ያልተሰበሰቡ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ከብክነት መከላከል እንደሚገባ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በወቅታዊ የግብርና ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ በክልሉ በሰብል ከተሸፈነው 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ሰብል ብቻ ነው የተሰበሰበው፡፡
ስለሆነም አርሶ አደሩ ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽኖችን ሳይጠብቅ ባለው ጉልበት ያልተሰበሰቡ ሰብሎችን በአግባቡ እና በወቅቱ በመሰብሰብ ሰብሉን ከዝናብና ከብክነት ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
ዶክተር ሰለሞን አክለውም በክልሉ ያለውን የገጸ-ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ አማራጮን በመጠቀም ሰብልን በማልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው የመስኖ ልማት ስራን በተደራጀ ሁኔታ ለማልማት የሚያግዙ የግብዓትና የጸረ ተባይ መድሃኒቶችን ለአርሶአደሩ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ ባለፈው አመት ከለማው 8 መቶ 37ሺ ሄክታር በተጨማሪ በዚህ አመት 2መቶ 20 ሺ ሄክታር መሬት በአዲስ እለማ ነው ብለዋል፡፡
ከመስኖ ልማቱ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ሐብት ስራን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት እና የተራቆቱ መሬቶችን በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለመሸፈን የሚያስችሉ ስራዎች በቀጣይ ቀናት ይጀመራሉ ብለዋል ሲል የዘገበው አብመድ ነው፡፡