በመሆኑም ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ስራዎችንም በመስራት በርካታ መንደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 41 ፕሮጀክቶች ተይዘዋል።
ኮሚሽነሩ ጨምረው እንደተናገሩት፤ መንግስት በጀት መድቦ በብድርና በተለያየ መልክ የአዲስ የውሃ ልማት ግንባታም ሆነ ጥገና ቢያካሂድም አቅርቦቱ በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ማርካት አልቻለም። በሌላ በኩል፤ እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ተቋም ከተመረተው ውሃ 39 በመቶውን እየባከነ በመሆኑ ይህን ለመከላከል መሰራት አለበት። በተመሳሳይ ግንባታዎች በትክክል ባለመካሄዳቸውና ስራዎች በመጓተታቸው ህዝቡ ለአመታት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ሳያገኝ ይቆያል። በአንዳንድ ቦታዎችም በሁለት አመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ከስድስት እስከ አስር አመት እየቆየ፤ መንግስትም ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ነው። በመሆኑም፤ ስራ ተቋራጮችም ሆኑ አማካሪዎች ለትርፍ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዜጋ አስበው ቢንቀሳቀሱ ተገቢ ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አጃናው ፈንታ በበኩላቸው፤ በአመቱ የተያዘውን እቅድ ለማስፈጸም የአቅም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በማስቀመጥ በዚህ አመት በመጠጥ ውሃ በአስራ ዘጠኝ ዘርፎች ከ46 ጊዜ በላይ ስልጠናዎች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ይናገራሉ።
እንደዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ስልጠናዎቹ እንደየጉዳዩ ስፋት ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት የሚወስዱ ሲሆን፤ ከከልል እስከ ወረዳ በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጡ ይሆናል። በስልጠናውም በከርሰ ምድር ውሃ ጥናትና ቁፋሮ፤ በገጸ ምድር ውሃ ልማት፤ በውሃ ሀብት አስተዳደር፤ የለሙ የውሃ መሰረተ ልማት ጥገና፤ በውሃ ብክነት ቁጥጥር፤ በክትትልና ቁጥጥር ስነ ምግባር፤ እንዲሁም ሌሎች ከውሃ አቅርቦትና እንክብካቤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይካተታሉ።
ስልጠናው በሁለት መንገድ እንደሚሰጥ የገለጹት ም/ዳይሬክተሩ፤ የመጀመሪያው ኢንስቲትዩቱ እቅድ አውጥቶ በመንግስት ስር ላሉ በውሃ ዙሪያ ለሚሰሩ ተቋማት የሚያቀርበውና ከጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ይህ ስልጠናም በሌላ ቦታ ስለማይሰጥ ለግል ተቋማትም ይሰጣል። የዚህ ወጪ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነውም በኢንስቲትዩቱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመንግስትም ሆነ ለግል በዚህ ዘርፍ ስልጠና እንዲሰጠን እንፈልጋለን ተብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግና መመሪያ በማዘጋጀት ኢንስቲትዩቱ ስልጠና ይሰጣል።
በተጨማሪም ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትም በሶስት መንገድ ስልጠና ይሰጣል። በዚህም፤ የመጀመሪያ ለአመራሩ ስልጠና እንዴት እንደሚሰጡ፤ ሁለተኛ፤ ለአሰልጣኞች እንዴት እንደሚያሰለጥኑና በቀጥታ ሙያውን የተመለከተ ስልጠና ይሰጣል ። በሶስተኛ ደረጃ፤ ተቋማቱ በእነርሱ ደረጃ ለሰልጣኞች ማቅረብ ያልቻሉትን የቁሳቁስ ግብአትም ሆነ አሰልጣኝ ኢንስቲትዩቱ ያቀርብላቸዋል።
ይሄ የኢንስቲትዩቱ እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ፤ የበጀት ውስንነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ መሰናክል ሆኖብናል የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በጣም አዋጭ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም ለተጠቃሚ ተደራሽ ለማድረግ እንደተቸገሩ ይናገራሉ። በዚህም፤ ኢንስቲትዩቱ “ስማርት ቴክ” የሚባል ቴክኖሎጂ አዘጋጅቶ ለስራ ቢያውልም ተደራሽነቱ ግን በሚፈለገው ደረጃ አልሆነም። ቴክኖሎጂው በትልልቅ ማሽኖች የሚቆፈሩትን (እስከ ሰላሳ ሜትር የሚደርሱ) የውሃ ጉድጓዶች በቀላል ማሽኖች በአነስተኛ ወጪና የሰው ጉልበት ማልማት የሚያስችል ነው።
ቴክኖሎጂው በቀላሉ ንጹህ ውሃ የሚያስገኝ ሲሆን፤ በሰው ሀይል የሚቆፈርና በግለሰብ ደረጃ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር፤ ውሃ መሳቢያው ከነፓንፑ በሁለት ሺህ ብር ብቻ ሊሰራ የሚችል ነው። በፀሀይ ብርሀን ሀይል ውሃውን ለመሳብ ለሚፈልግም በአስር ሺህ ብር ወጪ ብቻ ማስገንባት የሚያስችል ነው። ቴክኖሎጂውን የማስተዋወቁ ስራ ባለፈው አመት የተጀመረ ቢሆንም፤ ለዚህ የሚለቀቀው በጀት አምስት መቶ ሺ ብር ብቻ በመሆኑ በአማራና በደቡብ ክልል ብቻ ለመወሰን ተገድዷል። በተያዘው በጀት አመትም በቂ በጀት ባለመኖሩ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልል ብቻ ለማስፋፋት ታስቧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት21/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ