የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የቀብር ስነስርአት ረቡዕ ከቀኑ በ9 ሰዓት በቅድስት ስላሴ እንደሚፈፀም ተገለፀ።
የብሔራዊ ቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሰጡት መግለጫ የቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የቀብር ስነስርአት ረቡዕ ታህሳስ 10/2011 ዓ.ም ከቀኑ በ9 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን የሚፈጸም መሆኑን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ብርቱካን በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በታታሪነት እና በብቃት ያገለገሏትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንቷን ግርማ ወልደጊዮርጊስን በሞት አጥታለች ብለዋል።
አክለውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለ 12 ዓመታት በርዕሰብሄርነት ያገለገሉ እና በልዩ ልዩ ሃላፊነት ለአገራቸው ረዥም ዘመን የሰሩ በእውቀታቸው እና በሞያቸው ለህዝባቸው የበጎ አገልግሎት የሰጡ የታታሪነትና የህዝባዊ አገልግሎት ሰጪነት ምሳሌ ሆነው እስከ ዕለተ ህልፈታቸው አገልግለዋል ብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ባደረባቸው ህመም በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ቆየተው ታህሳስ 05 ቀን 2011 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡30 አርፈዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የቀብር ስነ-ስርዓት ረቡዕ ታህሳስ 10/2011 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወገኖቻቸው በተገኙበት እንደሚፈጸም አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሯ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስክሬን ከመኖሪያ ቤታቸው ተነስቶ ኢትዩጵያውያን እኝህን የአረንጓዴ ልማት አርበኛ መሰናበት የሚችሉበት ቦታ እየተዘጋጀ መሆኑን እና ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ለህዝብ የሚገለጽ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለክብራቸው እና ለሚወዷት እናት ሀገራቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ የሚመጥን የቀብር ስነ-ስርዓት ለማከናወን 11 አባላት ያሉት ብሄራዊ ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከመከላከያ ተውጣጥቶ መቋቋሙን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ለማወቅ ተችሏል።