ሀሳብን በተቃውሞም ይሁን በድጋፍ ለማሰማት በሌላው የመንቀሳቀስና በህይወት የመኖር መብት ላይ ጫና በማሳደር መሆን የለበትም። ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ህገመንግሥታዊ አይደለም። ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የሌሎችንም ነፃነት በማክበር መሆን እንዳለበት በህገመንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ተደንግጓል።
ሰሞኑን አክትቪስት ጁሀር መሐመድ ‹መንግሥት የመደበልኝ የግል ጠባቂዎቼን ሊያነሳብኝ ነው› በሚል በማህበራዊ ድረ-ገጽ ያስተላለፈውን መረጃ መሰረት በማድረግ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለቀናት በዘለቀው ግርግር ላይ የወጣቶች ስሜታዊነት የተሞላበት ሁኔታ ብዙዎችን አስገርሟል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹ኢኮሊጂካልና ሲስተማ ቲክዚዮሎጂ› የትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዓመት ዲግሪ ተማሪ ወጣት ፀደንያ ሰለሞን ተቃውሞው የሚገለጽበትን መንገድ ትቃወማለች። ‹‹ጩኽትና መጋደልን ለጥያቄ መልስ ማግኛ መንገድ አድርጎ መውሰድና በስሜታዊነት የሚደረገው እንቅስቃሴ የትም አያደርሰንም። ወጣት ስለሆንና ጉልበት ስላለን ብቻ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ብሎ ማሰብም ስህተት ነው። ይህ ስሜታዊነት ነው፤ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል።
ቆም ብሎ ቢታሰብ ግርግርና ሁከቱ ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እያስከተለ ነው። ይልቁንም የወጣትነት ጊዜን ባላስፈላጊ ነገር ላይ በመሳተፍ ከማባከን እራስንም ሀገርንም በሚያሳድግ ነገር ላይ በማዋል ለተሻለ ውጤት ለመብቃት መጣጣር ያስፈልጋል›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
እርሷና የትምህርት ቤት ጓደኞችዋ ትምህርታቸ ውን ጨርሰው በተማሩት ሙያ ሀገራቸውን ለማገልገል ያላቸውን ተስፋ የሚያጨልምና ራዕይ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ድርጊት እንደሆነ በመጠቆም ተግባሩን ትኮንናለች። ከእርሷ የሚጠበቀውንም ለመወጣት ጥረት ታደርጋለች። በግሏ ሁከትና ግርግር ውስጥ ተሳትፋ አታውቅም። ነገሮችን በውይይትና በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ ባገኘቸው አጋጣሚ ሁሉ ለጓደኞችዋ ትገልጻለች።
ሀሳቧን በሀይል እንዲቀበሉም አታደርግም። የሌላውን መብት ሳይጋፉ የራስን ሀሳብ ማራመድ እንደሚቻል የምታደርገው ጥረት ለታናናሾችዋ ትምህርት እንደሚሆን ታምናለች። ችግሮችን ለማስወገድ ሰው ከእራሱ መጀመር አለበት ትላለች። ነገሮችን በውይይት የማዳበር ባህል በቤተሰብ ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በአካባቢ፣ በጓደኛማማቾች መካከል ቢዳብር አሁን እየገዘፈ የመጣውን ሁከትና ግርግር ማስቀረት ይቻል እንደነበርም ትገልጻለች።
ወጣት ፋሩ ሁንዱማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹ኢኮሊጂካልና ሲስተማቲክዚዮሎጂ› የትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ናት። ‹‹እኔ ልክ ነው ያልኩት ነገር በሌላው እይታ ልክ ነው ማለት አይደለም። የሌላውን መብት አክብሬ ሀሳቤን ስገልጽ ሀሳቤን የማይደግፈኝ እንኳን ቢኖር ያከብረኛል ብዬ ስለማስብ መከባበሩ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ›› ትላለች።
በእርሷ እምነት አንድ ነገር ላይ ለመሳተፍ እኔ አስፈልጋለሁ? ለምንስ እሳተፋለሁ? ብሎ አስቦ እንጂ በስሜታዊነት መሳተፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ስሜታዊ ከሚያደርጉት ነገሮች መቆጠብ ያስፈልጋል። የሰሞኑ ግርግር ስሜታዊነት የበዛባቸው እንደበሩ ትገልጻለች። የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ እንቅስቃሴያቸውን ትክክለኛ ስለመሆኑም ትጠራጠራለች። እርሷ እንዳለችው መጠላላቱ ያመዝናል። ተቃውሞው ወይም ድጋፉ በትክክል ይሄ ነው ወይ? ሲባል መልዕክቱን ስቷል ስትልም ሀሳቧን ሰጥታለች።
‹‹በግርግሩ ላይ በስፋት ተሳታፊ የሆነው ወጣት ስለሆነ ነገ የሚረከባት ሀገር ምን አይነት ናት የሚለውን በምክንያታዊነት ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል›› የምትለው ወጣት ፋሩ ሁሉም ወጣት ተመሳሳይ የሆነ ተልዕኮ አለው። ወይም ደግሞ አንድ አይነት አመለካከት ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው ለማለት እንደማይቻል በመጠቆም በተለይ መንግሥት የወጣቱን ፍላጎትና ስሜት ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግራለች።
ለአዲስ አበባ ከተማ እንግዶች የሆኑት ወጣት ጌታቸው ሞገሴና መሀመድ ኑር ጌታቸው የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመሆናቸው በተስፋ ትምህርታቸውን ለመከታተል ተዘጋጅተዋል። እነርሱ ለትምህርት ዝግጅት ላይ ሆነው የእድሜ እኩዮቻቸው ደግሞ በእኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው በነገ ተስፋቸው ላይ በሁከትና ግርግር የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ይቃወማሉ።
መሀመድ ኑር ጌታቸው በከፊል መስማት አይችልም። ሁከትና ግርግር እንደርሱ ለተለያየ የአካል ጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች እጅግ የከፋ እንደሆነ ይናገራል። ተሳታፊዎቹ ወጣት መሆናቸው ደግሞ አሳዝኖታል። ከውጭ ሆኖ ከሚሰማው በስተቀር ጠለቅ ብሎ ነገሮችን እንዳልተረዳና የወጣቱ ፍላጎትም እንዳልገባው ይናገራል። ሲነገር ከሚሰማው ግን አሳሳቢ እንደሆነ ይረዳል። ሀሳብን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ እየተቻለ ባልተገባ መንገድ መንቀሳቀስ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና በህግም ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳል።
ጌታቸው ሞገሴ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ መማር የሚፈልገውን የጤና ትምህርት ለመማር ሰላም አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል። በሁከትና ግርግር ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶች በነገ መልካም ተስፋቸው ላይ እየቀለዱ እንደሆነ ሊገነዘቡ እንደሚገባም ይመክራል። ከብጥብጥና ሁከት ሞትና ጉዳት እንጂ ትርፍ እንደሌለው በተግባር እየታየ መሆኑንም አመልክቷል።
አስተያየታቸውን ያካፈሉን ወጣቶች ስሜታዊነት መዘዙ ብዙ መሆኑን ተገንዝበው በትምህርታቸው ጠንክረው ውጤታማ ለመሆን እየተጉ ይገኛሉ። ስሜታዊነት የነገ ተስፋን ያጨልማል። ከስሜታዊነት ሲወጣ እራስን መጥላትና መውቀስ ይመጣል። በአጠቃላይ ስሜታዊነት የወጣትነት ጊዜን ያባክናል።
ወጣት ፀደንያ ሰለሞን፤
አዲስ ዘመን ጥቅምት20/2012
ለምለም መንግሥቱ