«ለጋሽ ነኝ» ኮንሰርት ተካሄደ
በሐበሻ ዊክሊ አስተባባሪነት ትናንት መስከረም 17 በሞዛይክ ሆቴል የተዘጋጀው «ለጋሽ ነኝ» ኮንሰርት ለሙዚቀኛ ሙሉቀን ታከለ የህክምና ወጪ የሚሆን ገቢ የማሰባሰቢያ ፕሮግራም ነው:: የመግቢያ ዋጋው መደበኛ 300 ብር፣ ቪአይፒ 500 ብር እንደነበረም ሰምተናል::
በተሸንፌያለሁ አልበም ሥራው ታዋቂነትን ያገኘው ሙዚቀኛ ሙሉቀን፤ በኩላሊት ህመም ተይዞ በህክምና እየተረዳ ሲሆን፤ ከአገር ውጭ ሄዶ የማይታከም ከሆነ ችግሩ እንደሚባባስ ታውቋል:: ስለሆነም ለህክምና በቅርቡ ወደ ሕንድ ይጓዛልና ይህንን ወጪውን ለመሸፈን ሲባል የሥራ ባልደረቦቹ የሙዚቃ ዝግጅቱን አድርገዋል:: በዚህም ብዙ ገንዘብ ይገኝለታል ተብሎ ታምኗል::
ብሌን የኪነጥበብ ምሽት ከነገ በስቲያ ይጠብቁ
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ያዘጋጀው ብሌን የኪነጥበብ ምሽት ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ለአስረኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ‹‹የዘመን ቀለማት›› በሚል ርዕስ ጉዳይ ተግባራዊ ይደረጋል:: በቦታው ላይ ታላላቅ ጸሐፍት የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ዲስኩር ለማቅረብ ዶክተር ምህረት ደበበ፣ መዋዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት እና ኢንጂነር ጸደቀ ይሁኔ የሚገኙ ይሆናል መባሉን ሰምተናል::
የተለያዩ ገጣሚያን ማለትም እንደ እነ አበረ አያሌው፣ በቃሉ ሙሉ፣ ልዑል ኃይሌ፣ ማህሌት አፈወርቅ የሚቀርብ ሲሆን፤ ኮሜዲያን አዝመራው ሙሉሰውም በሚገባ ታዳሚውን ያዝናናዋል ተብሏል:: ምሽቱን ለመሳተፍ የምትፈልጉ በብሔራዊ ቴአትር ከምሽቱ 11 ሰዓት ላይ የምትወዱትን እየጋበዛችሁ በነፃ መታደም የምትችሉ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል::
ኦዳ አዋርድ ጥቅምት ሰባት ይካሄዳል
2009 ዓ.ም በጋዜጠኛ በሻቱ ቶለማርያም አዘጋጅነት የተጀመረው ኦዳ አዋርድ ካለፉት ሁለት ውድድሮች የተሻለ ሆኖ በመጪው ጥቅምት 7/2012 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሰምተናል::
በዚህ ዓመት በሙዚቃ፣ ፊልም እና መጽሐፍት ድርሰት፤ የተካተቱ ሲሆን ዘርፎቹም 18 ደርሰዋል:: ለሽልማት የሚበቁት ዕጩ ሥራዎች በአጠቃላይ በ2011 ዓ.ም የተሰሩት ብቻ ይሆናሉ ተብሏልም::
በተጨማሪም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለአንድ ሙያተኛ የሕይወት ዘመን የሽልማት ማዕረግ ይሰጣል መባሉን ሰምተናል::
የሽልማት ዘርፎቹ ደግሞ በሙዚቃ ዘርፍ:- የዓመቱ ምርጥ አልበም፣ የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ የዓመቱ ምርጥ ቪድዮ ክሊፕ፣ የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዓመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፣ የዓመቱ ምርጥ ሴት ድምፃዊ፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ጥምረት፣ የዓመቱ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብሎ የሚሸለሙ ሲሆን፤ በፊልም ዘርፍ፡- የዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተዋንያን፣ የዓመቱ ምርጥ ሴት ተዋንያን
የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር፣ የዓመቱ ምርጥ ደራሲ፣ የዓመቱ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር፣ የዓመቱ ምርጥ ኤዲተር ተብሎ ሽልማቱ ይበረከታል:: በተመሳሳይ በመጽሐፍ ዘርፍ፡- የዓመቱ ምርጥ ልብ-ወለድ መጽሐፍ፣ የዓመቱ ምርጥ የግጥም መድብል፣ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ይሆናሉ::
ዳንኤል ጥላሁን ገሰሰ ‹‹ሰው›› የተሰኘ አዲስ አልበሙን ለቀቀ
የአንጋፋውና የሙዚቃ ንጉሡ ጥላሁን ገሰሰ ልጅ ዳንኤል ጥላሁን ‹‹ሰው›› የተሰኘውን አልበም መስከረም 15 ሐሙስ ምሽቱ 1 ሰዓት 30 ላይ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ሜትሮ ክለብ በደማቁ ተመርቋል:: በወቅቱ በርካታ ሙዚቀኞች፣ ገጣሚያንና የሙዚቃ አድናቂዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሙዚቃውን ንጉሥ የጥላሁን ገሠሠ 79ኛ ዓመት የልደት በዓል የታሰበበት እንደነበር ሰምተናል:: ዝግጅቱን ያደመቀው ደግሞ ኤክስፕረስ ባንድ መሆኑን ሰምተናል::
‹የምድር ዘላለም›› የግጥም ስብስብ ገበያ ላይ ዋለ
በገጣሚ ዲበኩሉ ጌታ (ያለው አዛናው) የተጻፈ ‹‹የምድር ዘላለም›› የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ በገበያ ላይ ውሏል:: የግጥም ስብስቡ ለገጣሚው የመጀመሪያ መጽሐፉ ሲሆን ገጣሚው በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ሥራዎቹን ያቀርብ ነበር::
‹‹የምድር ዘላለም›› የግጥም መድብል በ202 ገጾች የተጻፈ ሲሆን 119 ግጥሞችን ይዟል:: መጽሑፉ በ125 ብር ይሸጣል:: በሜክሲኮ ቡክ ኮርነር፣ ጃፋር መጻሕፍት መደብር (ለገሃር) እና ጌታቸው መጻሕፍት መደብር (ፒያሳ) መጽሐፉ የሚገኝባቸው መደብሮች ናቸው::
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012 ዓ.ም