ሀገራችን የበርካታ የተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ባለቤት በመሆኗ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንዳለብን አሁን የአለንበት የልማት ደረጃ አመላካች ነው። እናም የአማራ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴም ከሀገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ብዙም ያልተለየ ስለሆነ የቱሪዝም ሀብቶቹን በተለያየ መንገድ ያስተዋውቃል። እኛም ከቱሪዝም ቢሮ ያገኘነውን መነሻ አድርገን ሁለቱን ቦታዎች ልናስተዋውቅ ወደናል።
ጮቄ ተራራ
የጮቄ ተራራ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኝ ተራራ ነው∷ የጮቄ ተራራ ከባህር ወለል በላይ በ4413 ሜትር ከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ተራራ በሰሜን ምሥራቅ ከሁለት እጁ እነሴ፣ በምሥራቅ ከእናርጅ እናውጋ፣ በደቡብ ምሥራቅ ከደባይጥላት ግን፣ በደቡብ ስናን፣ በምዕራብ ማቻከል፣ በሰሜን ምዕራብ ደጋዳሞት እና በሰሜን ቢቡኝ ከሚባሉ የዞኑ ወረዳዎችን ሲያዋስን በምዕራብ ደጋዳሞት እና በሰሜን ቢቡኝ ከሚባሉ የዞኑ ወረዳዎችን በዋናነት ያካልላል።
የጮቄ ተራራ በዞናዊ አቀማመጡ ከዞኑ ምዕራባዊ ጫፍ ላይ ይገኛል። በዞኑም የስናን ደባይጥላት ግን፣ ሁለት እጁ እነሴና ቢቡኝ ወረዳዎችን በዋናነት ይነካል። የጮቄ ተራራ ከ373 ትናንሽና ትላልቅ አባይ ገባር ወንዞች ከስሩ ያመነጫል። ተራራው ከፍተኛ ቅዝቃዜ አለው። በተለይም በክረምት ወራት ለተወሰኑ ሳምንታት በበረዶ ተሸፍኖ ይቆያል። የጮቄ ተፈጥሯዊ መልክዓምድር በጣም ሳቢ ውብና መንፈስን የሚማርክ የተፈጥሮ ገጸበረከት ነው። በአካባቢው የተለያዩ ሀገር በቀል እጽዋት ይገኛሉ።
ጮቄ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ገና ብዙ ያልታወቁ ዋሻዎች፣ጥንታዊ መኖሪያዎች ያሉበት ስፍራ ነው። የጮቄ ተራራ በስሩ ያካተታቸው ወረዳዎች መሠረት አድርጐ በተለያዩ ክፍሎች ከፍሎ መቃኘት ይቻላል። በዚህ ሊጠቀስ ከሚችሉት አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ አራት መከራክር አንደኛው ነው። አራት መከራክር በስናን ወረዳ ከረቡዕ ገበያ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ ይገኛል። አራት መከራክር እንደስያሜው አራት በተለያየ ቁመት ከደቡብ ምሥራቅ ወደ ሰሜን
ምሥራቅ መስመር ሰርተው የቆሙ ሰንሰለታማ ኮረብታዎች የጋራ ስያሜ ነው። የአራት መከራክር አካባቢና ጮቄ ተራራ በአካባቢው በሚበቅሉ የአስታ፣የግምይ እና የጅብራ ዛፎች አረንጓዴያማ ቀለም የደመቀ ነው።
በከፍታው የመጀመሪያውና ትልቁ እናት አምባ ሲሆን፤ በአቀማመጡም ከወደ ተራራው ከፍተኛ ክፍል ባለው የኮረብታዎች መስመር ጫፍ ይገኛል። ይህ ኮረብታ ከትልቅነቱ በተጨማሪ በሥሩ የመድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን ፀበል እና ወረድ ብሎ ንጉስ ላልይበላ የጀመረው ነው የሚባል ፍልፍል ጅምር ይገኝበታል። እናት አምባ ተራራ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ለመሄድ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ይወስዳል። ጫፉ ላይ ዱር፣ ገላጣ፣ ሜዳማና አለታማ መሬት
አለው። ጫፍ ላይ ወጥቶ ወደታች ማየት እጅግ የሚያስደስት ተፈጥሮን የሚቃኝበት ቦታ እንደዚሁ ምሥራቅ ጐጃም መርጦለማርያም አካባቢ አባማኒዎስ ተራራ አለ።
ፎቶ፡
ሰከላ ከባህርዳር ደቡባዊ ምዕራብ 165 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የወረዳዋ ርዕሰ ከተማ ግሽ አባይ የምትባል ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ 430 ኪሎሜትር ከምትገኘው ቲሊሊ ከተማ 30 ኪሎሜትር ገባ ብላ የምናገኛት ነች።
የሰከላ ወረዳ የአባይ ወንዝ መነሻ እንደሆነች ይነገርላታል። ግሽ በሚል መጠሪያ ከሚታወቀው ተራራ ያለው ረግረጋማ መሬት የዚህ ትልቅ ወንዝ ምንጭ እንደሆነም ይታመናል። የወንዙ አነሳስ በፀበል አንድ ቦታ በፈነዳ ምንጭ ይጀምርና በዝቅተኛ መጠን በሚንቆረቆር ወራጅ ውሃ ይቀጥላል። ይህ ወራጅ ውሃ አምስት መቶ ሜትር በማይሞላ ርቀት በአንድ እርምጃ የሚዘለል ቦይ ይፈጥርና ከ500 ሜትር በኋላ ሦስት ሜትር ያህል ሰፍቶ ሌሎች ገባሮችን አሰባስቦ ግልገል አባይ (ወተት አባይ) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትንሹ አባይ በመባል በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ጣና ሐይቅ ይወርዳል። ከዚያ ሐይቁን ከተቀላቀለ በኋላ አቋርጦ ይነጉዳል።
የአባይ ወንዝ መነሻ እንደሆነ የሚነገርለት ወራጅ ውሃው በፈዋሽ ፀበልነትም ይታወቃል። እናም ይህ ስፍራ የተለያዩ ዋሻዎችንም በእቅፉ ከቶ የሚገኝ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለርዕሳችን መነሻ የሆነው አባግስ ግንብ እየተባለ የሚጠራ የሕንፃ ፍርስራሽ ነው። ይህ ፍርስራሽ የተለያየ መጠሪያ ያለው ሲሆን፤ አብስከን ማርያም ቀበሌ የፋሲል ግንብ እያሉ ይጠሩታል። የሚገኘው አብስከን ማርያም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ከወረዳው 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።
ሰከላ ወረዳ ከፍርስራሹ 15 ሜትር ገባ ብሎ ሦስት ሜትር ከፍታ ያለው ጣራ አልባ ቤት አለ። ከዚህ ቤት 20 ሜትር ርቀት ላይ በተመሳሳይ ቅርጽ ተሰርቶ የፈረሰ ቤትም ይገኛል። ይህ ደግሞ የፋሲል ግንብ እንደሆነ ይነገራል።
አጼ ፋሲል በንግስና ዘመናቸው ከአባታቸው ከሱሲኒወስ የሥልጣን በትር እንደተረከቡ መቀመጫቸውን ከጐንደር ወደ ጐጃም ለማድረግ አሰበው ስለነበር ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የቀረ ቤተመንግሥት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እናም ይህንን ታሪካዊ ምድርና የቱሪስት መናኸሪያ የሆነን ቦታ ጎብኙ ብለን በመጋበዝ ለዛሬ አበቃን።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/ 2011
ጽጌረዳ ጫንያለው