የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ የሚያደርገውን የበረራ አገልግሎት ትናንት ሌሊት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለበርካታ ዓመታት ወደ ሩሲያ በረራ ሰያድርግ ቢቆይም በተለያዩ ምክንያቶች በፈረንጆቹ 1991 አገልግሎቱን ማቋረጡን አስታውሰዋል።
“አየር መንገዱ ወደ ታላቋና በዓለም ሃያል ከሆኑት ሀገሮች አንዷ ወደ ሆነችው ሩሲያ በረራውን እንደገና መጀመሩን አበስራለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2025 ባቀደው ራዕይ መሰረት የበረራ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን ወደ ሞስኮ የሚደረገው በረራም የዚሁ አካል መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ወደ ሞስኮ በረራ መጀመሩን ተከትሎ አየር መንገዱ ወደ አውሮፓ የሚያደርገውን የመንገደኞች አገልግሎት ሳምንታዊ በረራ ወደ 54 ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ በየሳምንቱ ወደ አውሮፓ 33 የእቃ ጭነት አገልግሎት በረራ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሳምንቱ አዳዲስ መዳረሻዎችን እየጨመረ ነው፤ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍርካ ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱ ትልቀ ሚና አለው ብለዋል።
የአየር ለአየር ትስስር መፍጠር ለሀገራት ማህብረ-ኢኮኖሚያዊ እድገትና ትስስር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ቭሴቮሎድ ትካቼንኮ በበኩላቸው የአየር መንገዱ በረራ መጀመር የ120 ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸውን ሀገራት ትስስር በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በሩሲያ መካከል ድልድይ ለመሆን የቀጥታ በረራ መጀመሩን አድንቀዋል።
ከቱሪዝምና ከኢኮኖሚ ፋይዳዎች ባሻገር የመንገደኞችን የበረራ አማራጭ በማስፋት ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆንና በቀጣይ በኤምባሲያቸው በኩል ትብብሮችን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞስኮ በረራ ሲጀምር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።