ሁሉም የሰው ልጅ ህሊና የሚባል ሚዛን አብሮት ተፈጥሯል። አምልኮተ ሥርዓቱ ምንም ሆነ ምን፣ የሚከተለው የዕምነት ዘውግ ምስራቃዊም ሆነ ምዕራባዊ ደግም ሆነ ክፉ፣ መራራም ሆነ ጣፋጭ ሰው በመሆኑ ብቻ ይህን መለየት የሚችልበት ህሊና የሚባል መመዘኛ አለው።
ይህንን ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፣ ከላይ በርዕሱ ለማሳየት እንደሞከርኩት ማንም ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ እንደማይወጣ ሁሉ፣ ሁለት እጅ አለኝ ብሎም አንዱን ወደቀኝ ሌላውን ወደግራ አይፅፍበትም። እንዲህ ስል ምንም እንኳን እውቀት የዘለቀው ሰው ቢሆንም በአንድ ጊዜ በሁለት ቋንቋ እያሰበ በሁለት ቋንቋ አይፅፍም። በዚህ ጉዳይ የሚሞግተኝ ካለ ለመከራከር ዝግጁ ነኝ። እንዲያውም አርእስተ ጉዳዬን ስለሚያጠናክርልኝ ገፋበታለሁ። ምክንያቱም ሰው በሚያስብበት ቋንቋ ሲናገር ነው፤ የሚሳካለት እንጂ በሌላ ቋንቋ እያሰበ በሌላው ለመናገር ሲሞክር እንኳን የአረፍተ ነገር አሰካክና ዘይቤው ይፋለስበታል።
ለምሳሌ ያህል፡- በአማርኛ እያሰበ በእንግሊዝኛ ለመናገር የሚሞክር ሰው ምንኛ አሳዛኝ እንደሚሆን ሁለቱን ቋንቋ የሚያውቅ ሰው ያውቀዋል። ምክንያቱም የሁለቱ ቋንቋ የስዋሰው አገባብ ፣ የድምጽ ሥርዓትና፣ ውልድ ቃል ሁሉ የተለያየ ከመሆኑ ሌላ የአንደኛው የቃላት አጠቃቀም ከሌላኛው በአመሰራረቱም የተለየ በመሆኑ ተናጋሪውን በሃሳብ ድህነትና ዝቅጠት ውስጥ ይጥለዋል።
አንድ ጊዜ የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝደንት የነበሩት ሞሐመድ ዚያድ በሬ፣ ከ1969 ዓ.ም የሁለቱ ድንበረተኞች ጦርነት በኋላ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፍለው ሲወጡ፣ ከዓለም ዙሪያ ልዩ ልዩ ጋዜጠኞች ስብሰባውንና የድንበር ግጭቱን አስመልክቶ፣ “የኢትዮ – ሶማሊያውን ጦርነት ማስቀረት አይቻልም ነበር ወይ? እርስዎን ማለትም ሃገርዎን የቀድሞ ወዳጃችሁ፣ ሶቪየት ህብረት የከዳችዎት አይመስልዎትም ወይ? ከስብሰባው ምን ውጤት ይጠብቃሉ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱባቸዋል። በወቅቱ፣ ፕሬዝደንት መሐመድ ፣ ዚያድ ባሬም መልሳቸው “ኢት ዎዝ ዩናኒመስ” የሚል ብቻ ነበረ። በጊዜው የምዕራባውያን ጋዜጠኞች መሳለቂያ ሆነው እንደነበረ ይታወሳል።
በዚህ በኩል የሐገሬ መሪዎች፣ በተለይም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ “በሊግ ኦፍ ኔሽንስ” የኢጣሊያን የግፍ ወረራ አስመልክቶ ሲናገሩ የወቅቱ የሊጉ ቋንቋ በነበረው በእንግሊዝኛ በቅድሚያ መግቢያውን ከተናገሩ በኋላ ይቅርታ ጠይቀው፣ የልባቸውን በሚገልፅላቸው በአማርኛ ነው፤ መናገር የጀመሩት። በዚህ ጊዜም የኢጣሊያን የግፍ ወራሪነት፣ የተጠቀመችውንና በጦርነት የተከለከለውን፣ የመርዝ ጋዝ እንዲሁም ተጋፊነቷን በመግለጽ ወረራውን እንዲያወግዙና ሊጉ፣ በህጉ መሰረት ተገቢውን ድጋፍ ለተወራሪዋ ኢትዮጵያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ከዚያም ሌላ፣ እስከዛሬ የሚወደሱበትን ታሪካዊ ንግግር በወራሪዎቹና በዝምታ በሚመለከተው ዓለም ፊት ያለአንዳች ፍርሃት ተናገሩ። “ ዛሬ የግፍ ተጠቂ የሆነችው ኢትዮጵያ ናት፤ ነገ ደግሞ እናንተ ትሆናላችሁ። ” ሲሉ ታሪክን ከአምላክ ፈራጅነት ጋር አዋህደው እንደ ትንቢት ተናገሩ። ውሎ አላደረም ፤ በ2ኛው ዓመት ላይ ሒትለር ግማሽ አውሮፓን ወረረ። ጣሊያን የጀርመን ግብረ-አበር በመሆን (Axis powers Vs Allied forces) የእርሱ ማህበረተኛ ሆነች። ከዚያም በኋላ በተሳተፉባቸው ስብሰባዎች ሲገኙ ደጋግመው የሚናገሩት በሐገሪቱ የሥራ ቋንቋ በሆነው በአማርኛ ነበረ። ይኼ አንድም የራስን መለያ ለሌላው ዓለም ማሳየት ሲሆን በሌላ በኩል በሚያውቁት ልክና የህሊና ሚዛን መስራትን ያመላክታል።
የዚያድ ባሬን ችግር ሳስበው ሌላ ሳይሆን ከልምድ ማጣቱ በተጨማሪ፣ በሶማሊኛ እያሰቡ በእንግሊዝኛ ለመናገር መሞከራቸው ይመስለኛል።
ወደ ዋነኛው ዓላማዬ ልመልሳችሁና አንድ ሰው ፣ የተሰጠውን የሚዛን ጸጋ በሚገባ መጠቀም ካልቻለ አንድም አውቆ አጥፊ ነው፤ አለዚያም ባለድሑር አእምሮ ነው። እያሰበ የማያልም፤ እያቀደ የማይፈጽም ፣ ነው። ለዚህ ነው፤ ከላይ ህሊና ስለተባለው ሚዛን አበክሬ ያነሳሁት። ማንም ሰው ህሙም ካልሆነ በስተቀር በአንድ ጊዜ ወዳጅም ጠላትም ፣ አወዳሽም ነቃፊም፣ ደግም ክፉም፣ ጀግናም ፈሪም፤ ርህሩህም መሰሪም ሊሆን አይችልም።
የህሊና ሚዛን ፣ ሲጠይቅ፣ የሆነብኝ ከሆነልኝ በላይ ነው፤ ወይስ አይደለም? ክፋት ከደግነት፣ ለጋስነት ከንፍገት፤ ምህረት ከፍርድ ይሻላልን ? ብሎ መበየን የሚያስችል ፀጋን ለሰው የሚያጎናጽፍ ነው። በህሊና ዳኝነት ሰውን ደግ ስላደረገልኝ ብቻ ሳይሆን ክፉም ቢያደርግብኝ አልከፋበትም፤ ሲል ውሳኔን የሚሰጥ ባለጸጋነት አለው።
እርግጥ ነው፤ በህይወት አጋጣሚ በኑሮ ውጣ ውረድ የሚያጋጥመን የባህሪ መዋዥቅ በማንም ሰው ላይ ሊያጋጥም ይችላል። አፄ ቴዎድሮስ፣ ሃገሪቱን አንድ ለማድረግ በተነሱበት ጊዜ አጥብቆ የሚያዘውን ከመያዝ፣ የሚቀርበውን ከማቅረብ ይልቅ ማራቅ መረጡና በሴራ ጉንጉን ነገራቸው እየተጠላለፈ ይመጣባቸው ነበረ። በኋላ ግን፣ ባለፈው ሳምንት ባኮረፉበት ነገር በዚህኛው ሳምንት በኩርፊያቸው መቀጠል አቆሙና፣ በፍትህ ጉባኤ መቀመጥን መረጡ፤ ሊያለዝቡትም ሞከሩ።
እየያዙ መልቀቅ፣ እያሸሹ ማቅረብ የመሪ ባህሪ ቢሆን አይደንቅም። ለጋሻ ጃግሬ ግን (ለአጃቢና ቅርብ ሰው) የሚመከር ባህሪ አይደለም። ታማኝና ትጉህ ፣ መካሪና ገሳጭ፣ ትሁትና ጽኑ መሆን ይጠበቃል። ስለአፄ ቴዎድሮስ የጻፉት የውጭ ፀሐፍት እነ ራሳምና ሔንሪ ብላንክ፣ የገብርዬን ቅርብነት፣ የተዋበችን ተሰሚነት( ሚስታቸውን ) አለዛቢነት፣ አክባሪነትና ፍጹም ትህትና ጽፈዋል።
በሌላ በኩል ቴዎድሮስ ህዝቡ አልገዛ ሲላቸው፣ ድብረታቦርን ሰራዊታቸው እንዲያነድድ አዝዘው ምናልባት ክፉ መንፈሳቸው አብሮ ቢቃጠልልኝ መልካም ነበር፤ ሲሉ ይደመጣሉ። የዚያኔውን ትንሹን ልጅ ምኒልክን ማርከው አስረዋቸዋል። እንዲህ ስል፣ “ደግ አደረጉ” ማለቴ እንዳልሆነ ማሰብ ከስህተት መደምደሚያ ያድናል። ቴዎድሮስ እንደተሳሉበት ጭካኔ፣ ጨካኝ ብቻ አልነበሩም ፤ ማለቴ ነው እንጂ። እንዲያውም፣ ምኒልክ በምርኮ በእርሳቸው ዘንድ በነበሩ ጊዜ የአመራር ጥበብን ሳይማሩ እንዳልቀረ እገምታለሁ። በተለይም በአመዛኙ ጭካኔ ከተሞላው የአገዛዝ ዘይቤ፣ ይልቅ በአግባቢ ዲፕሎማሲ ሃገርን መምራት እንደ ቴዎድሮስ በአጭር የአመራር ዘመን ከመገደብ ያድናል፤ ብለው እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም ።
እዚህ ላይ፣ ይህንን የታሪካችንን ገጽ ያነሳሁት አንድ መሪ ጨከን የሚል ብቻ አይደለም ፤ ርህሩህም ነው፤ ቀጪ ብቻ አይደለም፤ መሐሪም ነው፤ አስፈሪ ብቻ አይደለም ፤ ተወዳጅም ነው፤ ለማለት ነው። ይሁንናም ለሁሉም ነገር ከአገዛዝ አዋጅና ፍትሐ ነገስት ይልቅ ፣ የህሊና ሚዛን የሚባለው ህገ-ልቦና ለሰው ተሰጥቷልና ፤ በዚህም ይመራሉ።
እዚህ ላይ አንድ ታሪክ ላውሳችሁ። ቴዎድሮስ አንድ ጊዜ በቀሳውስቱ ሥራ መፍታት ያዝኑና፣ አዲስ የቤተ-ክህነት አደረጃጀትና የአሰራር ውሳኔያቸውን ያሳውቃሉ። በኋላም፣ አቡነ ሰላማ (የወቅቱ አቡን) “ንጉስ ሆይ፣ ይሄ በቤተ- ክርስቲያን አደረጃጀት ሊሰራ የሚገባው አይደለም፤ ፍትሐ- ነገስቱም አያዝዝም” ይሏቸዋል። ንጉሱም መልካም እንግዲህ፣ ሸንጎው ይፈርድብናል፤ ይሉና፣ የሊቃውንት ጉባኤ ተጠርቶ ጉባኤ ይቀመጣሉ። ቴዎድሮስ ግእዝ አይችሉምና፣ ፍትሐ ነገስቱ በዚህ ጉዳይ ምንድነው? የሚለው ሲሉ ከአንባቢው ለተርጓሚው፣ ይጠይቃሉ። አንደኛው ቄስ ያነብባል፤ ሌላኛው ወደአማርኛ አስማምተው ይተረጉማሉ። ከሰሙ በኋላም ትርጉም ወደእርሳቸው ፍላጎት አለመዝመሙን ሲያውቁ፣ ተናድደው፣ “አንድሽ አንባቢ፣ አንድሽ ተርጓሚ “ ሆነሽ ተጫወቺብኝ እንጂ፤ ብለው መቆጨታቸው ይነገራል። ይህንን ቢሉም ሃሳባቸውን ግን ተቀብለዋቸው ፈጽመዋል።
ስለአፄ ቴዎድሮስ ካነሳሁ አንድ ዘና የሚያደርግ ቁምነገራም የክስ ገጠመኝ ልንገራችሁ።
በእርሳቸው የአገዛዝ ዘመን አንድ ሌባ በአንድ ባላገር በረት ገብቶ ከብት ሊነዳ ሲሞክር፣ ባለቤቱ ይወጣና “ማነህ!” ሲል እንደተነቃበት ያወቀው ሌባ ከበረት ዘሎ ይሮጣል። አሳዳጅ ጦሩን ይዞ እንደተከተለው ያየው ሌባም ክፉኛ ይሮጥና ከአይኑ ይርቃል፤ በዚህ ጊዜ እንደማይደርስበት ያወቀው ባላገር፣ “በህግ አምላክ! በቴዎድሮስ ይዤሃለሁ!” ሲለው ሌባው ቆመ። በቆመበትም ስፍራ ጦሩን አምዘግዝጎ ይወጋውና፣ ጠዋት ለዳኛ ይዞት ይቀርባል።
በአጋጣሚ በዚያ መንደር የንጉስ አጀብ ሲያልፍ ነበርና፣ ሌባውም፣ የመጣው ይምጣ ብሎ፣ “ንጉስ ሆይ ይዳኙኝ ፤” ሲል፣ ይጮሃል። እሳቸውም ከፈረሳቸው ወርደው፣ ጉዳዩን ይጠይቃሉ። ታሪኩን ከተረዱ በኋላም ፤ ቆስሎና በቁራኛ የቆመውን ሌባ፣ ያስፈቱና ቁራኛውን በእጃቸው አስገብተው ፣ ሊያመልጥ ይችል የነበረው ሌባ፤” በህግ አምላክ – በቴዎድሮስ አምላክ ፤” ተብሎ ሲቆም መውጋት፣ በተሸነፈ ጠላት ላይ መታበይ፣ አይሆንም ወይ? ጌቶቼ ሆይ፣ ‘ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል ወይ’ ሳትሉ፣ ፍረዱኝ የተወጋው ሌባዬ ነው፣ ወይስ ? በስሜ የቆመው ህጉ ነው፤ ይላሉ። ጥብቅናውን የቆሙለት ሌባ መቼም ‘ሺህ ዓመት ንገስ፤ ቴዎድሮስ’ ሳይል አይቀርም። ዳኞቹም ጉባኤ ይቀመጡና ግራና ቀኙን ካዳመጡ በኋላ፣ ፍርዳቸውን ያሰማሉ።
በብይናቸውም ለህግ አክባሪው ተከ ሳሽ፣ ከሳሽ፣ እስኪድን ድረስ ሰውነቱን እንዲጠግነውና ካሳም እንዲሆነው አንድ ወይፈን ከጥገት ጋር እንዲሰጥና ጥፋተኛው ካገገመ በኋላ ለጥፋቱ ብይን እንሰጣለን ሲሉ፣ ይበይኑበታል። ቴዎድሮስም ሌባዬ ያለቅጣት ማምለጥ ሲችል ቆሞ ለህግ እጁን ሰጥቷልና፣ ማሩልኝ ሲሉ ዳኞችን ጠየቁ ፤ ይባላል። እንዲህም የሚመዝን ዳኝነት፣ እንዲህም የሚፈርድ ህሊና፣ እንዲህም አንጥሮ የሚያይ አስተዋይነት አለባቸው። ሌባውን ግን ሳይወቅሱት አላለፉም ይላል፤ መዋዕለ ታሪካቸው።
እንደገና ወደ ቀደመው ነገሬ ልመልሳችሁና ፤ ህሊና የተባለው ሚዛን ለሁሉም ሰው ተሰጥቷልና፤ ማንም በሌላው ላይም ሆነ በራሱ ላይ ሊያደረግ የሚገባውን ለማድረግ ሚዛናዊ ሊሆን ይገባዋል እንጂ፤ መሰሪም ቀናም፣ ጠርጣሪም አማኝም እየሆነ ሊያከናውን አይገባውም።
የሰው ልጅ ብቻውን ሲሆን የማያምነው ምን እውነት ይኖረዋል። ምክንያቱም ህሊናው እንዲህ ይለዋል፤ ቅድም በሰውየው ፊት ያሳየኸው ባህሪ ማስመሰል አልነበረበትምን? ያን ያህልስ ልታንቆላጵሰው ይገባ ነበርን? ስለእርሱ በሰዎች ፊት የማትመሰክርለትን ማንነት በራሱ ፊት አላሳየኸውምን? ለምን የልብህንስ ሃሳብ፣ ቅያሜህንና ቅሬታህን አልተናገርከውም? ሲል ይሞግትሃል። በሰው ፊት ስንሆንማ የምንፈራውን ሰው እንዳፈራለን፤ የምንጠላውን ሰው ወዳጅ እንመስላለን ፤ ይህንን ክፉ ባህሪያችንን ግን የምናምነው ለራሳችን ነው፤ ግብዝነታችንን የምንናዘዘው ለነፍሳችን ብቻ ነው።
እውነተኛና ትሁት ፣ ባለህሊና ሰው የሚወደውን ሰው እንደሚረዳ ሁሉ ፤ የሚጠላውንም ይረዳል። ለሚወደው ሰው እንደሚያበድር እንዲሁ ለሚጠላውም ሰው ያበድራል፤ የሚወደውን ሰው እንደተዋሰው የሚጠላውንም ሰው ይዋሰዋል፤ የሚወደውን ሰው መልካም እንደነገረው ሁሉ ለሚጠላውም ሰው ያንኑ መልካሙን ነገር ይነግረዋል። ህሊና የማያዳላ ዳኛ ነው፤ ፍርድን ለሚገባው ሰው የሚፈረድበት የራስ ችሎት አደባባይ ህሊና ነው። ልብ በሉ፤ ጥላቻ፣ የጠይው እንጂ የባለህሊናው ሰው አይደለም። ህሊና ያለው ሰውማ ሰውን አይጠላም ።
አደራ ተቀብለህ መብላትህን ከባላደራው የበለጠ ራሱ ህሊናህ ይነግርህ የለ? ኪዳን ገብተህ መካድህን ከመሐላ አስፈጻሚው የበለጠ ህሊናህ ይነግርህ የለ? ግን ላደርከው ክህደት መዓት የማስፈፀሚያ ሰበባ-ሰበቦች፣ ስትደረድር ህሊናህ እንዲህ ይልሃል፤ “ኧረ፣ ተው አንተ ሰው ፤ ኧረ ተው አንተ ምስኪን፣ ያደረግከውንም እኔና አንተ እናውቃለን!” ሲል ያሳስብሃል ። ህሊናዬ እንዲህ አይለኝም የሚል ካለ፤ አንድም ህሊናውን የካደ ካለዚያም ያሸለበበት ነው።
ከዶክተር ምህረት ደበበ አባባል ልዋስና “ ጤናማ ሰው ሲቸግረው ንብረቱን ጥሪቱን፣ ቅርሱንና ውርሱን አለፍም ሲል ኩላሊቱን ሊሸጥ ይችላል፤ ህሊናውን ከሸጠ ግን አለቅጥ ቸግሮታል/ወይም ችግሩ አሳምሞታል። (ሰረዝ የኔ ነው)” ይላል ፤ ይኼ ለሁላችንም የሚሰራ፣ ልናስብበት የሚገባና ሳይሞቀን አራግቡልን፤ ሳይበርደን ደርቡልን የሚያስብል ማንነት የሚፈጥር ግለ-ክህደት ነው። ሰዎች ተርበው ስለጥጋባቸው፤ ተሰድደው ስለመረጋጋታቸው፣ ታውከው ስለሰላማቸው መናገር የሚቃጣው ማንነት፣ የተሸጠ ህሊና ውጤት ካልሆነ ሰው በጤናው እንዲህ አይሆንም።
ይህንን ወደ ግለሰብ ደረጃ ስታመጡት ተመሳሳይ እውነት አለው። በባል ስካር ሰላሟ የተናጋን ሚስት ጎረቤቷ ፣” ማታ ማታ በጸባችሁ ሰላማችን ተናጋ እኮ፣ ምናል ባለቤትሽን ተው ብትይው” ስትላት፣ ተቆጥታ “ብንሰክር በቤታችን ብንረብሽ በራሳችን፣ ምናችሁን ነካን…?” የምትል ሚስት፣ በማለዳ ተነስታ ነጠላዋን ለብሳ ቤተክርስቲያን ስትሄድ ያየ ጎረቤት፣ “ከባሌ ስካር አስጥለኝ” ለማለት ነው? ወይስ “በነጋታው ከትናንቱ የበለጠ ሰፈሩን የሚበጠብጥበት የስካር ጉልበት ስጥልኝ”፤ ለማለት ካልሆነም” ‘ባሌን ረበሸን’ የሚሉትን፣ የጎረቤቶቼን ጆሮ፣ ድፈንልኝ” ለማለት ነው፤ የምትሄደው ያስብላል። ይኼ ረብሻውን የራስ ማድረጊያ ዘዴ፣ በራስ ግቢ እንጂ በተከራዩበት ቤት ሲሆን ያስመርራል። እንዲህ ዓይነት ከህሊናቸው ያልታረቁ ሰዎች ሲኖሩ ደግሞ እያለቀሱ ሳቅ ፤ እየታመኑ መስረቅ ፣ ይቻል ይሆን ያስብላል።
መልካም ሳምንት ይሁንልን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ