– የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች
ትናንት ደሙን ከፍሎ ያመጣውን የለውጥ ጭላንጭል መቋጫ ሳያበጅለት በሚያጠምዱለት መረብ ሥር ወድቆ ጭንቅ የወለደው አንድነቱን፣ የኦሮማራ ጥምረቱን፣ እትብት መቅበሪያ እናቱን በዋዛ የሚክድ ወጣት ማየት ያሳፍራል። አዎ ወጣት ከአንደበቱ የሚወጣው የእምነት ቃል በወገኑ ዘንድ መኩሪያ እንጂ ማፈሪያ መሆን የለበትም።
በዚህ መነሻነት በሀገራዊ የለውጥ ሂደቱ ‹‹ደምህ ደሜ ነው›› ፣‹‹የአንተ ሀገር የኔም ነው››፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› በሚል ከሌሎች የሀገሪቱ ወጣቶች ጋር አያሌ ፈተናዎች የከፈለው ኦሮማራ ጥምረት (ቲም ለማ) አሁን የሚገኝበት ቁመና ምን ይመስላል? የሚናፈሱ ትርክቶችን መክቶ ለውጡን የማስቀጠል ሚናውስ? ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደምሮ ያረጁ አስተሳሰቦችን በመታገል ለሀገር ሰላምና አንድነት ሚናውን እየተወጣ ይሆን? ስንል ወጣቶችንና የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል።
ለሀገራዊ ለውጡ መምጣት በድርጊትም ሆነ በአስተሳሰብ ከፍተኛ ጫና በማሳደር የአንድነትና የፍቅር መሰረት የጣለው የኦሮማራ ጥምረት አሁንም በስራ ላይ ይገኛል የሚለው ወጣት በላይነህ ስላይኑ፤ ወጣቶች ሀገር በማፍረስም ሆነ ሀገር በመገንባት ሂደት ዋና ተጠያቂዎች ናቸው። በመሆኑም በሀገሪቱ የሚገኙትን ስራ አጥ ወጣቶች ለረብሻ በመጠቀምና መሰረት የሌላቸው ትርክቶችን በማሰራጨት ትርፍ የሚነግዱ ቁጥራቸው ከፍ ብሏል። በተመሳሳይ የጋራ ጥረት ውጤቶችን፣ የጋራ ታሪኮችንና የጋራ ድሎችን ጭምር ‹‹የኔ ነው፤ የኔ ነው›› ባይ ስግብግብነት የተጠናወተው የሚመስል ቡድንም ትታዘባለህ። ነገር ግን ይሄ አካል ወይም ቡድን ሁሉንም ብሔሮች የሚወክል ተደርጎ በፍጹም ሊወሰድ አይገባም ይላል ወጣት በላይነህ።
እንደ ወጣት በላይነህ ገለፃ፤ ወጣቶች የአባቶቻቸውን ታሪክ ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። የትኛው ነው እውነት? የትኛው ነው ስህተት የሚለውን መለየት ይኖርባቸዋል። ታሪክን ጠንቅቆ ማወቁና እንዲጎለብት ማድረጉ ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ ያልተረዳ ትውልድ መፍጠርና ታሪክን አለማስተዋወቁ ደግሞ በተገላቢጦሹ ታሪክ እየተለካ ለጥፋት መሳሪያ ማጥመጃ የሚውልበት እድል አልፎ አልፎ እንደምናየው በጣም ሰፊ ነው ሲል አጫውቶናል።
በኦሮማራ ጥምረት መካከል ምንም ችግር አይፈጠርም፤ ምክንያቱም ትስስሩ የፖለቲካ
አይደለም፤የወጣት ለወጣት እና በአጠቃላይ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች ድሮም የነበረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ጥምረት ነው። ለጥቅም የሚፈልጉት አካላት ዛሬ ላይ እኛ የመሰረትነው አስመሰሉት እንጂ እኮ አባቶቻችን ከጥንት ጀምሮ የሚያደርጉት መስተጋብር ነው።
የተጋቡ፣የተዋለዱና አብረው የኖሩ ሕዝቦች ናቸው። መቼም ሊፈርስ፣ ሊቀርና ሊቀየር አይችልም። አንዳንድ ስግብግብ ሰዎች የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ነጥሮ ወጥቶ ስለሚታይ እንጂ ተቆጥሮ የማያልቅ መልካም ስራዎች በመካከላችን አሉን። መጋጨት ቀርቶ ሕዝቡ መቀያየምን አያስበውም፤ወንድም ከወንድሙ ጋር እንዴት ሆኖ ይለያያል። በማለት የአማራ ተወላጁ ወጣት አስረድቷል።
ወጣት ብርቅነህ ጋሻው የኦሮሞ ተወላጅ ሲሆን በኦሮማራ ጥምረት ብቻ ሳይሆን በብዙ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በወጣቱ ዘንድ ብዥታ ይስተዋላል ይላል። የችግሩ ምንጮች መንግስታዊ መዋቅሩና ባለስልጣናት አካባቢ እንጂ ወደ ሕዝቡ የደረሰ አይደለም። ነገር ግን በማህበረሰቡ ዘንድ ምንም አይነት ችግር አለመኖሩን ያስረዳል።
አክቲቪስት እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኛው አሰራራቸው በብሔራቸው ላይ በጠባቡ የተንጠለጠለ በመሆናቸው የተበረዙ ሃሳቦች ለማራመድ ተጋላጮች ሆነዋል፤ተከታዮቻቸውም በዚሁ በሽታ ይለከፋሉ፤በስሜት ተመርተው ያልሆነ ተግባር ይሰራሉ የሚለው ወጣት ብርቅነህ፤ የሕዝቡ ችግር አለመሆኑን አስረግጦ ያስረዳል። ለውጡም ወደ ኋላ በምንም ተአምር የሚመለስ አይደለም ምክንያቱም ሰው በብሔሩ ታጥሮ ማሰብ አሁን ላይ አይሰራም፤ ጊዜው ከዚያ ተሻግሮ ማሰብን ይጠይቃል። መደመር እሳቤው እኮ ይሄ ነው።
ነገር ግን በጥቅም የሚታለሉ ወጣቶች በየትኛውም ብሔር ይኖራሉ። እነርሱ በሚፈጥሩት ችግር የኦሮማራ ግንኙነት ሻክሯል ወይም ተበላሽቷል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአዲስ አበባና በዙሪያው በቅርቡ የሚስተዋሉ ችግሮችን መንግስት ሰፊ ኃላፊነት ውስዶ ማስተካከል ነው ያለበት። በጥቂት ሰዎች ስሜታዊ መሆን የተፈጸመ እንጂ ሕዝቡን የሚወክል አይደለም።
ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ መጠየቅና መወያየት እየተቻለ ወጣቶች አላስፈላጊ ጥፋቶች ማድረስና የማህበረሰቡን ሰላማዊ ሕይወት ማወክ ተገቢ አይደለም። ወጣትነት ሲደመር፣ ስራ አጥነት፣ ስሜታዊ ያደርጋል። በአብዛኛው ለዚህ ተጋላጭ ሲሆኑ የሚስተዋሉት በአደረጃጀት ያልታቀፉ እና በተለያዩ አስተሳሰቦች የተጠለፉ ወጣቶች ናቸው።
የኦሮማራ ጥምረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፤ በሀገሪቱ ሰፊ ቁጥር የሚሸፍን በመሆኑ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል። በዚህ ምክንያት በመካከላቸው አለመተማመን እንዲፈጠር በማድረግ የራሳቸውን አላማና ጥቅም ለማስፈጸም የሚሯሯጡ አይጠፉም። በቀጣይም ይኖራሉ። ወጣቱ ለሰላሙና ለደህንነቱ ዘብ መቆም አለበት።አሁን የሚስተዋሉ ችግሮች በጣም ጥቃቅንና የሚጠበቁ ናቸው፤የሚያሰጉ አይደሉም በማለት ወጣት ብርቅነህ ተናግሯል።
የአማራ ተወላጁ ወጣት ጌታቸው አበራ እንደተናገረው፤ የኦሮማራ ጥምረት ወይም በአማራና በኦሮሞ መካከል ጦርነት ሊከፈት መሳሪያ እየተወለወለ ያለ የሚያስመስለው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው። በተግባር ግን አንድም ችግር የለም። የኦሮሞም ይሁን የአማራ ወጣቶች ለዚህ አይነት ጫጫታ ጆሮ አይሰጡም።በዚህ ነገር ቢነሱማ ኖሮ እስከአሁን ድረስ ከፍተኛ ችግር በተፈጠረ ነበር።ስለዚህ አሁን ላይ ወጣቱ ምክንያታዊ መሆን ጀምሯል። በማያምንበት ጉዳይ እጁን አያስገባም። ሀገራዊ ለውጡ መሰረት እስኪይዝ ድረስ የሚነፍሱ ንፋሶች እንደሆኑ ጠንቅቆ ይረዳል፤
ተግባሩን ከኋላ ሆኖ ማን እንደሚመራው በግልጽ ይታወቃል። የማጋጨት ዘመቻው እኮ ከማህበራዊ ሚዲያው አልፎ በመግለጫ ጭምር እየሆነ ነው። መንግስት ለሕዝብ መርዝ የሆነ አስተሳሰብ የሚረጩ ግለሰቦችንና ባለስልጣናትን እንዲሁም ሚዲያዎችን ለይቶ ማስተካከል አለበት ሲል ወጣት ጌታቸው ተናግሯል።
የሚዲያ ተቋማት እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግለሰቦች ከየትኛውም ነገር በፊት ሀገራዊ ሕልውናን የሚያስጠብቅ ስራ ሰርቶ የማለፍ ታሪካዊ አደራና ግዴታ አለባቸው። ይህን መርሳት የለባቸውም የሚለው ወጣት ጌታቸው ኢትዮጵያ በብዝሃነት የደመቀች ሀገር መሆኗ የበርካታ መልካም እድሎች ባለቤት አድርጎ የዚህ ዘመን ወጣት ትውልድ ተገንዝቦ ወደ ውጤት መቀየር ካልቻለ የዚህች ሀገር ተስፋ ማን ሊሆን ነው ሲል ትውልዱን ይጠይቃል።
አቶ ሁሴን ዝናቡ በኦሮሚያ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ የኦሮማራ ጥምረትና ውህደት ወቅታዊ ሳይሆን ታሪካዊና ውልደታዊ ትስስርን የተላበሰ ነው። መነጠል በማይቻል አንድነት የተገመዱ ሰፊ ሕዝቦች ናቸው። ምንም እንኳን አንዳንድ ስርዓቶች ጭቆና ቢያደርሱባቸውም ሳይነጣጠሉ ለእልፍ ዘመናት አብረው ተከባብረውና ተዋድደው የኖሩ ናቸው። ለውጡን ለማምጣት ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል። በመሆኑም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እነዚህ ሁለት ሰፊ ሕዝቦች እንዳይተማመኑ ለማድረግ የሚጥር አካል በሰፊው ቢንቀሳቀስም ተቀናጅተው በጋራ ታግለውታል።
አቶ ሁሴን እንደሚሉት፤ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ለመነጣጠል ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ይስተዋላል። በዚህ ተግባር የተጠመዱት የከሰሩና ጥቅማቸው የቀረባቸው አኩራፊ ባለስልጣናት ሲሆኑ፣ ወጣቱ እነዚህን ሀይሎች አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል፤ምክንያቱም የወጣቶችን ሕይወት የሚያጨልሙና ተስፋ የሚያሳጡ ድርጊቶች በመሆናቸው።
የሀገርን ሰላም በማወክ የወጣቱን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ወጣቱ አንድነቱን በማጠንከር አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል የሚሉት አቶ ሁሴን፤ በመደመር እሳቤ በጋራ ለምንገነባው ሀገር የአማራና ኦሮሞ አንድነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው ከዚህ በሚመነጭ ስጋት ሁለቱን ሕዝቦች ለማጋጨት በተለይም ወጣቱ ላይ ያነጣጠረ የሴራ ትርክት ይነዛል። ይሄን ወጣቱ በትኩረት እየተከታተለ በማክሸፍ አስፈላጊ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ያለፈውን ስርዓት ለመመለስ የሚንደፋደፉትን ሰዓት ያለፈባቸው አካላት የሁለቱን ብሔሮች ግጭት ዋና መጠቀሚያ ለማድረግ ከፍተኛ በጀት ጭምር መድበው ማህበራዊ ሚዲያዎችን የጦርነት ስትራቴጂ ሜዳ በማድረግ ከፍተኛ ውዥንብር ሲፈጥሩ ከርመዋል፤ አሁንም በመፍጠር ላይ ይገኛሉ።
በየትኛውም አካባቢ የሚስተዋሉ የጥፋት ድርጊቶችን ወጣቱ በሰከነ መንገድ ተረጋግቶና አጢኖ ምላሽ መስጠት እንደሚገባው የሚያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ያለፈውን ስርዓት ከመናፈቅ በስተቀር መልሰው ማምጣት እንደማይችሉም አስረግጦ ሊነግራቸው ይገባል። አሁን ሀገሪቱ ለምትከተለው ለውጥ አነሰም በዛ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በመሆኑም የጋራ ቤታችንን የጋራ ሀገራችንን ስም ለማጠልሸትና ሀብትና ንብረት ለማውደም ቀን ከሌት የሚንቀሳቀስ አካል የጋራ ጠላታችን ስለመሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ገልጸው፤ የጋራ ጠላትን በጋራ መክቶ ሀገርን ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ የተጣለበት የሀገሪቱ ወጣት ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
ሙሐመድ ሁሴን