መቼም ኑሮን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ኑሮህን ልብ ብለህ ብትከትበው የኮርስ ቁጥር አይሰጠው ” ኮንታክት አወር “ አይወሰንለት እንጂ፤ በየዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ያልተቀጠረለት ግሩም መምህር ነው፡፡ ይህንን ያልኩት በራሴ የተጓዝኩባቸውን የህይወት ምዕራፎችና ጊዜያት ልብ ብዬ ሳስባቸው፤ የተማርኳቸው ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ብዙ እየተማርኩ አንዳንዱን እየወደቅኩና በጸጋ እየተቀበልኩ ሌላውንም እያለፍኩ ነው፤ የመጣሁት፡፡ “ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ” እንደሚለው የቴሌቪዥን ማስታወቂያ፣ ኑሯችን ሁሌ “ሙሉና ዝግጁ” አይደለም :: ማቀድ ፣ መጀመር ፣ ማስኬድና መፈፀም የየራሳቸው ከፍታና ዝቅታ አላቸው፡፡
ስታቅድ ወይም ግብ ስታስቀምጥ ግብህን በትክክል ለመድረስ የሚያስፈልጉህን የሰው ሃይል፣ የመሳሪያ (የቁሳቁስ፣) እና የገንዘብ መጠንህን በማስተዋል ወይም በትክክል እደርስበታለሁ ፤ በምትለው አቅም ደረጃ መወሰን ያንተ ፋንታ ነው፡፡ የእነዚህ ሶስት አካላት ሁነቶች እርስ በእርስ መመጋገብ ነው፤ ያንተን ሥራ ጤናማ ውጤት የሚያመጣው፡፡ አንዱ ሲጎድል ሥራህን አንካሳ እንዳያደርገው የሶስቱንም ምንጭ በማስተዋል ማቀድ የተገባ ነው፡፡
ሥራውን ከሶስቱ አንዱ ባልተሟላበት ጀመርክ እንበል፤ ተስፋ የምታደርግበት ምንጭ እንኳን በራሱ ምክንያት አልሟላ ካለህ የሥራው አጀማመር ካነሰ አካሄዱ አነከሰ ማለት ነው:: እንዲህ ከሆነ ምንም እንኳን ፍጻሜው የማይቀር ቢሆንም ጊዜ የተባለ ሃብትህን አባክኖ ነው፤ ወደታሰበው ግብ የሚደርሰው፡፡ በሂደቱ ውስጥ የማቴሪያልና የገንዘብ አቅርቦቱ ተሟልቶ እንኳን የሰው ሃይሉ ተግባብቶ አለመስራት ስራውን እንደሚበድለው ማጤን መልካም ነው፡ ፡ ሰራተኛው ሃይል መጥቶ እንኳን በሥራው ላይ ከለገመ ፕሮጀክትህን ማጓተቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ትዳር አንዱ የህይወትህ ፕሮጀክት ቢሆን በውስጡ አራት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጉታል:: በቅድሚያ የአንተና ሴቷ በአካል መገናኘት፣ ሁለተኛ ማደሪያ በጀቱ፣ ሶስተኛ መጠለያው፣ አራተኛ በአእምሮና መንፈስ መግባባት ሲሆን ከእነዚህ አንዱ በጎደለበት ትዳሩ አንካሳ ፕሮጀክቱ በከርካሳ መኪና የሚከናወን ነው ፤ የሚሆነው፡፡ ከርካሳ መኪና ደግሞ ከሚያግዘው ይልቅ የሚታገዘው ይበልጣል፡፡
በትዳር ውስጥ ፍቅሩ ካለ ሁሉም አለ፤የሚባል ቋንቋ የሚሰራው በሰው ስር ጥገኛ በሆኑባቸው በመጀመሪያዎቹ የፍቅርና የማር ጨረቃ (Honey moon) ወራት እንጂ አብረው መኖር ከተጀመረና ፕሮጀክቱ ከተመረቀ በኋላ እንኳንስ በጀት የሌለው ጥምረት ፣ ዕዳ ያለበት ቤት እንኳን ፍቅሩን ያመክነዋል፡፡ እዚህ ላይ የምን ዕዳ ልትሉ ትችሉ ይሆናል፤ አንዳንዱ በቅጡ ሳይቆም ተከምሮ፣ ሳይጀምር እዳ ሰፍሮ፣ ሃይለኛ ድግስ ደግሶ ወደ ጎጆው ቁልል ዕዳ አፍሶ ነው፤ የሚገባው፡፡ ስለዚህ የሰርጉን እዳ ለመቀፍቀፍ ከዝምታ እስከ መዘጋጋት የሚያስከትልና “አንተ ነህ – አንቺ ነሽ” ወደሚያባብል ዘለፋ የሚወርድ ድንገቴ ይፈጠራል፡፡ ያ፣ ብቻ አይደለም “ገደ-ቢስና ኮቴ ደረቅ” ወደመባባል ደረጃ ያዘቅጣል፡፡ ወይ አቅምን አለማወቅ!
ሲጀመር ያኳረፈ፣ ሲሄዱበት እንዴት እንደሚያምና እንደሚቆረቁር እናንተ ገምቱ:: ስለዚህ ሁሉንም በማስተዋል ማስኬድ በጣም ያስፈልጋል ፡፡ “ያለዕዳ ዘመዳ” ያለው ማን ነበረ? ረሳሁት፡፡ እዳ በሌለበት የተደረገ ጥምረት መልካም ጋብቻ ብቻ ሳይሆን በንፁህ አንሶላ ቤት ያስጀምራል፡፡ ያለ ውዝፍ ዕዳ ዝምድናን እንደማጠናከር ትዳርን መስርቶ ልጆችን እንደማሳደግ ያለ ጥሩ አካሄድ የለም፡፡ እንዲህ ስንል ፣በኑሮ ጉዞ ውስጥ ዕዳ አያጋጥምም ማለት አይደለም ፤ በራስ ህመም፣ በድንገተኛ አደጋ፣ በዋስትና ጦስ፣ በልጆች ጥፋት፣ ወዘተ… ዕዳ ውስጥ መገባቱ ያለ ነው:: ግን አውጥተውና አውርደው ከቤተዘመድ ተማክረው ያደረጉት እርምጃ አያስወቅስም:: ለሌላው ደስታ ፣ ለስም መጠሪያ ፣ ለላንቲካ እና እዩኝታ ዕዳ መግባት ግን ፌንጣነት ነው፡፡
ከዚያም በኑሮ ሂደት የሚያጋጥሙ በርካታ የህይወት አንጋዳዎች ብዙ ናቸው:: እርስ በእርስ ለመማማር ያልተዘጋጀ ልብ፣ የሚመከረውን አልሰማ ማለትና መካሪን መጥላት ፣ ነፋስ አመጣሽ ገንዘብ (ጉቦ፣ ህገ- ወጥ ንግድ፣ ያልታወቁ ሽርክነቶች …ወዘተ) የሚያሳብጠው ልብና የሚያስከትለው ጦስ፣ ዝናና ያልታሰቡ ክብሮች የሚያስከትሉት መቆለሎች ትዳርን በጎሪጥ ኣይን የሚያሳዩ ቤትን የሚያሳንሱና ራስን የሚጥሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ባሎች ሆይ! ባደግን ቁጥር የተነሳንበትን አንርሳ!
ከዚህ ሌላ እስቲ አንዳንድ ባሎች ሚስቴ ጠገበች፣ በጣም እየተበተች ነው፤ ልቧ ደጅ ደጅ ሳይል አይቀርም ብለው ሲያስቡና ችግራቸውን ወደውስጥ፣ ከማየት ይልቅ ወደውጭ ማየት ሲጀምሩ የሚናገሯቸውን ሐረጎች ጥቂቶቹን እንያቸውና በመጠኑ እንተንትናቸው፡፡
ቅድመ ጋብቻ ግንኙነቷን አስበውበት ያውቃሉ? ስንል ብዙዎቹ ወድጃታለሁና፤“ይቺን ልጅ አጋቡኝ” ይሉና በቤተዘመድ ግፊት ልጅቱን በእጃቸው የሚያገቡ ሲሆን ከጋብቻው ማለዳ ጀምሮ ችግሩ እንደሚጀምር አይጠረጥሩም፡፡ ምክንያቱም ልጅቱ በሌላ ሰው ፍቅር ተይዛ እያለች በአሁኑ ባሏ ቤት የገባች ልጅ ልትሆን ትችላለችና ፡፡ አንድም በቤተሰብ ግዳጅ ሁለትም በኑሮ ግፊት ገብታ ከዚህኛው ሰውዬ ጋር ሆና ያኛውን ሰው ልታስብ ስለምትችል በጥንቃቄ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ እናም በዚህ ሳቢያ ባሎቻቸውን የሚጠሉ ሚስቶች ቢኖሩ አይገርምም፡፡ ምክንያቱም ይኼኛውን ሰውዬ አቅፋ ያኛውን ሰውዬ እያሰበች ነውና ፡፡ ይኼ ደግሞ በጠላው ሰው ግንባር ላይ አይጻፍ፤ ችግር ነው!! ይኼኔ ነው እንዴት ነሽ፤ ደህና ነሽ ማለት!!
የጠበቁትን ደስታ ማጣት ፡- ሌላው ሴትየዋ ዓመሏ ተለውጧል ብለው የሚያኮርፉበት ምክንያት ፣ ሴቶቹ በጋብቻ ህይወቴ አገኛለሁ የሚሉትን ደስታ በገቡበት ቤት ውስጥ ሲያጡት ወይም ጣዕሙ አልገባቸው ሲል አንድም “አይሸቱም” አለያም ”አይገሙም” ፡፡ እንዲህም ማለት ለሚሆነው ነገር የሚያሳዩት ምላሽ መደነቅም መገረምም፣ ማዘን መተከዝም የሌለበት የማይነበብ ፊት ይሆናል ማለት ነው:: በጣም የተደሰተችበት ቀን ነው፤ የተባለ እለት ጥርሷን ብልጭ አድርጋ የምትዘጋበት ቅጽበት ይሆናል ማለት ነው:: እናም ሴትየዋ ባሏን የጠላች ይመስላል ፤ ወይም ውዴታዋን ማሳየት አትፈልግም፡፡
በተጨማሪም ሰውየው ሲመገቡም፣ ሲለብሱም፣ ሲንሸራሸሩም፣ ዘመድ ጥየቃ ሲሄዱም በቤታቸው በአልጋቸው፣ የአፍቃሪ ባልነት ገጽታና አክብሮት ሲሸሻቸው ሴትየዋ ቁጣ ቢቀናት በሰበብ አስባቡ ነገር ነገር ቢላት አይፈረድባትም፡፡ በትዳር ውስጥ ሴትን ልጅ ከሲኦል የከበደ የሚነዝራት ነገር ቢኖር ንቀት ነው፡፡ የተናቀች የመሰላት ቀን ባሏን የባለስለት ወንበር ላይ ነው፤ የምታስቀምጠው ፡፡ ስለዚህ ጠባይዋ ተቀይሯል ሳይሆን ባህሪዋ እንዲቀየር ምን አደረግኩ ማለት ነው ፤ ዋናው ነገር፡፡
ሌላን ማወደስ…ባል ሆይ! በሄድክበት ስፍራ በተገኘህበት አደባባይ ፣ ብትችል ራሷን ሚስትህን እንጂ ዘመድህ ያልሆነችን ሌላ ሴት፣ አቤት አለባበስ፣ አቤት አመጋገብ፣ አቤት አረማመድ፣ አቤት አወራረድ ብለህ በሌላ ሴት መቀመጫ ዙሪያ ኣይንህ ከመንከራተቱ ሌላ ፣ በአፍህ ማወጅ ከጀመርክ ወዮልህ:: ሚስት፣ የገዛ እህቷ እንኳን ባንተ አፍ እንድትወደስ አትፈልግም፡፡ ብዙ ጊዜ ለትዳር መፍረስ ምክንያቶቹ እንዲያውም የቅርብ ዘመዶች ተገቢ ያልሆነ ቅርበት እንደሆነ የአማካሪዎች ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ እህቴን ፈለጋት፤ አባበላት፣ አላግባብ አቆላምጦ ፊቴ ላይ ይጠራታል፤ ጠረጥራቸዋለሁ፣ ላዩ ላዩ ስትለጠፍ ተይ አይላትም ፤ እንዲያውም የሆነ ነገር በመካከላቸው ያለ ይመስለኛል፤ እነርሱን ማየት እየዘገነነኝ ነው፤ ይላሉ ሚስቶች፡፡ ስለዚህ ከአፍህ መቆጠብ ለሰላማዊ ትዳር ምቹ መሆኑን ማወቅ መልካም ነው፡፡
ሌላው፡- የሚገርመው ደግሞ ምስኪኗ ሚስትህ ፊት አንዴ ሳይሆን ደግመህና ደጋግመህ ስላለፈችው “ሚስትህ” ሆነ ሴት ጓደኛህ በአድናቆት ደጋግመህ ታወራለህ:: ይህች ሰው ምን የሚሰማት ይመስልሃል ? እሷን እያሰበ ነው እኔን ያገባኝ ስለዚህ እኔም …ላ ብትል ምን ይውጥሃል ፡፡ አይደለም ስለዛኛው ወንድ መልክና የአለባበስ ችሎታ፣ እቃ ወድቆ የሌለ የወንድ ስም ሁለት ቀን ብትጠራ መፈጠርህን ነው የምትጠላው:: “ማነው እሱ ፣ ማን አልሽው? ከየት የመጣ ስም ነው፤ እንዴት እኔ እያለሁ፤ የሌላ ወንድ ስም ይጠራል? የትኛው አጎትሽ ነው? የአባትሽ ስም እንዳልሆነ አውቄያለሁ፤ እና ማነው” ማለትና መለፍለፍ ትጀምራለህ፡፡ እና ያንተ ጊዜ ሲሆን ግን ቅቤ እየቀባሃት ነው? የእሷ ጊዜ ግን የጋለ ብረት ምጣድ አተኮሰህ ? ስለዚህ ተው ፤ አትገበዝ!! የእሷም ህመም ይመምህ:: ይቅር ብለን ነው እንጂ፤ ማቃጠሉንማ እኮ ተክነንበታለን ፤ ብትልህ ምላጭ ትውጣለህ:: እና ጠንቀቅ፡፡
ቃልህን ትጠብቃለህ? ባል ሆይ! ቆንጆዋን ሚስትህን ከማግባትህ በፊት ከገባህላት ቃሎች የትኛውን ፈጸምክላት፤ ወይ ሙከራ አደረግክላት? አስተምርሻለሁ ብለህ ነበር? መኪና እንገዛለን ብለሃት ነበር? የሥራ ለውጥ አደርጋለሁ ብለሃት ነበር፤ ቀለበታችንን ለውጠዋለሁ ብለሃት ነበር? ልጃችንን ጥሩ ትምህርት ቤት አስገባዋለሁ ብለህስ አልነበር? እህትህን ወደቤተሰቦቿ እመልሳታለሁ ያልከውንስ ነገር ረሳኸው? በሱቅ በኩል ስታልፉ ገዛልሻለሁ ያልካትን ቀሚስስ ገዛህላት? ቁምነገሩ ያንተ መግዛት እንጂ ራሷ እኮ ልትገዛው ትችላለች ፤ አንተ ግን ጉዳዩን እንኳን አንስተህ ተስፋዋን ለማለምለምና አለመርሳትህን ለመናገር እንኳን ፈርተህ አድፍጠሃል፡፡ እና ቃል አባይ ባል ብትልህ ትፈርድባታለህ?
ማስታሻ ከአንድ ወገን መጠበቅ፡- ለሥራ፣ ለቀጠሮ፣ ለፍቅር ፣ ለማህበራዊ ጉዳይ ፣ ለመድሃኒት ፣ ለምግብ ወዘተ…መልእክት ከእርሷ ብቻ የምትጠብቅና አንተ የማትነሳሳ ከሆነ ይከፋታል፤ ቢነኩት ደንገጥ የማይል ጉድ ነህ ትልሃለችና አስታውሰህ መደወልን አትርሳ! እሷን ብቻዋን የማንቂያ ሰዓት (Alarm watch) ማን አደረጋት ? እንዴ እርሷም እኮ አሳቢ ያስፈልጋታል እኮ፤ ቀዳሚው ሰው ደግሞ አንተ ነህ ፤ ማንም የለም፡፡
አሳቢነቷን አታጣጥል፤አስባና ተጨንቃ ሸሚዝህ ቆሽሹዋል ለውጠው፣ ከራባትህ ተዛንፏል አስተካከለው፣ ቅንጬው ጥሩ ነው ብላው፣ ላንተ ያዘጋጀሁት ነው፤ ቅመሰው ስትልህ ነገሯን ሁሉ ካጣጣልከው ምኑን አጋር ሆንክ፤ ባታጣጥል እንኳን አመሰግናለሁ ማለትን ማን ገደለ፤ እና ማን ነህና በዝምታህ ታስጮሃታለህ? ስለዚህ ትጠላሃለችና አስብበት:: አድናቆት ቢቀር እርግማንና ምሬቱን ምን አመጣው?
በየምክንያቱ ካልተደባደብኩ ትላለህ? ዱላ አህያን ከመንገድ ይመልስ ይሆናል እንጂ ሰውን አያርመውም፡፡ ደግሞ ሁሌ እንደተደባደብክ አትዘልቅም፡፡ አንድ ቀን የጠርሙስ አንገት ይዛ እስቲ ንካኝ ያለችህ ቀን ግን “ሰማይ ምድሩ” ይዞርብሃል ፡፡ በጡንቻ ማሰብ ላንተ ብቻ የፈቀደው ማነው፡፡ ደግሞ ብዙ ጊዜ ቀድመሃት ስለምትተኛ በእሷ ይቅርታ ስር መሆንህን አስበኸው ታውቃለህ? በተኛህበት እኮ፣ አለ ብዙ ነገር!!
አንድ ምሳሌ አስታወስኩኝና ላካፍላችሁ:: ወጣት ባልና ሚስት ናቸው ፡፡ ሁለት ልጆች አላቸው፡፡ አንድ ቀን ምሳ ይጋብዙኛል፤ ሄድኩ:: ከእርሱ ጋር ፣ እንደገባን “የእጅ ውሃ አለ እስቲ አምጪ” ማለት፡፡
“እራስህ ወስደህ እንግዳችንን አስታጥባ !” ሚስት፡፡
“ምን አልሽ?” ማለት ፤ ባል፡፡
“ሰምተሃል !” ትመልሳለች ከጓዳ ፡፡ በንዴት ወደ ውስጥ ሲገባ አየሁት፡፡ እናም የሆነ የሆነ ነገር ተነጋገሩና ግድግዳው ግው ሲል ሰማሁት፡፡ ሚስት ወደቀች መሰለኝ ፡፡ ቀፈፈኝ፡፡ ከዚያም ፣ እንደ ጤነኛ ሰው ወደ እኔ መጣ ፡፡ “ምንድነው የወደቀው” አልኩት ፡፡ እ…እቃ ነው፤ አለኝ፡፡
ሚስት ቲማቲም ይመስለኛል፤ በፍጥነት ትከትፍ ነበረ ቅድም፡፡ አሁን ቀስ እያለች መከተፉን ቀጠለች፡፡ ትንሽ ቆይቶ ፣ “ኧረ፤ እየራበን ነው ምሳ ! (ባል)
እሺ ና-ና ይዘህ ማውጣቱን አግዘኝ አለችው፡፡(ሚስት)
የቅድሙን በአፍታው ረስቶት፣ ሳያቅማማ ሊያግዛት ፣ ገባ ፡፡ በአፍታው እትትት …ብሎ ሲጮህ ሰማሁት ፡፡ ሳቄን እፍን አድርጌ ፣ ምን ሆናችሁ? አልኩት ፡፡ ም…ን…ም…አለና መጣን- መጣን አለኝ፡፡ ወደ ሳሎንም ደም በደም መስሎ ብቅ አለ፡፡ ለካ ልክ ወደ ኪችን ሲገባ ለምሳ ያዘጋጀችውን በቁንዶ በርበሬ ያበደ ቲማቲም ቸልሳበታለች፡፡ ሳቄን አፈነዳሁት፡፡
ይኸውልህ እንዲህ ነን ፤ አለኝና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ …. ምሳው መጥቶ መብላት ጀመርን፡፡ በመሐል፣ ቅድም የወደቀው እቃ ምን ነበር ስለው ፤ ሚስት ቀደም ብላ ፣የማይነካ እቃ ነክቶ እኮ ላዩ ላዩ ተመልሶ ወድቆበት ነው፤ አጸፋውን ያገኘው አለች፤ እየሳቀች ፡፡ እናም ባልሆይ! አንዳንዴም አፀፋ አለና፤ ደርሰህ በሰው ፊት አትገበዝ፡ ፡ እዚህ ላይ አጸፋዊ ድርጊትን እያደፋፈርኩ አይደለም፡፡ ግን የሚያስጠላብህን እያደረግክ ብቻ አትኖርም ፤ የምትጠላውም ሊደርስብህ ይችላል ማለቴ ነው:: ጡንቻህን በትልቅ በትንሹ ጉዳይ ላሳይሽ አትበል፡፡
ደግሞ ወደሌላው ባህሪህ እንለፍ:: አንድ ባል ለሚስቱ ያደረገው ነገር እኮ፣ ለራሱ ያደረገው ነው፤ እና በሰው ፊት ሰበብ ፈልጎ እንዲህና እንዲያ አደረግኩልሽ ብሎ መዘባነንን ምን አመጣው፡፡ ከዚህም መታቀብ መልካም ነው፡፡ ከዚህ በፊት የአንገት ሃብል ገዝተህላት ነበር ? ታዲያ የትም ጣለችው እያልክ ማውራቱ ምን ይጠቅምሃል ፡፡ አንተስ ብትሆን ልትጥለው አትችልም ነበር? ይሄኔ፣ የጋብቻ ቀለበትህ ጠፍቶ ሳትነግራት አሰርተህ መምጣትህን ፣ አልነገርካትም ፡፡ ዕቃ በመጣል አንተን የሚደርስብህ ማን አለ?! ማንም ፡ ፡ ዕቃ ጥለህ መጥተህ ቀድመህ የምትቆጣው አንተ አይደለህም እንዴ? ስለዚህ ዝም በል:: ቢጠፋም የጠፋው ላንተ ብቻ ሳይሆን ለእርሷም ነው፡፡
ቂመኛ ነገር ነህ? ይቅርታ ካለማድረግህም ሌላ በየጊዜው ደጋግመህ የበደለችህን በደል ሰበብ ባገኘህ ቁጥር ማነሳሳት ለማንም አይጠቅምም ፡፡ ሆዴ ውስጥ የያዝኩት ብዙ ነገር አለ፤ ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንጂ፣ እያልክ የምታላዝነውን ነገር አቁምና ያለውን ዘርግፈኸው ይውጣልህ ፡፡ እንዲያውም ነገር በሆድ ሲያድር የአንጀት አልሰርና ጨጓራን ማቃጠል ነው ትርፉ፡፡ አንዴ በተናገርከው ጉዳይ ምሽቱን ሙሉ አትነዛነዝ፤ አንቺ እዚህ ቤት ያለሽው እኔን አቃጥለሽ ለመግደል እንጂ ለሌላ አይደለም እያልክ ሰላሟን አታደፍርሰው::
እባክህን በእንግዳ ፊት መናገር ካልቻልክ ደግሞ ዝም በል ፡፡ የምትናገረው ካላማረልህ በዝምታህ ውበት አሳልፈው፡፡ የተጋበዘች የሰው ሚስት እቤትህ መጥታ ፣ ምን ሲደረግ ነው፤ እንኳን አንቺን ያላገባሁ ሚስቴ ውብ እኮ ናት ብሎ ነገር ቀልድ ነው ? ዚቅ ነው? የጓደኛህን ፤ ልጅ እያየህ ደግሞ ይቺ ልጅ እኮ ደረሰች ፤ ባል አምጡ ብላለች እያሉ መፏነን ምንድነው:: አድማጩ ጓደኛህ ምቾት የሚሰማው ይመስልሃል? በዚህስ ባለቤትህ እንዴት እንደምትሸማቀቅ አስበኸዋል:: እንዲህ እንዲህ ያለው ባህሪህ ግምት ላይ አንተን ከማስጣሉም በላይ እንግዶችህን አሸማቅቆ ባለቤትህን ጥፍሯ ውስጥ መደበቅ እንዲያምራት ያደርጋልና ተቆጠብ፡፡
ከሁሉም ከሁሉም የከፋው ደግሞ ፣ ለካ ዘርሽ እንትን ነው፤ ሳላውቅ ነው እኮ ያገባሁሽ ማለት የጀመርክ ዕለት …(አንዳንድ ባሎች ይህንን የሚሉት ደግሞ ልጆቻቸውን ከዳሩ በኋላ ባለው ዕድሜ ነው…አስቂኞች ናቸው) ይህንን ያልክ እለት በመንፈስ ሙትቻ፣ በአስተሳሰብ ኮትቻ፤ በአመለካከት “ጉራቻ” (ጥቁር እንዲሉ ኦሮሞ ዘመዶቻችን) ሆነሃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዘረኛ አትሁን!!
በገንዘብ ላይ መንቻካ ነህን? … ያለፈው ወር ጤፍ እንዴት ቶሎ አለቀ? ሌማቱ ውስጥ ስንት እንጀራ ቀረ? ባይ ዓይነት ሰው ነህ ? እንዲህ የምትመናቸክ ከሆነ፣ ወዮልህ አንድ ቀን ቆጥራህና አስቆጥራህ ሲሰለቻት ከአጠገብህ የሄደች እለት “ምጣዱን አስማልኝ፤ ወጡን አማስልልኝ፤ ሚጥሚጣውን ደቁስልኝ፤” የምትል ትመጣብህና መፈጠርህን ትጠላለህ:: የማጀትና የየቤት አስተዳደሩን ጉዳይ ነጻነት ከሰጠህ አንተም ነጻ ትሆናለህ፣ ስትጋበዝና ምክር ስትጠየቅ ያኔ ትሰጣለህ፡፡ እና በገንዘብ ጉዳይ ነዝናዛ አትሁን!!
በማንኛውም ማህበራዊም ሆነ ግለሰባዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አንተ የምታስበውን ሚስትህ ልታስብ እንደምትችል አድርገህ መቀበል ካልቻልክና እርሷን ከግምት አሳንሰህ ማየት ካላቆምክ … በጎደልክበት ልታሟላልህ ባነስክበት ልታገዝፍህ የምትችል አድርገህ ካላየሃት፣ ህይወትህ መመሰቃቀል ይጀምራልና ፤ ደጋግና መልካም በሆኑ ጉዳዮች ራስህን በምትገምትበት መስፈርት ሁሉ እርሷንም ማየት አትርሳ፡፡ ለክፋትማ ማን ብሎን ፤ “ኧረ ይሄን ባሌን አንድ በሉልኝ!” ማለት ከጀመረች አበቃልህ! ስለዚህ እነዚህን ወይም ከእነዚህ ፣ ብዙውን አለማድረግ “አቶ ባልን” እንደሚያስወቅስህ አውቀህ ብትጠነቀቅ መልካም ነው፡፡
ቤተሰብ ስንል የተሟላ እና ሁሉ ሙሉ የሆነበት ቤት አይደለም ፡፡ ቤተሰብ ስንል ትንሽ ሆስፒታል፣ እንዲሁም ፈውስ ፤ ትንሽ አስራት ደግሞ መፈታት፣ ትንሽ ለቅሶ ደግሞ ደስታ፣ ትንሽ ጉስቁልና ደግሞ ፍንደቃ ያለበት ተቋም ነው፡፡ ትልቁ መንግስት የሚቆምበት የሀገር መሰረት ቤተሰብ መሆኑን አንርሳ!! በነገራችን ላይ ሚስቶች… በሚቀጥለው ጽሁፍ እንገናኝ !!
መልካም የማስተዋል ሳምንት ይሁንልን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ