በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ በተዘጋጁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና የማስፈጸሚያ ህጎች ላይ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ለኦሮሚያ ብ/ክ/ መንግስት የከተማ አመራር በአዳማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ጋር በመተባበር በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ በተዘጋጁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና የማስፈጸሚያ ህጎች ላይ ያዘጋጀው ይህ ስልጠና በየጊዜው እያደገ ያለውን የከተማው ህበረተሰብ የመልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ የሚችል የአመራር ቁመና የተላበሰ አመራር ለመፍጠር ነው ተብሏል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ ስልጠናውን በንግግር የከፈቱ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2007 እና 2010 በጀት ዓመት ከሁሉም ክልል ለተውጣጡ 9121 የሚደርሱ የከተማ አመራርና ባለሙያዎች በሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች አስልጣኝነት በዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ በ7 ማዕከላትና ዩኒቨሪስቲዎች ስልጠና መስጠቱን ገልፀው በያዝነው የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ለሁለተኛ ጊዜ በሴክተሩ የተያዙትን ዋና ዋና ግቦች በማሳካት በከተሞች መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ከተሞቻችን ለኢንቨስትመንት እና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል ከልማታዊ መንግስታችን መርህ ጋር የተጣጣመ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ያለው ብቁ የሆነ የከተማ አመራርን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ማብቃትና ማሰማራት ወሳኝ በመሆኑ በየወቅቱ የከተማ አመራር አቅም መገንባት ወሳኙ ነው ብለዋል።
የአምስተኛው ዙር የከተማ አመራሮች ስልጠና በአራቱም ዋና ዋና ክልሎች ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ እየተተገበረ ሲሆን ዛሬ በአዳማ የተጀመረው ስልጠናም የዚሁ አካል ነው ተብሏል።
እንደ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ስልጠናው እስከ ታህሳስ 19/2011 ለ1ኛ ዙር ሰልጣኞች የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ዙርም በቀጣይ የሚሰጥ ይሆናል።