ምዕራባውያን የብዙ ሙያዎችና ተሰጥኦዎች ባለቤት የሆነን ግለሰብ ለመግለፅ ‹‹A Jack of All Trades›› የሚል አገላለፅ ይጠቀማሉ። ‹‹ለዚህ አገላለፅ ተገቢ (እውነተኛ ምሳሌ) የሆነ ኢትዮጵያዊ ማነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አንዱና ዋነኛው ስለመሆናቸው ብዙም ክርክር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
ስመጥር አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ቀራፂ፣ ሰዓሊ፣ ነጋዴ፣ መኪና አሽከርካሪ፣ መካኒክ፣ ፖለቲከኛ፣ ፎቶ አንሺ … የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የበርካታ ሙያዎችና ተሰጥኦዎች ባለቤት ሆነው ሳለ የአበርክቶዎቻቸውን ያህል ታዋቂነትና ውለታ የተነፈጋቸው ሰው ናቸው።
ነጋድራስ ተሰማ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተየስ ሐብቱ ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.ም ምንጃር ውስጥ ቀርሾ አጥር በተባለ ስፍራ ተወለዱ። አባታቸው አቶ እሸቴ ጉቤ በመሰንቆ ተጫዋችነታቸው ተወዳጅነትን ያተረፉ አዝማሪና የራስ መኮንን ባለሟል ነበሩ። ራስ መኮንን ወደ ሐረር በዘመቱበት ወቅት እርሳቸውን ተከትለው ወደሐረር የዘመቱት አቶ እሸቴ ኑሯቸውን በዚያው በሐረር አድርገው ሳለ ሕይወታቸው አለፈ።
የአባቱን ማረፍ ተከትሎ ወደአዲስ አበባ የመጣው ታዳጊው ተሰማ ገና በልጅነቱ በስዕል ችሎታቸው ተደናቂ መሆን ቻለ። ለሙዚቃም የተለየ ፍቅር ነበረው። ይህ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት ከአባቱ ወርሶት ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። በችሎታውም በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ የአውሮፓውያንን ጭምር ቀልብ ለመግዛት ብዙም አልተቸገረም።
ሙሴ አርኖልድ ሆልስ የተባለ ጀርመናዊ በአዲስ አበባ የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ለስንብት ወደ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዘንድ ሲቀርብ ለንጉሰ ነገሥቱ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው። ሦስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ወደ ጀርመን ወስዶ በማስተማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው እንደሚፈልግ ተናገረ። ንጉሰ ነገሥቱም ተሰማን በጥሩ ሰዓሊነቱና ቀራፂነቱ ያመሰግኑት ነበርና ‹‹ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ስለሆነ መኪና መንዳትና መጠገን እንዲማር እርሱም ይሂድ›› ብለው ከሦስቱ ወጣቶች መካከል አንዱ ተሰማ እሸቴ እንዲሆን ፈቀዱ። ወደ ጀርመን ሄዶም ለሁለት ዓመታት ያህል የአውቶሞቢልን አሰራር (መኪና መንዳትና መጠገን) አጥንቶ ተመለሰ።
በጀርመን ቆይታው በንጉሰ ነገሥቱ ከተፈቀደለት ትምህርት በተጨማሪ በራሱ ተነሳሽነት ‹‹ሂስ ማስተር ቮይስ›› ከሚባለው ኩባንያ ጋር በመዋዋል 17 የዘለሰኛና የመዲና ዘፈኖቹን በሸክላ ላይ አስቀርጿል። ይህም ሙዚቃን በሸክላ ላይ ያስቀረጸ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንዲሆን አስችሎታል። ሁለቱ ሙዚቃዎቹ በግዕዝ ቋንቋ የተሰሩ ነበሩ። በሙዚቃ ስራዎቹ ግጥሞች ላይ ያነሳቸው ጉዳዮች ሰውየው በወቅቱ የነበረው የዕይታ አድማስ ሰፊ እንደነበር የሚያመለክቱ ናቸው። በግጥሞቹ ላይም በጊዜው በኢትዮጵያ ስለነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ በድፍረት አመልክቷል። እቴጌ ጣይቱንና የወቅቱን ታላላቅ መኳንንት ጭምር ወቅሷል፤ አስጠንቅቋል፤ መክሯል። ስራዎቹን ላስቀረፀበትም 17ሺ የጀርመን ማርክ ተከፍሎታል። ከዚያ በፊት ዘፈኖችና የአዝማሪዎች ስራዎች የሚደመጡት በግራማፎን ነበር። ሌሎች ዘፋኞች ዘፈኖቻቸውን በዲስክ ማስቀረፅ እስከቻሉበት እስከ 1925 ዓ.ም. ድረስ ለ20 ዓመታት ያህል በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች ይደመጡ የነበሩት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ስራዎች ብቻ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል።
ከጀርመን እንደተመለሰም የቤተ-መንግሥት መኪናዎች ኃላፊ ሆነ። ኢትዮጵያውያን መኪና አሽከርካሪዎችንም አሰለጠነ። በዚህ ሙያውም ከፍተኛ ተወዳጅነትን አተረፈ። ባሳየው የስራ ትጋት የአዲስ አበባ ፍል ውሀ ድርጅትን እንዲመራ ተሾመ። የራስ ካሣን አህት ወይዘሮ ፀሐይወርቅ አንዳርጌን አገባ። ከወይዘሮ ፀሐይወርቅ ጋር የነበራቸው ትዳር ሊሰምር ባለመቻሉ ወይዘሮ ሙላቷ ገብረሥላሴን አገባ። ከትዳራቸውም ሰባት ልጆችን አፍርተዋል። ከልጆቻቸው መካከል አንዱ ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ አባት›› በመባል የሚታወቁት ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ይደነቃቸው ተሰማ ናቸው። ልጆቻቸውንም ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ አድርገዋል። ቁጥራቸው በርከት ያሉ ታክሲዎችን ከውጭ በማስመጣትና የሕዝብ ትራንስፖርት በማቋቋም በርካታ ኢትዮጵያውያን ሹፌሮችን አሰልጥነዋል።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከሙዚቃ ችሎታቸው በተጨማሪ በግጥም ችሎታቸውም እጅግ የተደነቁ ነበሩ። ብዙዎቹ ግጥሞቻቸው የሰምና የወርቅ ፍችዎች ያሏቸው፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት ጠንካራና በአፃፃፍ ቴክኒካቸው የተዋጣላቸው ናቸው። ብዙዎቹ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ግጥሞች በወቅታዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ፤ የትችነት ባህርይ ይንፀባረቅባቸዋል። ቀጥለው የተጠቀሱት ሶስት ምሣሌዎች የነጋድራስ ተሰማን የግጥም ርዕሰ-ጉዳዮችና የግጥሞቹን ደረጃዎች ሊያመለክቱ ይችላሉ።
‹‹ የአገሬ ወንዞች መጥኔውን ይስጣችሁ፣
ክረምት ሲመጣ እየጨነቃችሁ፣
ዋጋ አትቀበሉ አስታዋሽ ያላችሁ፣
ከአዳም ጀምሮ እስከአሁን እድሜያችሁ፣
ሰውንም ከብቱንም እቃ እንዳጋዛችሁ፣
የማትታመኑ በዋል ፈሰስ ናችሁ፣
ለውቅያኖስ ዓሣ እያስረከባችሁ፣
አንድ እንኳ አታመጡ ወዲህ መልሳችሁ።
***
አገሬ ታውቂያለሽ እንደምንወድሽ፣
በታመምሽ ጊዜ ተዘግቶ ጆሮሽ፣
በነፃነት ፀጋ እስክትፈወሽ፣
በአራቱ ማእዘን ዓለም ሲጠራሽ፣
ያምላክ ውለታ ምነው ማጥፋትሽ፣
አትናገሪም ወይ ተሰማ ብለሽ?
***
የወዲያ ሰዎች ክፋታቸው፣
ሬሳ አጋድመው መብላታቸው፣
የሸዋ ሰው መልካም፣
ወዳጁን ሳይቀብር አይበላም። ››
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት ሲኖሩ በበርካታ ሙያዎቻቸው የሚታወቁትን ያህል በቀልድ አዋቂነታቸውም የተደነቁ ነበሩ። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን በቅርብ እናውቃለን የሚሉ ወገኖች ከወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት የሚያመነጯቸው ቀልዶች ከአለቃ ገብረሃና ቀልዶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ሲናገሩ ይስተዋላል። ነጋድራስ ተሰማ በሕይወት ዘመናቸው ከቀለዷቸው አሽሙሮች መካከል ሁለቱን ቀጥሎ እንመልከታቸውና ምላተ-ጉድለታቸውን እንመርምር።
ሀ). ነጋድራስ ተሰማ በአንድ ወቅት ከመኳንንቱ ጋር ቁጭ ብለው ሲጫወቱ «አሁን ሁላችሁም በሆዳችሁ የምታስቡትን አውቃለሁ» በማለት ተናገሩ። መኳንንቱም ‹‹አያውቁም›› ሲሉ ተከራከሯቸው። ከመኳንንቱ አንዱ «አያውቁም» ብለው በመቶ ብር ተወራረዷቸው። እርሳቸውም «ሁላችሁም ለንጉሡ ነው የምታስቡት። በሆዳችሁ ያለው ይህ ነው» ብለው ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ደፍሮ ‹‹አይደለም›› ብሎ የሚከራከር በመጥፋቱ ውርርዱን ረቱ።
ለ). በአንድ ወቅት ደግሞ ንጉሰ ነገሥቱ ባሉበት የኢላማ ተኩስ ሲደረግ እልፍኝ አስከልካዩ በመጀመሪያ ጥይት ተኩሶ ኢላማውን መታ። በዚህ ጊዜ ነጋድራስ ተሰማ ቀስ ብለው «ባንዴ ቡን አደረጋት!» ሲሉ ተናገሩ። እልፍኝ አስከልካዩ በፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዓመታት ባንዳ ስለነበር ያንን በአሽሙር ለመንካት ሲሉ የተናገሩት ጣምራ ትርጉም ያለው ንግግር ነበር።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በኢትዮ ጵያ ባልተለመደ መልኩ ሃሳብን በነፃ መግለፅና መንግሥታትንና መሪዎችን መተቸት ባህርያቸው ነበር።
‹‹ባለስልጣኖቹ እስኪ አስቡ በት፣ መናገራችሁን እንዳትተ ውት።›› ብለው የገጠሙት የዚሁ ማሳያ ነው።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው። ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ነበራ ቸው። በልጅ ኢያሱ የአስተዳደር ዘመንም ሰይድ ባዝራ ከተባለ ግለሰብ ጋር በመሆን ከብት ወደ ውጭ አገራት ይልኩና ወደአገር ውስጥ ደግሞ ፈቃድ ጠይቀው የጦር መሳሪያ ያስመጡ ነበር።
አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሐል አገሩ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለፈ ጊዜ ሁሉ ነጋድራስ ተሰማ ግን የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ ዘልቀዋል። ልጅ ኢያሱ ከዙፋን ሲወርዱም የልጅ ኢያሱ ወዳጆችና ደጋፊዎች ለግዞትና ለእንግልት ተዳረጉ። ነጋድራስ ተሰማም ጅማ ውስጥ በግዞት ተቀምጠው ቆዩ። ከልጆቻቸው መካከል አራቱ የተወለዱት በግዞት ላይ ሳሉ ነው። ነጋድራስ ተሰማ በአባ ጅፋር ግቢ ለሰባት ዓመታት ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
‹‹ አታበሉኝም ወይ ከጮማው ቆርጣችሁ፣
አታጠጡኝም ወይ ከጥሩ ጠጃችሁ፣
ሰባት ዓመት ሙሉ ተለፋሁላችሁ።›› ብለው ስሜታቸውን ገለፁ።
ከግዞት በተጨማሪም ብዙ ንብረቶቻቸው ተወርሰውባቸው ነበር። ሳይወረስ የቀረው አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ (ፒያሳ አካባቢ) የሚገኘው ቤታቸው ብቻ ነበር። በጉምሩክ መሥሪያ ቤትና በአንድ ግሪካዊ ነጋዴ ቤት ያስቀመጡት 300ሺ ብር የሚያወጣ ጠመንጃና ጥይትም ሳይመለስላቸው ቀረ።
የማይጨው ዘመቻ እንደተጀመረ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደዘመቻው ከማምራታቸው በፊት የልጅ ኢያሱ ደጋፊዎች ዝም ብለው አይቀመጡም ብለው በማሰብ ከአዲስ አበባ ያርቋቸው ጀመር። ነጋድራስ ተሰማም በነጋድራስነት ሹመት ሰበብ ወደ ወላይታ ግዛት እንዲርቁ ተደረገ። በዚህ ወቅትም፣ የጠላት ወረራ የፈጠረው የብጥብጥ ስሜት በግዛቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳያስነሳ የፀጥታ ኃይል አቋቁመው ህግና ስርዓት እንዲጠበቅ አድርገዋል።
የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር የተጣሉ ሰዎችን ሰብስቦ አክብሮት መለገስ ጀምሮ ስለነበር ነጋድራስ ተሰማም የተወረሰው ቤታቸው ተመለሰላቸው። ቤታቸውን አከራዩት። ይሁን እንጂ ቤታቸውን የተከራዩት ጣሊያኖች ለነጮች እንጂ ለጥቁሮች ቦታ ስላልነበራቸው ነጋድራስ ተሰማ ከዕለታት አንድ ቀን ምግብ ለመብላት ወዳከራዩት የራሳቸው ቤት ሲገቡ በጥቁርነታቸው መገለል ደረሰባቸው። ቀደም ሲል ወደወላይታ እንዲርቁ መደረጋቸውና አሁን ደግሞ በጥቁርነታቸው ምክንያት የደረሰባቸው አድልኦ ያበሳጫቸው ነጋድራስ ተሰማ እንዲህ ብለው ተቀኙ።
‹‹ ታሪኬ ብዙ ተሰማ እሸቴ፣
ተደብቄያለሁ በገዛ ቤቴ። ››
ወደፋሺስት አስተዳደር አለቃው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ሄደው ‹‹ልናሰለጥናችሁ መጣን ብላችሁ የዘር ልዩነት ልትመሰርቱና ከሰው በታች ልታደርጉን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው። ግራዚያኒም ‹‹አዝናለሁ፤ ከሙሶሊኒ የመጣ ትዕዛዝ ነው›› ብለው መልሰውላቸዋል።
ነጋድራስ ተሰማ በነገር የሚሸነቁጡት ምዕራባ ውያንንም ጭምር ነበር።
‹‹ የሰላም አለቆች እንግሊዝ ፈረንሳይ፣
እግዜር እንዳይገድለኝ የእናንተን ጉድ ሳላይ ›› በማለት እንግሊዝና ፈረንሳይ በወቅቱ በኢትዮጰያ ላይ ይሸርቡት የነበረውን ሴራ ጠቁመዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ተሸንፎ ንጉሰ ነገሥቱ አዲስ አበባ ሲገቡ ነጋድራስ ተሰማ ‹‹ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር ተባብረው መስራታቸውን እናውቃለን›› የሚሉ ከሳሾች በዙና ወሊሶ አካባቢ ለስድስት ዓመታት በግዞት እንዲቆዩ ተደረገ። ይሁን እንጂ ፋሺስት ኢጣሊያ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱት አርበኞች ከነራስ አበበ አረጋይ ጋር እንዲያስታርቁት ሽምግልና ልኳቸው ነበር። ነገር ግን አርበኛውን የሚጠቅምና ጠላትን የሚጐዳ ድርድር አድርገው መመለሳቸው ስለታወቀ ለተወሰነ ጊዜ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ፋሺስት ጣሊያንን የሚቃወሙና የሚተቹ ብዙ ግጥሞችን ገጥመዋል።
‹‹ እገበያ መሀል ፈስ እያንዛረጡ፣
አውራ ጐዳና ላይ ዳቦ እየገመጡ፣
ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትምባሆ እየጠጡ፣
እንዲህ ነው ወይ ጣልያን አልጋ ላይ ሲወጡ ››
ብለው ነበር።
የጣሊያንን ክፋትና አደገኛነት ለህብረተሰቡ ለማሳወቅና በጀግንነት እንዲመክተው ለማድረግም ይህን ብለዋል።
‹‹ እናንት ገበሬዎች በፊት ተማከሩ
አረማሞ እንክርዳድ ሲናር እንዳትዘሩ
ገና በሽፍኑ ፍሬ ሳያፈራ ጨፍጭፎ ቆራርጦ
መጣል ነው ለአሞራ።
ይህን የመጥፎ ዘር የባህር ማሽላ
ነቃቅሎ ማጥፋት ነው መቼም አይበላ።››
ከግዞት እንደተፈቱም የሻሸመኔ የእንጨት ፋብሪካና የቲማቲም ድልህ ፋብሪካ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ መትከል የጀመሩት እርሳቸው ነበሩ። አገራቸው በግብርና ዘርፍ ታዋቂ እንድትሆንና የውጭ አገራት ጎብኚዎችን ዓይን እንድትስብም ጥረት ያደርጉ ነበር። በሶደሬ፣ በወንጂ፣ በወሊሶ፣ ፍልውሃና በቦኮ እንፋሎት ላይ ያከናወኗቸው ተግባራት ለዚህ ምስክሮች ናቸው። በቱሪዝም ረገድ ለአገራቸው የነበራቸውን ስሜትም በዚህ ስንኝ ገልጸውታል።
‹‹ ከዓባይ ኢንዱስትሪ ከአዶላም ከወርቁ፣
ከዋቢ ሸበሌም አትክልቶች ሲፀድቁ፣
የዓለም ቱሪስቶች እኛን እንዲያደንቁ፣
ደስም እንዲላቸው ሲመጡ ከሩቁ።
ይህ ነው የኔ ምኞት ጥንትም ሆነ ዛሬ፣
እንዲህ ሆና እንዳያት ኢትዮጵያ አገሬ። ››
የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል አጥብቀው ይጥሩ እንደነበር የሚነገርላቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ እርሻና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ለንጉሠ ነገሥቱ ሃሳብ እያቀረቡ የውሀ ግድቦችና ሰፋፊ እርሻዎች እንዲሰሩ አድርገዋል። በፍል ውሃ ድርጅት ዳይሬክተርነትና በፖስታ ሚኒስትርነትም አገልግለዋል። የሕዝብን መንፈስ የሚያዳክሙ ነገሮችን በፅኑ ይቃወሙ ስለነበር ከልክ ያለፈ የመጠጥ፣ የትምባሆና የጫት ተጠቃሚነት አመል እንዲጠፋ በምሳሌነትም ሆነ በምክር ከፍ ያለ ትግል አድርገዋል። የእርሳቸው አመጋገባቸውና የመጠጥ አወሳሰዳቸው በጥብቅ ፕሮግራምና ስርዓት ይከናወን እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል።
ከመንግሥታዊ አገልግሎታቸው በተጨማሪም፣ በተለያዩ ጊዜያት ከግሪካውያን ጋር በመሆን የሸክላ ጣሪያ በማምረትና በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ይታወቃል። ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ አለቃ ነገደ እስራኤል የተባሉ መምህር ቀጥረው ከመንደሩ ለተውጣጡ ልጆች ነፃ የአማርኛ ትምህርት እንዲያገኙ አድርገዋል።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ‹‹ነጋድራስ ተሰማ የአማርኛን ውበትና ውስጠ ምስጢር በተሰጥኦ የተካኑ፣ የቋንቋውን ብልት ተንትነው የበለቱ፣ ሰዋሰውስ የሸዋ ሰው የሚያሰኙ ነበሩ›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል። የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አደርኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና አረብኛ ቋንቋዎችን ይናገሩ ነበር።
የአየር ኃይል አብራሪ የነበረው ልጃቸው መቶ አለቃ ኤልያስ ተሰማ በአውሮፕላን አደጋ መሞቱን ሰምተው ደንግጠው ሲታከሙ ቆዩ። በአንጎላቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱና የልሳን ማዕከላቸው በመጎዳቱ የመናገር ችሎታቸው ቀንሶ ለአምስት ዓመታት በሕክምና ላይ ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 3 ቀን 1957 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
አንተነህ ቸሬ