ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? ሰላም ናችሁ? አዲሱ ዓመት እንደተስማማችሁ እገምታለሁ። የመስቀል በዓልስ እንዴት ነበር? መስቀል በሀገራችን ከሚከበሩ በዓሎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። ይህ በዓል በተለያየ ቦታ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት ተከብሮ ውሏል። በዓሉ የአደባባይ በዓል በመሆኑም በተለይ በዋዜማው ደመራ ተደምሮ በልዩ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ነው የተከበረው። በየዓመቱ መስከረም አስራ ሰባት ቀን የመስቀል በዓል በመላ ሀገሪቱ ይከበራል።
ዛሬ የማቀርብላችሁ ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተጉዤ የተመለከትኩትንና ከመስቀል በዓል ለየት ያለ ነው። በዓሉ ያሆዴ ይባላል። የሀድያ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። ይሄንን ሳስነብባችሁ እንደምትደሰቱም አልጠራጠርም።
ሀገራችን በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓልን መስከረም አንድ ታከብራለች። አሮጌውን ዓመት አልፎ አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ ተቀብላ ለስኬትና ለሰላም ሽርጉድ እያለች ነው። ከዚህ የዘመን መለወጫ አቆጣጠር ለየት ያለ አቆጣጠር ያላቸው ብሔረሰቦች ደግሞ በደቡብ ክልል አሉ። ከዚህም መካከል ሀዲያ አንዱ ነው። በሀዲያ ብሔር ማንኛውም ነገር አንድ ተብሎ የሚቆጠረውና የራሳቸውን የዘመን መለወጫ በዓል መሠረት በማድረግ ነው። ማለትም ከመስቀል ጀምሮ። ኧረ ለመሆኑ ይህ በዓል መጠሪያው ምንድን ነው ታውቁታላችሁ? እሺ ልንገራችሁ “ያሆዴ መስቀላ” በመባል ይታወቃል።
እስኪ ስለ ሀዲያ ካነበብኩትና ከሰማሁት እንዲሁም ከታዘብኩት መካከል አንዳንድ ነገር ልንገራችሁ። ሀዲያ ከአዲስ አበባ በ244 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። እንዲሁም በ13 ወረዳዎችና በ4 የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረች የጥንታዊት የሕዝቦች መኖሪያ ናት። ተፈጥሯዊ ውበቷ ሳቢና ማራኪ ነው። የሀዲያ ሕዝብ የራሱ የሆነ ባህል፣ ቋንቋ፣ የአለባበስ ሥርዓት አለው። መልከዓ ምድሩ አረንጓዴ በመሆኗ ለግብርና አመቺ ሲሆን እንሰት በሀዲያ ሕዝብ በጣም ተፈላጊ ነው። የእንሰት ተዋፅኦ የሌለበት ምግብ አይሰራም። ታዲያ እንሰት ለሀዲያዎች ሕይወት ነው ቢባል ይበዛበታል? አይበዛበትም። ሀዲያ ከእንሰት ምርቷ በተጨማሪም በስንዴ ምርት ታዋቂ ናት። የብዙ ጀግና መፍለቂያም ጭምር እንደሆነች ይነገራል።
አሁን ደግሞ ያሆዴ መስቀላ የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ላጫውታችሁ። ያሆዴ በሀዲያ ብሔር የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ፣ ሕዝቦቿ ለአዲስ ዓመት አዲስ እቅድ የሚያቅዱበትና የሰላም ማብሰሪያ ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ በዓል ዘመድ አዝማድ ከሩቅ ተጠራርቶ የሚጠያየቅበትና የተጣሉም በፍፁም ሳይታረቁ የዘመን መለወጫን የማይሻገሩበት በዓል ነው። ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ለሀዲያ ሕዝብ ተስፋው የሚለመልምበት በፍቅር አንድ ሆኖ ለዕድገት የሚሰራበት ነው። ታዲያ በያሆዴ ምሽት ወጣት ልጆች ጦምቦራ (ችቦ) እና ሌሎችን ቁሶችን በመያዝ በየሰፈሩ ‹‹ያሆዴ ያሆዴ እና ኦሌ ኦሌ›› በማለት ይጫወታሉ።
በዚህ ጭፈራ የመጨፈር ችሎታ ያላቸውና ፍቃደኛ የሆኑ ልጆች ተመራርጠው ጭፈራውን ይመራሉ። ያስተባብራሉ። እንዲህም እያሉ ይጨፍራሉ።
ያሆዴ ያሆዴ………………..…..ሆይ ያሆ
ያሆዴ ያሆዴ……….…….……..ሆይ ያሆ
ህንቾ ሁንዳ መስቀላ…………ሆይ ያሆ
ሁንዲ አፉኮዮ………………….ሆይ ያሆ
ዶሚኒሴ ሀቃ ጉሎ….………..ሆይ ያሆ
ዳጂንሴ ዋኦ ጉሎ………….….ሆይ ያሆ
ዳቦሪ ገቲሲ… ……………….…ሆይ ያሆ
ኡዋኮኢ ብራ……………….…ሆይ ያሆ
እየና ኬማቴ……………………….. ሆይ ያሆ
ኡንጄና ዲነቴ… ……………….….ሆይ ያሆ
አባ እያንቾ……………………..…….ሆይ ያሆ
አቼ እዩሚቼ… …………………..….ሆይ ያሆ
አንቶኦ ሙንቶኦ……….………….. ሆይ ያሆ
መሎም ቤይዱታ……………….…. ሆይ ያሆ
ኡዊቶ ሉዋ ኡዊታ ሆሬ………….. ሆይ ያሆ
እያሉ ይጨፍራሉ። ዘመን መለወጫቸውንም በደስታ ያሳልፋሉ። በዚህ ዓመትም ባሳለፍነው ሳምንት በደመቀ ሁኔታ በሆሳዕና ከተማ አክብረዋል። በየቤቱ እየዞሩም የቤቱን አባወራና እማወራ የቤተሰቡን አባላት በሙሉ እያወዳደሱ ይጫወታሉ። የሚጨፍሩት በጨለማ በመሆኑ ጦምቦራ በመያዝ ይንቀሳቀሳሉ። ለጭፈራ የሚሄዱበት ቤት በር ሲከፈትላቸው ከዚህ ቤት ችግርና ርሀብ ይውጣ፤ መልካም ነገር ይግባ እያሉ ጭፈራቸውን ማድመቅ ይጀምራሉ። ከጨፈሩም በኋላ የቤቱ አባወራ እረፍት እንዲወስዱ ይፈቅድላቸውና ለበዓሉ ተብሎ የሚዘጋቸውን የሀዲያ ጣፋጭ ባህላዊ ምግብ የሆነውን አተካና እንዲመገቡ ይሰጣቸዋል። እንደ አባወራው ሀብት ብርም ይቸራቸዋል። ልጆች የተሰጣቸውን አተካና ተመግበው ከጨረሱ በኋላም የቤቱን አባላት በሙሉ «ከዓመት ዓመት ድረሱ፤ አትለያዩ፤ ድሃ አትሁኑ፤ ዕድሜያችሁ ይርዘም» ብለው ጨዋታቸውን በምርቃት ይዘጋሉ።
ልጆች! አሁን ደግሞ ስለ ያሆዴ የዘመን መለወጫ በዓል የልጆች ሚና ምንድን ነው የሚሉትንና ያሆዴ ሲመጣ የሚሰማቸውን ስሜት ያነጋገርኳቸው ልጆች ሀሳባቸውን እንደሚከተለው አካፍለውናል። በመጀመሪያ ሀሳቧን ያካፈለችን ተማሪ ናርዶስ ደሞዜ ትባላለች። የምትማረው በኤቨረስት አካዳሚ ሲሆን የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ወደፊት የህክምና ዶክተር በመሆን ህሙማንን ለመርዳት ታስባለች። አሁንም ደስተኛ ሆና ትምህርቷን እየተከታተለች ነው። ያሆዴ ካከበረች በኋላ ሙሉ ሥራዋን ወደ ትምህርት በማድረግ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ማሰቧን ነግራኛለች።
«ሁሌም ያሆዴ ሲደርስ ደስተኛ ነኝ። በተለይ ደግሞ ለበዓሉ አተካናና ክትፎ በተለየ ሁኔታ ስለሚዘጋጅ ለበዓሉ የተለየ ስሜት አለኝ። አተካና በጣም እወዳለሁ። በበዓሉ ሁሉም አዲስ ሆኖ በአዲስ የሚንቀሳቀስበትና ሰላም የሚወርድበት በመሆኑ ልዩ ስሜት አለኝ» ብላኛላች።
ሌላው ያነጋገርኩት ተማሪ እንደገና ወንዱ ይባላል። የሚማረው አባ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ወደፊት ደግሞ ፓይለት መሆን ይፈልጋል። ፓይለት የመሆን ፍላጎት ያደረበትም የጀት አብራሪውን የኮሎኔል ጴጥሮስ በዛብህን ታሪክ መስማት ከጀመረ በኋላ ነው። ይህም ሁኔታ ፓይለት የመሆን ጉጉቱን ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ምኞቱንም እውን ለማድረግ የሳይንስ ትምህርቶችን በጥሩ ሁኔታ እያነበበ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ለሂሳብ ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። የያሆዴ በዓል ሲደርስ በጣም ደስተኛ ነው።
«ሁል ጊዜ የማይዘጋጁ የሀዲያ ባህላዊ ምግቦች ለያሆዴ የዘመን መለወጫ ብቻ ስለሚዘጋጁ በዓሉን በጉጉት እጠብቀዋለሁ። ከምንም በላይ ደግሞ አተካና በጣም ይናፍቀኛል። የዘንድሮው ያሆዴ ሲከበር ከበፊቱ በተሻለ ስለተከበረና ብዙ ሰው እያወቀው ስለሆነ ደስ ብሎኛል። ወደፊትም ብዙ ሰዎች እንዲታደሙ ስለ በዓሉ ብዙ እንዲያውቁ የሚመለከታቸው አካሎች መስራት ይጠበቅባቸዋል። ለሀዲያ ሕዝብ ቀላል በዓል አይደለም። ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀውና ተስፋውን በአዲስ መልክ የሚያልምበት ነው። አዲስ ነገር ሁሉ የሚጀምርበት በዓል ነው።» ብሏል። በመጨረሻም እንኳን ለሀዲያ ሕዝብ ያሆዴ የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲል መልካም ምኞቱን አስተላፏል።
ተማሪ ዮናስ ጌታሁን በአባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ይህ በዓል በጣም ደስ የሚልና ሁሉም ሰው በጋራ በመሆን የሚያሳልፈው በዓል መሆኑን ይናገራል። በተለይ ደግሞ የተጣላ የሚታረቅበትና ይቅር የሚባባልበት ስለሆነ በአዲሱ ዓመት አብሮ ለመኖር ይጠቅማል። የወደፊት እቀዱም ልክ እንደ ተማሪ እንደገና ፓይለት መሆን ነው። ፓይለት ለመሆን የፈለገው ሰዎችን አሳፍሮ በሰማይ መብረር ስለሚያስደስተው ነው። በርካታ የፈጠራ ሥራዎችም አሉት። ስለ ፓይለት ያጠናል ሰው ይጠይቃል። ብዙ ማንበብና ጎበዝ መሆን እንዳለበትም ተረድቷል።
ያሆዴ ሲደርስ የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋል። ልጆችም ቤተሰብን በማገዝ ድርሻቸውን ይወጣሉ። እንዲሁም ጦምቦራ በመስራት በዓሉን እናደምቀዋለን። ተማሪ ዮናስ እንደሚለው አተካናና ክትፎ ስለሚዘጋጅ በዓሉን እንድንናፍቀው ያደርገናል። በመጨረሻም ያሆዴን ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች ለመጡ ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ ብሏል።
በመጨረሻ ሀሳቡን ያካፈለኝ ተማሪ አብነት አርጋው ይባላል። በሆሳዕና ከተማ ቁጥር ሦስት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ያሆዴን ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር በጋራ በመሆን አከብራለሁ። በዓሉ ሁሉም ሰው በመረዳዳት ያከብረዋል። ጦምቦራ ሰርተን አዲስ ልብስ በማስገዛት ባማረና በደመቀ ሁኔታ በዓሉን እናደምቀዋለን። የተጣላቸውንም በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ይቅርታ ጠይቋል። ይቅርታ የጠቁትንም ይቅርታ አድርጎላቸዋል። እየዞሩ የተጣሉትንም በመፈለግ አስታርቀዋል። ‹‹አሁን ቂም መያዝ አይቻልም። በአዲስ ዓመት አዲስ ጓደኛሞች ነን›› ብሏል። ለሀዲያና ከሀዲያ ዞን ውጪ ላላችሁ በሙሉ እንኳን ለሀዲያ የዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል።
ልጆች! ደስ እንዳላችሁ እርግጠኛ ነን። አሁን ስለ ያሆዴ ግንዛቤ አገኛችሁ አይደል? እናንተም በዓልን ስታከብሩ የተጣላችሁትን ይቅር በማለትና ለሌላቸው በመርዳት መሆን አለበት። እንዲሁም ቤተሰባችሁን ማገዝና መርዳት ይኖርባችኋል። መልካም ቀን ይሁንላችሁ!
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
ሞገስ ፀጋዬ