‹‹የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎችና የግቢ ደህንነት አጠባበቅ ስርዓት በተማሪዎች፣ በወላጆችና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚገባ የኃላፊነት መውሰጃ ውል›› የተሰኘው ይህ ሰነድ የትምህርት ጊዜ እንዳይስተጓጎልና ሰላማዊ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን ተማሪዎች፣ወላጆችና የዩኒቨርሲተው ማህበረሰብ በጋራ ይፈርሙበታል። በመሆኑም የሰነዱን ይዘት ከዓላማው አንፃር እንዴት ይመለከቱታል? ስንል ተማሪዎችን፣ወላጆችንና አስተማሪዎችን አነጋግረናል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመማር ላይ የሚገኘው ተማሪ ታደለ የሻነው እንደሚለው፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎቻችን ተመርዘዋል። ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ንጹህ አዕምሮ ይዞ ለመማር የገባ ተማሪ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አላማውን ረስቶት ታገኘዋለህ። ከአስተማሪ እስከ ተማሪ፣ከኃላፊ እስከ ተራ ጥበቃ ድረስ የእኔ የሚለውን ለመጥቀም፣ከእኔ ወገን አይደለም የሚለውን ደግሞ ለመጉዳት እና በመካከላቸው ልዩነት በመፍጠር በጥሩ አይን እንዳይተያዩ ለማድረግ የሚማስን ተራ ሰው ሞልቷል ሲል ሃሳቡን ይሰነዝራል።
‹‹ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያዊ ወንድምና እህት መሆናችን እንዲያስተሳስረን፣እንድንተዛዘን፣የጋራ ቤታችንን እንዳናፈርስ፣ስግብግብነታችንን እንድንረሳ በሚያደርግ አስተሳሰብ መቃኘት ብንችል ምንኛ ጥሩ ነበር። ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው የዘረኝነት በሽታ ምን አልባት ግንፍል እያለ መታየቱ ካልሆነ በስተቀር ከውጪ በማህበረሰቡ ውስጥ ሥር የሰደደ ችግር ነው፡፡›› ሲል ተማሪ ታደለ ይናገራል፡፡
ስለዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪውን ብቻ በመቆጣጠር ለውጥ የሚመጣ አይመስልም። በየትኛውም አካባቢ የሕግ የበላይነት በፍትሃዊ መንገድ መከበር አለበት። ቤተሰቦች ከውጪ በሰላም መኖር ሲችሉ በትምህርት ቤት ማህበረሰብ ዘንድም ሰላም ይፈጠራል። ነገር ግን አሁን የወጣው መመሪያ ሳይወጣ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀሉን ያስታውሳል።
ውሉ በመዘጋጀቱ ከማንም በላይ ደስተኛ ነኝ የሚለው ተማሪው በሰላም ተምሮ ለመመረቅ ያለን ጉጉት ከፍተኛ በመሆኑ ይህን እውን ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው ብሏል። ‹‹እህት ወንድሞቼ እና እናት አባቴ ሕይወታቸው ሰላምና ደስተኛ እንዲሆን እኔ ይሄን ግዴታ መወጣት ይጠበቅብኛል። ተማሪውም ይሄን መፈረሙ ቢያንስ በሚሰራው ድርጊት ሁሌም ቤተሰቡ ጭምር እንዳለበት ማሰብ እንዲችል የሚያደርግ ይመስለኛል፤›› ብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አዲስ አስተሳሰብ መፍጠር አለበት። የሰለጠነ አዕምሮ እንዳለው ሰው ማሰብ ይኖርበታል። ከትምህርት ውጪ ሌላ ምንም አይነት እንቅስቃሴና ተግባር በግቢ ውስጥ መፈጸም የለበትም። ለመመሪያው ተፈጻሚነት ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በጋራ መስራት አለበት ሲል አሳስቧል።
‹‹በዚህ ጊዜ ልጅን ዩኒቨርሲቲ ልኮ ማስመረቅ አርግዞ ከመውለድ የበለጠ ጭንቀት ያስይዛል፤ ተመርቆ እስኪወጣ ድረስ ወገቤን በመቀነቴ አስሬ ሳስብ እኖራለሁ። አስተምሮ እዚያ ማድረስ አለም ይመስለኝ ነበር። በየቀኑ ችግር ተፈጠረ በተባለ ቁጥር በቁሜ ሰቀቀን ይጨርሰኛል። ሥጋዬን የጨረስኩት በእሱ ነው›› ያሉት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ልጃቸውን ልከው የሚያስተምሩት ወይዘሮ እማሙ ኡመር ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ‹‹ይሄ አሰራር ችግር መፈጠሩን ያስቀረው ብለህ ነው? ምን ያድርግ መንግስትም ቢቸግረው ነው ማስፈረሙ። አገራችንን ሰላም ያድርግልን። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለሥራ በተመደቡበት አካባቢም ቢሆን የሚያስተማምን ጊዜ ባለመሆኑ ቤተሰብ መጨነቁ አልቀረለትም። የቤተሰብን ችግር እንዲያቃልሉ ነበር ማስተማራችን። አሁን ግን የእነሱ እዳ ባሰን። ከዚህ አልፎ አስክሬን ሲመጣለት ወላጅ የሚሆነውን አለማሰብ ይሻላል። አሁን መመሪያው መዘጋጀቱ ጥሩ ሆኖ በተግባር ልጆቻችን በሰላም ሲማሩ ስናይ ደግሞ የበለጠ ብናመሰግነው የተሻለ ነው። አላማው ግን ጥሩ ነው›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪው ዶክተር መሐመድ አደም በበኩላቸው፣ ‹‹ይሄ መመሪያ አንድ ርምጃ ሊያሻግር ይችላል። ጅምሩ ሊበረታታ ይገባል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ቁመናቸው ተፈትሾ ሊስተካከል ግድ ነው። በእውቀት እና በችሎታ ሳይሆን በኮታና በሰፈር፣በብሔር አጥር ተለክተው የተሰሩ እስከመሆን ደርሰዋል ይላሉ። ትምህርት የተሻለ ሀገር ሄዶ ለመማር፣የተሻለ ጥቅም ለማግኘት፣የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ለመሆን፣በሰራተኛነት ለመቀጠር ብቻ ለራሱ ጥቅም ሲል ሰው ማንነቱን ያልሸጠ ማግኘት ይቸግራል፡፡
እነዚህ አስጸያፊ ባህሪያትን መላበስ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ማስነወራቸው ቀርቷል። ሰው ልሁን ብሎ የተፈጠረ ይመስል በማንነቱ ምክንያት ብዙ ነገሩን እንዲያጣ ሲደረግ ኖሯል። የዚህ የለውጥ ሂደት በዩኒቨርሲቲዎች መጀመሩ እኔ አሁንም ትውልድን ለማዳን አልመሸም ባይ ነኝ። ወላጆች፣ተማሪዎችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ መፈራረሙ ከችግሩ ስፋት አኳያ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ያመጣል ብሎ ለማሰብ ቢቸግርም በረዥም ጊዜ እና በሂደት ግን መፍትሄ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
አሁን እየመጡ ያሉ የለውጡ አካል የሆኑ አሰራሮች በመማር ማስተማሩ ላይ የሚፈጥሩት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ዘርፈ ብዙ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኘው አመራር እና አስተማሪ ቀና አስተሳሰብ ካለው ተማሪው ጥፋትን ከየት ይማረዋል? ስለዚህ ቁጥር አንድ መስተካከል የሚገባቸው እነዚህ አካላት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ምሁር በሚባል ስም የተሰባሰቡ አረሞች ብዙ ናቸው። አሁን የሚታረሙበትና አደብ የሚገዙበት ወቅት የደረሰ ይመስለኛል። ራሳቸውን የቻሉና ከ18 አመት በላይ የሆናቸው ልጆች በሚያጠፉት ጥፋት ከሩቅ የሚኖረው ወላጅ ለምን ይጠየቃል? በሕግ አግባብስ የሚያስኬድ ነው? በማለት ለሚያነሱ አካላት የሕግ እውቀቱ ባይኖረኝም በእኛ ጥቂት ተሳትፎ ሀገራችን ከጥፋት መዳን ከቻለች፣ በእኛ መጠነኛ አስተዋጽኦ ትውልድ መዳን ከቻለ እና ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር እስከቻልን ድረስ ከመጠየቅ ያለፈ ኃላፊነት ተሸክሞ ለውጡን ለማገዝ ዝግጁ ልንሆን ይገባል የሚለው የመምህሩ መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ሙሐመድ ሁሴን