በ1866 ዓ.ም ምዕራብ ሸዋ፣ አገምጃ ውስጥ ልዩ ስሙ ሰርቦኦዳ ኮሎ በተባለ ቦታ አቶ ጋሪ ጎዳና እና ወይዘሮ ሌሎ ጉቴ 13ኛ ልጃቸውን አገኙ። ስሙንም ‹‹ገሜሳ›› አሉት። ሕፃኑ ገሜሳ የልጅነት እድሜውን ያሳለፈው በተወለደበት አካባቢ፣ ኦዳ ኮሎ ነበር። ገና በለጋ እድሜው አርቆ አሳቢና አስተዋይ ነበር ይባላል።
የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጦር ወደ አገምጃ አካባቢ ባቀናበት ዘመቻ ወጣቱ ገሜሳ ፊታውራሪ ዘመንፈስቅዱስ በሚባሉ የጦር መሪ ተማርኮ ወደ አዲስ አበባ፣ ከዚያም መሐል ሸዋ፣ ቡልጋ አውራጃ ወደሚገኘው ኢቲሳ ተክለሃይማኖት ገዳም ተወሰደ። ይህ ገዳም አያሌ ወጣቶች ለወደፊት ኃላፊነት የሚታጩበትና ታማኝ እንዲሆኑ የሚቀረፁበት ቦታ ከመሆኑም በላይ የሃይማኖት ትምህርት እየተማሩ የቤተመንግሥትን ስርዓት እንዲሰለጥኑ የሚደረግበት ስፍራም ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ወጣቱ ገሜሳ ‹‹ገብረማርያም›› በሚለው የክርስትና ስሙ መጠራት የጀመረው።
የረጅም ጊዜያት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ ወደትውልድ መንደሩ ተመልሶ ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኘ። ወደ ፊታውራሪ ዘመንፈስቅዱስ ዘንድ ተመልሶ ትምህርቱን አጠናቀቀ። በወቅቱ የቤተ-መንግሥቱ ገንዘብና ግምጃ ቤት ሹም የነበሩት በጅሮንድ (በኋላ ደጃዝማች) ባልቻ ሳፎ ገብረማርያምን የቤተ-መንግሥቱን ስርዓት በማስተማር ታማኝ ወታደር ብቻም ሳይሆን ብቁ አስተዳዳሪም እንዲሆን አደረጉት። በፈረስ ጉግሥ ጨዋታ ብርቱ የነበረው ገብረማርያም ጋሪ ‹‹አባ ንጠቅ›› የተሰኘውን የፈረስ ስም ያገኘው በዚያን ጊዜ ነው ይባላል።
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር የ22 ዓመት ወጣት የነበረው ገብረማርያም ጋሪ ለንጉሠ ነገሥቱ የክተት አዋጅ ምላሽ በመስጠት ከበጅሮንድ ባልቻ ሰራዊት ጋር ዘመተ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጦርነቱ ሲጀመር ጎህ ሲቀድ ወደ ውጊያ የገባው የበጅሮንድ ባልቻ ጦር እጅግ ከባድ ውጊያ አደረገ። ገብረማርያም አዝማቹ በጅሮንድ ባልቻ ጭምር እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆነው ጦርነት ተርፎ የድሉ ተቋዳሽ መሆን ቻለ። ድሉም ገብረማርያምን ለፊታውራሪነት ማዕረግ አበቃው።
በ1889 ዓ.ም ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ የሲዳሞ ግዛት ገዢ ሆነው ሲሾሙ ፊታውራሪ ገብረማርያም አብረው ወደ ሲዳሞ ተጉዘው በልዩ ረዳትነትና በኋላም የአውራጃ ገዢ በመሆን እስከ 1900 ዓ.ም ድረስ ሲያገለግሉ ቆዩ። በ1900 ዓ.ም ደጃዝማች ባልቻ የሐረርጌንና የባሌን ግዛቶች አንድ ላይ ለማስተዳደር ወደ ሐረር ሲዛወሩ ፊታውራሪ ገብረማርያምም አብረው በመሆን እስከ 1902 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል።
በ1902 ዓ.ም ደጃዝማች ባልቻ በድጋሚ ፊታውራሪ ገብረማርያምን ይዘው ተመልሰው ወደ ሲዳሞ ተጓዙ። ልጅ ኢያሱ ደግሞ በ1907 ዓ.ም የሲዳሞን ግዛት ከደጃዝማች ባልቻ ነጥቀው ለእህታቸው ባል ለቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ሰጧቸው። በዚህ ሹም ሽር ሳቢያ አገር ለማቅናት ሲደክሙ የነበሩት የዓድዋ ጀግኖች ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ እና ባለሟላቸው ፊታውራሪ ገብረማርያም ጋሪ ከመንግሥታዊ ሥራ ውጭ በመሆናቸው ወደትውልድ ስፍራቸው ሄደው በርስታቸው ላይ እያሳረሱ መኖር ጀመሩ።
ፊታውራሪ ገብረማርያም ወደትውልድ ስፍራቸው ተመልሰው በነበረበት ወቅት ጎንግ የተባለውን ወንዝ አስጠልፈው፣ ግድብ አሰርተው በውሃ ኃይል የሚሰራ ወፍጮ አስተክለዋል። ከግድቡ የሚወጣው ውሃ የወፍጮውን ሞተር ካስነሳ በኋላ በኩሬ መልክ እንዲጠራቀም በማድረግ ለከብቶች መጠጥ እንዲውል አድርገዋል። በአገምጃ የስልክ መስመር እንዲዘረጋ ያደረጉትም እርሳቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች በርካታ የልማትና የአስተዳደር ስራዎችን እንዳከናወኑ የአካባቢው አዛውንቶች ይናገሩላቸዋል።
በመስከረም 1909 ዓ.ም በተደረገው ሹምሽር (የልጅ ኢያሱ ከዙፋን መነሳትና የዘወዲቱ ምኒልክና የተፈሪ መኮንን መሾም) የተናደዱት የልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል አሊ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር ሲዋጉ ደጃዝማች ባልቻ አዲስ አበባ ከተማን አንዲጠብቁ ኃላፊነት ተሰጣቸው፤ፊታውራሪ ገብረማርያም ደግሞ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር ዘመቱ። ፊታውራሪም በሰገሌው ጦርነት ላይ ቢቆስሉም ድሉ የማዕከላዊው መንግሥት ጦር ሆነ።
ውሎ አድሮ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክና በአልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን መካከል የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ደጃዝማች ባልቻን አላስደሰታቸውም ነበር። ለንግሥቲቱ ሲወግኑ የነበሩት የደጃዝማች ባልቻና የአልጋ ወራሹ ልዩነት በግልፅ ታየ፤አልጋ ወራሹም የደጃዝማቹን ታማኞች ማስከዳት ጀመሩ። ደጃዝማች ባልቻን ከሁሉም አስበልጦ የጎዳቸው የባለሟላቸው የፊታውራሪ ገብረማርያም ወደአልጋ ወራሹ ማዘንበላቸው ነበር።
ፊታውራሪ ገብረማርያም የአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን አገልጋይ በመሆን ወደ ቤተ-መንግሥት ከመጡ በኋላ በቅድሚያ የተመደቡት በአጋፋሪነት ነበር። በግንቦት 1922 ዓ.ም ፊታውራሪ ገብረማርያም በደጃዝማችነት ማዕረግ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ተሾሙ። የኢጣሊያ መንግሥት በ1900 ዓ.ም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተፈራርሞት የነበረውን ውል በመናድ ወታደሮቹን ወደ ኦጋዴን ግዛቶች በጥልቀት በማስገባት አንዳንድ መሬቶችን ከመያዙም በላይ ቋሚ ግዛቶቹ ለማድረግ በመጣር ላይ ስለነበር ኦጋዴንን ከኢጣሊያ መከላከል የደጃዝማች ገብረማርያም ተቀዳሚ ስራቸው ነበር። በዚህ መሰረት ለጉዳዩ መፍትሄ ለመፈለግ በሐምሌ 1923 ዓ.ም ጂግጂጋ ከሚገኘው ጠቅላይ ሰፈራቸው ሦስት ሺ ወታደሮችን ይዘው ተንቀሳቀሱ። አካባቢውን ከኢጣሊያ ሰርጎ ገብ ወታደሮች ከማጥራታቸውም በተጨማሪ ከአካባቢው ሕዝብና ሹማምንት ጋር ሰላማዊ ውይይት በማድረግ ስፍራው የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑን አረጋግጠው ተመልሰዋል።
ደጃዝማች ገብረማርያም አካባቢውን ከሰርጎ ገቡ ኃይል ካጸዱ በኋላ በዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ ሰራዊት በማስቀመጥ የጣሊያኖችን ሰርጎ ገብነት በቋሚ ጦር ለመከላከል ጥረት አድርገዋል። ሌላኛው ዓላማቸው ከተሞችን በመቆርቆር ከዋናው የሐረርጌ አስተዳደር ጋር በመንገድና በአስተዳደር መዋቅር ማገናኘት ነበር። በኦጋዴን ግዛት ውስጥ የአስተዳደር መዋቅር በመዘርጋት ነዋሪው ሕዝብ የመንግሥትን ሚና ተረድቶ በተዘረጋለት የልማት አቅጣጫ ይጓዝ ዘንድ በተናጠል የሚኖርበትን የአሰፋፈር ዘዴ በመቀየር በአንድ አካባቢ እንዲሰፍርና ለልማቱ ሥራ አመቺ እንዲሆን መንደሮችንና ከተሞችን በመቆርቆር በርካታ የልማት ተግባራትን አከናወኑ።
በኋላ ግን ደጃዝማች ገብረማርያም ከሐረርጌ እንደራሴነታቸው ተነስተው የንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ ‹‹መስፍነ ሐረር›› ሆነው ተሾሙ። በዚህ ወቅት ደጃዝማች ገብረማርያም ስላበረከቱት አስተዋፅኦ ንጉሠ ነገሥቱ እንዲህ ብለው ነበር።
’’… አሁን በአደባባይ ጠርተን የምናናግርህ ሙያህን ለሕዝብ ለመግለፅ ነው። እኛ አገልግሎትህን ከጥንት ጀምሮ እናውቀዋለን፤ሁሉ ስላልተረዳው እናዝናለን። ገና ሥራ ስንጀምር አብረህ ሳትለይ የማለዳውን ቁርና የቀትሩን ፀሐይ ሳታዳምጥና ሳትበገር ዘብ ሆነህ ከዚህ ደርሰናል። በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ወሰኖች ብዙ ችግር እንደገጠመን ተገልጿል። ቅን ሃሳብህን ያልተረዱልህ አንዳንድ ሰዎች ባይመስላቸውም ስላላወቁልህ እናዝናለን። ከፊታቸው ስናመሰግንህ ለውለታህ የሚበዛበት አይደለም …‘ ከዚህ ንግግራቸው በኋላም ንጉሠ ነገሥቱ ለደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የኢትዮጵያን የወርቅ ኒሻን በአንገታቸው አጠለቁላቸው።
ከዚያም የአገር ግዛት ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። በዚህ ኃላፊነታቸውም እንደተለመደው ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ችለዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን ሕጋዊነት የሚያረጋግጠውን አዋጅ የማስፈጸም ኃላፊነት የተረከቡትም ደጃዝማች ገብረማርያም ነበሩ። የማኅበሩ ምስረታ ከፋሺስት ወረራ ጋር በመገጣጠሙ የማኅበሩ አባላት ለአርበኞች መድኃኒት ያቀርቡ፤ቁስለኞችንም ያክሙ ነበር። በዚህ ሥራ ውስጥም ደጃዝማች ገብረማርያም ድርሻ ነበራቸው። ከጀርመን መንግሥት ጋር የተደረገውን የመሳሪያ ግዢ ስምምነት ካስፈጸሙት ሰዎች መከከል አንዱ ደጃዝማች ገብረማርያም ናቸው።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በሰሜን፣ በደቡብና በምስራቅ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን ሲወር ደጃዝማች ገብረማርያም ጦር አሰልፈው ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመጓዝ ቆቦ ደርሰው ቦታውን ከተቆጣጠረው ግንባር ቀደም የጠላት ኃይል ጋር ውጊያ ገጥመው የጠላት ጦር ለቀጣዩ ውጊያ እንዲረዳው በማሰብ የዘጋውን በር ማስከፈት ችለዋል። ይሁን እንጂ በደቡብ በኩል የነበረው የጠላት ወረራ የበረታ ስለነበር ደጃዝማች ገብረማርያም ከሰሜን ወደ ደቡብ ሄደው ከራስ ደስታ ዳምጠው ጋር ሆነው ጠላትን እንዲመክቱ በንጉሠ ነገስቱ በመታዘዛቸው ወደ ደቡብ ግንባር ሄዱ።
በግንቦት 1928 ዓ.ም ደጃዝማች ገብረማርያም በታላቅ ወንድማቸው በደጃዝማች ኡርጋ ጋሪ፣ በወንድማቸው ልጅ በሻቃ በቀለ ወያ እና በፊታውራሪ ተሰማ አብዲ በመታገዝ ድኑን በተባለ አካባቢ በጠላት ጦር ላይ የሁለት አቅጣጫ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፤በመጨረሻም ድል ተቀዳጁ።
ኅዳር 8 ቀን 1929 ዓ.ም ደጃዝማች ገብረማርያም በመትረየሳቸውና ‹‹ገላግሌ›› በሚባለው ባለጋሻ መድፍ እየታገዙ በጠላት ላይ ጥቃት ከፈቱ። በዚህ ጥቃት ከመቶ የሚበልጡ የጣሊያን ወታደሮች ሲደመሰሱ ጫካውን ተገን አድርጎ ካመለጠው የአገር ተወላጅ ባንዳ በስተቀር አብዛኛው ባንዳ እዚያው ጫካ ውስጥ ቀርቷል። በኋላ እንደተረጋገጠው ደግሞ አንድ የጣሊያን የጦር ጀኔራልም በውጊያው ሞቷል። ከዚህ ውጊያ በኋላ የጣሊያን ጦር የማጥቃት ዘመቻ ቢያደርግም ምንም ውጤት ስላላመጣለት በቦታው የነበረው ጦር አዛዥ ጀኔራል ጀሎዞ ለማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ‹‹የተፈሪ ኬላን በር ጥሼ ወደመሐል አገር ወደ ይርጋለም ማለፍ አልቻልኩም፤ስለዚህ ወታደሮቼን ይዤ ወደኋላ ማፈግፈግ ግድ ሆኖብኛል›› በማለት መልዕክት ልኮለት ነበር።
በደጃዝማች ገብረማርያም የማጥቃት እርምጃ የተጎዳው የጣሊያን ጦር እንደገና ተጠናክሮ ማጥቃት ጀመረ። ደጃዝማች ገብረማርያምም በወንድማቸው ደጃዝማች ኡርጋ ጋሪና በሻቃ በቀለ ወያ ታግዘው የሲዳሞን ጦር ይዘው የጠላትን እግረኛ ጦር ለአራት ተከታታይ ቀናት መከቱ። በዚህ ውጊያ ብዙ የጠላት ወታደሮች ቢደመሰሱም የጠላት ጦር ሲጠናከር የወገን ኃይል ግን በስንቅም ሆነ በትጥቅ ተዳከመ።
በሰሜንና በምስራቅ በኩል የማጥቃት ዘመቻ የከፈተው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ዋና ከተማው አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ መግባት ቢችልም በደቡብ በኩል የነበረው ጦር ግን ከነራስ ደስታ ዳምጠው እና ከነደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ በኩል በገጠመው የመከላከልና የማጥቃት ዘመቻ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መድረስ ስላልቻለ የግንባሩ ጦር አዛዥ ጀኔራል ጀሎዞ እና ዋናው የአስተዳደሩ ተወካይ ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ለራስ ደስታና ለደጃዝማች ገብረማርያም ልመና፣ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ የተቀላቀሉባቸው ደብዳቤዎችን ጽፈውላቸው ነበር።
ጥር 1 ቀን 1929 ዓ.ም ሻንቆ በተባለው ቦታ ላይ በተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያውያን በጠላት እግረኛ ጦር ላይ ከፍተኛ ድል ቢቀዳጁም የጠላት ጦር በአውሮፕላን የሚያዘንበውን ቦምብና መርዝ ግን መቋቋም አልተቻለም። በመሆኑም አርቤጎናን በመልቀቅ ብዙ የወገን ጦር ወዳለበት ወደ ባሌ ግዛት ለመሄድ ተወሰነ። ውጊያው በመንገድ ላይም አላባራም ነበር። የወገን ጦር መንገድ የዘጋበትን የፋሺስት ጦር በመውጋት መንገድ እያስከፈተ ዘለቀ።
ጥር 20 ቀን 1929 ዓ.ም ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣ ደጃዝማች በዛብህ ስለሺ እና ፊታውራሪ ሽመልስ ሀብቴ ጦራቸውን ይዘው እነርሱም መድፍ ጠምደው ተሰለፉ። ደጃዝማች ገብረማርያም አመርቅዞ እየጠዘጠዘ ያሰቃያቸው የነበረውን ቁስላቸውን ከምንም ሳይቆጥሩ የታጠቁትን ሱሪ ወደላይ በመሰብሰብ ያለጫማ እየተራመዱ በያዙት ግንባር በኩል በግራና በቀኝ እየተሽከረከሩ ዝናር ሙሉ ያጎረሱትን መትረየስ በጠላት በኩል በማስገባት በር አስከፍተዋል። በዚህ ተጋድሎ ኢትዮጵያውያን አካባቢው በጠላት እጅ እንዳይወድቅ ከማድረጋቸውም ባሻገር በጠላት ጦር ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረስ ችለዋል።
የካቲት 10 ቀን 1929 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደቡታጅራ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የፋሺስት ጦር ላይ ጥቃት ተከፈተ። ጠላት ያላሰበው ጥቃት ስለነበርም ክፉኛ ተጎዳ። ለበቀል እርምጃ የተነሳው የጠላት ጦር እርምጃ መውሰድ ሲጀምር እልህ አስጨራሽ ውጊያ ተካሄደ። ራስ ደስታ ጥቂት ወታደሮችን ይዘው ወደ መስቃን ሄዱ። ቀኛዝማች ኡርጋ ጋሪ፣ ቀኛዝማች በየነ ጉደታ እና ሻለቃ በቀለ ወያ ያሉበት ቀሪው ጦር ደጃዝማች ገብረማርያምን አጅቦ ወደ ማረቆ ወደሚገኘው ጎጌቲ ገብርዔል ሲያመራ የጠላት ጦር ክትትሉን ስላላቋረጠ ጎጌቲ ገብርዔልን ከብቦ ያዘ። ደጃዝማች ገብረማርያምም እየመከቱ ሚልኮ ማርያም ደረሱ። ይህ ውጊያ የመጨረሻው እንደሚሆን ቀድመው ያወቁት የዓድዋው ጀግና ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ይህን ንግግር ተናገሩ …
’’… ዛሬ ሰርጌ ነው፤ለውድ አገራችን ለኢትዮጵያና ለሰንደቅ ዓላማችን ግዳጄን ፈፅሜ ሕይወቴን አሳልፋለሁ። ከዚህ እልፍ አልልም፤የመጨረሻ ትግሌ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል። ሩጫዬን አበቃለሁ! ጠላት እጄን አይጨብጥም። እንደማየው ጠላት ዙሪያችንን ከብቦናል። በዛሬው ቀን በምናደርገው የሞት የሽረት ውጊያ ላይ መሳተፍ የማትችሉ ከአጠገቤ መለየት ትችላላችሁ። እኔ ቁስለኛ እግሬ ሊያራምደኝ አይችልም። ውጊያው የተጠናከረ መሆኑን ስታውቁ ባመቻችሁ መንገድ ሁሉ ሾልካችሁ እስከወደቃችሁ ድረስ ባገራችሁ ጉራንጉር፣ በወንዞቻችሁ ሸለቆዎችና ዱር ግቡ። ሕያው እግዚአብሄር ይከተላችሁ …‘
ቤተሰቦቻቸውን ወደ አገምጃ እንዲሄዱ አደረጉ። ሻቃ በቀለ ወያንና ቀኛዝማች በየነ ጉደታን አቅርበው በምንም ዓይነት ሁኔታ እጃቸውን እንዳይሰጡ መክረውና መርቀው ካሰናበቱ በኋላ የጠላትን ወታደር ሲያጋድሙ ውለው ከጠላት ጦር በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ወደቁ።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ክቡር ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም ለአገራቸውና ለወገናቸው ክብር በ63 ዓመታቸው ከሚያልፈው ዓለም ላይ የማያልፍ ታሪክ ሰርተው አለፉ።
ደጃዝማች ገብረማርያም ከሞቱ በኋላ እንኳ ሲፈሩና ሲደነግጡ የነበሩት የፋሺስት ኢጣሊያ ሹማምንት የደጃዝማቹ አስክሬን ከተቀበረበት ተቆፍሮ ወጥቶ እርሳቸው መሆናቸውን በቅርብ ሰው እንዲታይ ስለማድረጋቸው ከደጃዝማች ከበደ ተሰማ የግል መዛግብት ውስጥ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ‹‹ሊሴ ገብረማርያም (Lycee Franco Ethiopien Guebre Mariam)›› ትምህርት ቤት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 7/2012
አንተነህ ቸሬ