የነሐሴ ወርን ጠብቆ የሚመጣው የልጃገረዶች የነፃነት በዓል የማይረሳ ትዝታ አለው። በዓሉ በተለያየ መልኩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በድምቀት ሲከበር የቆየ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን። ዘንድሮም በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ዝግጅት ሲከበር ቆይቷል∷ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማም የክልሉ ነዋሪ ልጃገረዶች የበዓሉን ማጠቃለያ በልዩ ድምቀት አክብረውታል። በወቅቱ ደግሞ የተለያዩ ጥናቶች በጉዳዩ ዙሪያ ቀርበዋል። እኛም ይህንን መነሻ አድርገን እንዲህ አቅርበነዋል።
ክብረ በዓላቱ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚከበሩ አይደሉም። በወል የታወቁትን ለማንሳት ካልሆነ በስተቀር። ስለዚህም አሁን በስፋት የሚከበሩትን ስናነሳ በዋግ ኽምራ ሻደይ፣ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በቆቦ አካባቢ ሶለል፣ በጎጃም ከሴ፣ እንግጫ ነቀላ፤ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ዓይነዋሪ እየተባለ ይከበራል። እናም ይህ ስያሜ እንዴት ተሰጠው ከተባለ ምክንያቱ ልዩ ልዩ እንደሆነ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል መምህር የሆኑት ዶክተር ዋልተንጉስ መኮንን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደገለጹት፤ የአዳም ከገነት መባረር፣ ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ ከድንግል ማርያም ፍልስታ፣ ከመስፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር ተሳስሮ ይከበራል። ከዘመን መለወጫ ጋርም በተያያዘ መከበር እንደተጀመረ ይነገራል። ለአብነት ሁለቱን ብናነሳ የአዳም ከገነት መባረርን እና የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ መዳን ምሳሌ እንደሆነ ማየት ይቻላል። ከአዳም ጋር ያለው አዳም ሕግ በመተላለፉ ጸጋ ርቆት እርቃኑን በሆነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን ቅጠል ተጠቅሟል። ልጃገረዶችም እንዲሁ ቅጠል በወገባቸው ላይ አገልድመው ያንን ጊዜ በማሰብ ያከብሩታል ይላሉ።
ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ጋርም እንዲሁ ምሳሌ መኖሩን የሚናገሩት ዶክተር ዋልተንጉስ፤ ልጃገረዶች በወገባቸው ላይ የሚያደርጉት ቅጠል ውኃው የመጉደሉ ምልክት ነው። ወደ ኖኅ ርግብ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት በምድር ሰላም እንደሆነ አብስራለች። ልጃገረዶችም ቢሆኑ ይንን ክብረበዓል ሲያከብሩ በየቤቱ እየተዘዋወሩ አገር ሰላም መሆኑን ያበስራሉ። ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን እያሉም ብስራቱን እየዞሩ ለአካባቢው ሰው ይናገራሉ።
ይህ በዓል ሁለት ትልልቅ ጉዳዮችን አቅዶ የያዘ እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተር ዋልተንጉስ፤ የምስጋና ቀናት እና የሽግግር ወቅት ማስጠንቀቂያዎች የሚያሳይ በዓል መሆኑንም ይገልጻሉ። በዓሉ ከምስጋና አንጻር ሲታይ ለመልካም ተግባራት ምስጋና የሚያቀርቡባቸው፣ ለሰው ልጅ ህልውና፣ ኑሮና ደህንነት መሠረት የሚሆኑ ታሪኮችና ገድሎች የሚዘክሩባቸው የትውስታ ቀናት መሆናቸውንም ያብራራሉ። ለሰው ልጅ ሕይወት መከራን የተቀበሉ፣ መስዋዕት የከፈሉ፣ ቤዛ የሆኑ፣ መከራን ያሻገሩ፣ ዕርቅን ያመጡ ሰዎችን ገድልና ታሪክ እየዘከሩ ቅንነትን፣ መልካምነትን፣ የሚተክሉ ባህላዊ እሴቶች የሚገነቡባቸውም መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ከሽግግር ወቅት ማስጠንቀቂያነታቸው አንጻርም ይህ በዓል ብዙ ነገሮችን እንደሚያመላክት የሚናገሩት ዶክተር ዋልተንጉስ፤ በእያንዳንዱ የሕይወት ጎዳና ላይ ያሉ ልዩ ልዩ የሕይወት ምዕራፎች በመሞትና በመወለድ የተገደቡ መሆናቸውን እየነገሩን ያስጠነቅቁናል። መንታና ተጻራሪ ሆነው የቆሙ ሁለት ጫፎች መኖራቸውንም እየነገሩን ይዘውን ይጓዛሉ። ስለዚህም ማህበረሰባችን ከዚህ ባህሉና የበዓል ከበሬታው እየተጀመረ የሚያልቀውን፣ ደረጃ በደረጃ የሚሸጋገረውን ነገር እየተረዳ እንዲሄድ ያደርገዋል። መሸጋገር ሲኖር ማስጠንቀቂያውን እያየ አቅጣጫውን አስተካክሎ እንዲራመድም ዕድል ይሰጠዋል ይላሉ።
ከተለያዩ ሚናዎችና የተፈጥሮ ባህርያት ጋር የሚያላምዱንና የሚያስተዋውቁን ውስብስብ የሆኑ ግን በባህል የሚብራሩና እያንዳንዱን ደረጃ ግልጽ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ዓይነት የክብር ሥርዓቶችን የሚያስተናግደውም ከዚህ አንጻር እየቃኘ ነው። ለዚህ ደግሞ ተፈጥሮን ተመርኩዞ የሚከበረው የልጃገረዶች በዓል በዋናነት የሚወሰድ መሆኑንም ይናገራሉ።
በየልጃገረዶች በዓል ብዙዎች የሚስማሙትና ልጃገረዶችም የሚያውቁት ከእምነት ጋር ተያይዞ ያለውን እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር የሆኑት ዶክተር አጸደ ተፈራ ናቸው። እርሳቸው እንዳነሱት፤ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ሔዋን ከ5500ዘመን በኋላ ነፃ እንደሚያወጣቸው በገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት በሔዋን ስህተት ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ በድንግል ማርያም አማካኝነት ከኃጢያት ባርነት ነፃ ወጣ። እናም ልጃገረዶች ነጻነን ሲሉ ይህንን በዓል የነፃነት ቀን አድርገው ያከብሩታል።
ድንግል ማርያም የተፈቀደላትን ዕድሜ በምድር ከኖረች በኋላ ሞተ ሥጋን ፈጽማ ብዙም ሳትቆይ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ አረገች፤ ይህንን እርገቷን በማሰብም እንደሚያከብሩት ይነገራል። ማንኛዋም ልጃገረድ ለምን ይህንን በዓል ታከብሪያለሽ ብትባል እርገቷን ወይም ትንሳኤዋን ለማክበር የሚል መልስ ነው የምትሰጠው።
የወል የሆኑ የማህበረሰብ የጋራ ታሪኮች የሚሰበኩባቸው፤ ማኅበራዊ ሥርዓት የሚጠበቅባቸውና የሚታደሱባቸው፤ለሁነቶች ያለን ውዴታ እና ጥላቻ የሚገለጹባቸው ቀናት ቢኖሩ እነዚህ የአደባባይ የልጃገረዶች በዓላት ናቸው ይላሉ ዶክተር አጸደ፤ በዓላቱ በደረጃ ቅየራ ምክንያት የሚፈጠርን የሚና ለውጥና የስነልቦና መሸበር ለመፈወስ የሚረዱ ናቸው። ልዩ ልዩ የማዝናኛ፣ የማረጋጊያና ከአዲሱ ሁኔታ ጋር የማስተዋወቂያ መድረኮች በመሆን እንደሚያገለግሉ ያብራራሉ።
በሰው ልጅ የዕድገት ዘመን ውስጥ ልጅነት ለተፈጥሮው ቅርብ በመሆኑ በንጽሕና፣ በቅንነት፣ መልካም የሆነው ነገር ሁሉ በዝቶና ተትረፍርፎ የሚገኝበት ተደርጎ ይታሰባል። በዚህም በልጅነት ይህንን ቅን ምልከታ ይዞ በየቤቱ ሲኬድ በረከት ይሞላል ተብሎ ስለሚታመን በዓሉ በልጃገረዶች መምጣት እንዲደምቅ ይደረጋል። ልጃገረዶች ደስተኛ ሆነው እንዲውሉም ይፈቀዳል።
የእንቁጣጣሽ ምስጢርን «ምድር ጭቃ ከሆነች በኋላ ብዙ ዐይነት ቡቃያና ተክል ማስገኘቷን ያሳያል» በማለት ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ላይ ገልጸውታል። በዚህም ይህ ጊዜ እህሉ እያዘረዘረ፣ እያፈራ ሄዶ በፀሐይ ዘመን እየቀላና እየበሰለ ይመጣል። ምድር ጸጉሯን ተላጭታ ያለልብስ ርቃኗን ትቆያለች። ከዚያም፣ በክረምት፣ ማዕት ወርዶ ምድርም ጨቅይታ ያንን የደረቀውንና የተራቆተውን አርሳና አበስብሳ፣ አጥባና አለቅልቃ ስታነጻው በዚህ ጊዜ ዓመት ይሞትና ውልደቱን በአዲስ መስከረም ላይ ይጀምራል።
ይህን ምሳሌ ተደርጎም ልጃገረዶች ይህንን በዓል ሲያከብሩ የተለያዩ ደረጃዎችን እንደሚያልፉ ይነገርበታል። ምክንያቱም ይህ በዓል መታጫና ለትዳር መጠየቂያም ጊዜ ነው። ስለዚህም ካላገባ ወደ አገባ፤ ከብቸኝነት ወደ ቤተሰብ ምስረታ የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ብዙ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸውም የሚያውቁበት ጊዜ ነውና የሽግግር ጊዜ ተደርጎም ይታሰባል።
ይህ በዓል ማህበራዊ ፋይዳው በጣም ትልቅ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አጸደ፤ በሕይወት መንገዳችን እንደ እንግጫ የተተከለብንን ጥላቻ፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ራስ ወዳድነት አረም የምናስወግድበትና ሰላም የሚሰበክበት፣ ሀብታምና ድሃ የማይለይበት እንዲሁም ህሊናን ለመልካም ቡቃያ የሚዘጋጅበት እንደሆነ ልጃገረዶቹ በሚያደርጉት ጨዋታ ይመሰክራሉ። ለምሳሌ አበባ ለማንም አይሰጥም ለሚወዱት እንጂ። እናም በዘፈናቸው ሁሉ ለምለምነትን ሳያነሱ አያልፉም።
አበባዬ ነሽ አበባዬ
ካፋፉ ዘልቀሽ እልል በይ
ሻደይ አበባዬ ሻደይ።
ሻደይ ነሽ አሉ
በያገሩ።
አሸንድዬ አሽንዳ አበባ፣
እርግፍ እንደወለባ፣
አደይ አበባ አደይ አበባ።
አደይቱ መስከረሚቱ
መውደድ እንደሌሊቱ። እያሉ ያዜማሉ። ይህ ደግሞ የሚያሳየው አበባንና መስከረምን ሁሉም ሰው እንደሚናፍቀውና እንደሚመኘው ነው። የልጃገረዶች ጨዋታ ነሐሴ ግም ሲል የሚጀምር ሲሆን፤ መነሻው በአቅራቢያቸው የሚገኝ ቤተክርስቲያን ነው። እናም በዚያ ሲሄዱ ደብሩን በተለያየ መልኩ ያሞግሳሉ። ለምሳሌ ከሚያዜሙት ውስጥ፡-
ተወረወረች ጨረቃ
በመድሃኒዓለም ጫንቃ።
ተወረወረች ኮከብ
በጊዮርጊስ ክበብ። ካሉ በኋላ የቤተክርስቲያን ምርጫ እንደሌላቸው ለመናገር ደግሞ እንዲህ ይላሉ።
ቤተክርስቲያኑን ሁሉ ዝም ብዬ እሳለማለሁ
ወይብላናት ሲሉኝ ዝም ብዬ እሳለማታለሁ ።
አንቺ ወይብላ ማርያም ሲሊቱ ሲሊቱ
አደራ አባቴን አደራ ስለእኔልጅቱ። እያሉ ታቦታቱን ይዘረዝራሉ። ያመሰግናሉ፤ እንዲጠብቋቸው ይማጸናሉ። ከዚያ በአካባቢ ትልቅና ክብር የሚሰጣቸው ሰው ቤት ያመራሉ። በዚያም ሲደርሱ እንዲህ እያሉ ያሞግሳሉ።
አሸንዴ ስልህ መሽቶብኝ
እባክህ በረኛው አስገባኝ። እያሉ ወደውስጥ ለመግባት ይጠይቃሉ። ከዚያም
እውዬ እዋውዬ
ከአሽከር ተዋውዬ
ቤቶች አሉ ብዬ
መጣሁ ሰተት ብዬ
ይሄ ቤት እህ
የማነው በወርቅ የነደደው
የአባባ ይሆን ወይ
መስጠት የለመደው። ይላሉ∷ ከገቡ በኋላ ደግሞ
ሎሚ ወድቆብኝ በስተኋላዬ
እስኪ አንሻት እስኪ አንሻት ባልንጀራዬ
የጌትዬ በቅሎ አትበላም ገለባ
አስለምደዋታል አሸንድዬ ወለባ።
የአንተ ቤት አቀበት የእኔ ቤት ቁልቁለት
ሆነልኝ በራልኝ እንደብር ቀለበት።
ስብር ብር እንደአገዳ ስብርብር እንዳአገዳ
የመውደድ እንግዳ
ያይሻል በአጥሩ ቆሞ ያይሻል በአጥሩ ቆሞ
ፈረሱን አስለጉሞ።
የሚፈልጉትን አግኝተው ሲወጡ ደግሞ እንዲህ እያሉ ያሞግሷቸዋል።
አሸንዴ ሸብ ሸብ ከፈረስ አፍንጫ ይውላል ትንኝ
የእዚህ ቤት ባለቤት ጤና ይስጥልኝ።
እኛም በእነርሱ የጭፈራ ዜማና ግጥም ጤና ይስጥልን በማለት ተሰናበትን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/ 2011
ጽጌረዳ ጫንያለው