በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ትልቅ አሻራ ያላቸው ገናናው ንጉሰ ነገሥት አፄ ዘርዓያዕቆብ ያረፉት ከ551 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት (ጳጉሜ 3 ቀን 1460 ዓ.ም) ነበር። ከመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል በገናናነታቸው ከሚጠቀሱት አንዱ አፄ ዘርዓያዕቆብ እንደሆኑ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር የታሪክ ጸሐፍት ይስማማሉ።
በናፓታ ፒያንኪ ፪ኛ፣ ቲሃርቃ፣ ሻባካ፤ በመርዌ ናስቶስኔን፣ ሀንዲው አብራ፣ ህንደኬ፤ በአክሱም ኢዛናና ካሌብ፤ በሮሃ ደግሞ እነላሊበላ ገናና ነገሥታት እንደነበሩት ሁሉ ከሸዋ ነገሥታት መካከል ደግሞ አፄ ይኩኖአምላክ፣ አፄ ዓምደጽዮንና አፄ ዘርዓያዕቆብ በስመጥርነታቸው የሚጠቀሱ ነበሩ።
‹‹ኢትዮጵያ የሕዝቦች ሙዚየም ናት›› በሚባለው ንግግራቸው የምናውቃቸው/የምናስታውሳቸው ጣሊያናዊው የታሪክ ጸሐፊ ኮንቴ ሮዚኒ፣ ስለ አፄ ዘርዓያዕቆብ በጻፉት መጽሐፋቸው፣ ‹‹አፄ ዘርዓያዕቆብ በመካከለኛው ዘመን ከነገሱትና እስከ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ድረስ ከነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዋነኛው ንጉሥ ናቸው›› በማለት ገልጸዋቸዋል። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ኢትዮጵያን ካስተዳደሯት መሪዎች መካከል ሕግና ሥርዓት በማበጀት እንዲሁም በርካታ መጽሐፍትንና አጫጭር ሕግጋትን በመጻፍ አጼ ዘርዓያዕቆብ ዋነኛው እንደነበሩ ይገልፃሉ።
አፄ ዘርዓያዕቆብ በዘመናቸው ለቁጥር የሚታክቱ ትልልቅ ተግባራትን አከናውነዋል። አዳዲስ የሆኑ በርካታ የቤተ-መንግሥትና የቤተ-ክህነት አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን አስተዋውቀዋል። አስደናቂ የፍልስፍና ሃሳቦችንም አፍልቀዋል። ቀደም ሲል የተለመዱና ይዘወተሩ የነበሩ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀሩ ህግጋትን አውጥተው ተግብረዋል። ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ነገሥታት ያልሞከሯቸውን ድንጋጌዎችና የአሰራር ስርዓቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርገዋል። የታሪክ ጸሐፊዎች ‹‹የአፄ ዘርዓያዕቆብ የሕግ አወጣጣቸው የዘመናዊ አስተሳሰብ ባለቤት እንደነበሩ ያሳያል›› ይላሉ።
ለበርካታ ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የኢትዮጵያን የቤተ-መንግሥት የሹም ሽር አወቃቀር ስርዓት አሻሽለውታል። የፍርድ ስርዓቱንም ሆነ አጠቃላይ የማዕረግ ስሞችንና መንግሥታዊ አወቃቀሮችን ዘመናዊ ማድረግ የቻሉት አፄ ዘርዓያዕቆብ፣ የመንግሥት ስርዓታቸውና አወቃቀራቸው ሁሉ ከቀደሙት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ የተለየ እንደነበር በታሪክ ተፅፏል።
በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን የያዙ ብዙ ሴቶች ነበሩ። ከነዚህም መካከል መድኅን ዘመዳ፣ ብርሃን ዘመዳ፣ ድል ሰምራ፣ አመተጊዮርጊስ፣ ሶፍያና አጽናፍ ሠምራ የሚባሉት ሴቶች ተጠቃሽ ናቸው።
አፄ ዘርዓያዕቆብ በአንድ በኩል እጅግ ሲበዛ ብልህ፣ ክርስቲያንና ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የነበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቅጣታቸው ከባድና አደገኛ የሆኑ ሰው ነበሩ። የተመሰከረላቸው የጦር ሜዳ ጀግናም ነበሩ። ስርዓተ ንግሳቸው የተፈፀመው ንጉሥ ተብለው ከተሾሙ ከአራት ዓመታት በኋላ ለየት ባለና ደማቅ በሆነ ስርዓት ነበር። ስርዓተ ንግስናቸውን ለመፈፀም አክሱም በደረሱ ጊዜ የአካባቢው ሕዝብና ካህናት በደስታ ተቀበሏቸው። የትግራይ ሹማምንትና ወታደሩ በፈረስ ሆነው፣ ጋሻና ጦራቸውን ይዘው፣ ሴቶች እየዘፈኑ የአክሱም ንቡረ እድ በቀኝና በግራ ሆነው እንደልማዳቸው የወይራ ዝንጣፊ ይዘው ተቀበሏቸው። ጥር 21 ቀን 1433 ዓ.ም ስርዓተ ንግስናቸው በደማቅ ስርዓት ተፈፀመ። ወደመናገሻቸው ወደሸዋም ሲመለሱ አብያተ ክርስቲያናትን እያስገነቡና ሹመት እየሰጡ ነበር።
አፄ ዘርዓያዕቆብ በጥንቱ ዘመን ከግሪክና ከሮም መንግሥታት ጋር ብቻ ተወስኖ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ወደ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታትም እንዲሰፋ ጥረት አድርገዋል። በዘመናቸው በተለያዩ ጊዜያት የሸፈቱባቸውንና ‹‹አልገብርም›› ብለው ያስቸገሯቸውን ባላባቶች አሸንፈው ከባድ ቅጣት እንደቀጧቸውም ታሪካቸው ያስረዳል።
አፄ ዘርዓያዕቆብ ለ34 ዓመት ያህል በዘለቀው ስልጣን ዘመናቸው ከጠላቶቻቸው ጋር ያደረጓቸውን ጦርነቶች ብልሃትና ጀግንነት በታየበት ስልት ያሸነፉ፣ ባዕድ አምልኮን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የጣሩ፣ ግጭትን በጋብቻ ለማርገብ የሞከሩ፣ የቤተመንግሥትና የቤተ ክህነት ሕግጋትን እንዲሁም የስጋዊ አስተዳደር አዋጆችን ከቀድሞው የበለጠ ያሻሻሉና አዳዲስ ድንጋጌዎችን የጨመሩ፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጹ፣ በርካታ መጻሕፍትን የፃፉ … ገናና ንጉሥ ነበሩ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
አንተነህ ቸሬ