“ህዝብ እንደ ህዝብ ሊጣላ አይችልም ከፍቅር ውጪ የሚያውቀው አጀንዳ የለውም” ሲሉ የኢህዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር እና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።
4ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሴቶች ሊግ ጉባኤ በትግራይ ክልል መቐሌ ከተማ በመካሂድ ላይ ነው።
በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙት የሊጉ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ጉባኤው አገሪቱ በጀመረችው የለውጥ ሂደት ላይ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በአገሪቱ አሁን እየተካሄደ ባለው ለውጥ በአንድ በኩል ተስፋ በሌላ በኩል ጠንካራ ትግል የሚጠይቅ ፈታኝ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
”የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ ራስን ማየት እና ከችግሩ ጋር ባለመደራደር ከችግር ተላቆ ወደ ፊት በመገስገሰ ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ይገባል” ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪያት።
በማህበራዊ፣ አኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች እየተገኙ ያሉ ድሎች እንዲቀጥሉ የተገኙ ውጤቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲፈታው ጠይቀዋል።
የሴቶች ተፈጥሯዊ ባህሪ ለሰላም የቀረበ በመሆኑ ሴቶች ሁለተኛ የሚባል አማራጭ እንደሌለ ተገንዝበው ለሰላም መምጣት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
”የጥላቻ መርዝ ስካር እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አንዳችን ወደ ሌላችን ጣታችንን መቀሰር ትተን ወደ ራሳችን ከተመለከትን አሳሳቢ ቢሆንም የማንሻገረው ችግር የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
በጉባኤው በክብር እንግድነት የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ሴቶች ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲከበር ሰላማዊ ትግል ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
”ትልቅ መስዋትነት የተከፈለበት ህገ መንግስታችንን ለማፍረስ ከውስጥም ከውጪም እየተደረገ ያለውን ዘመቻ በተግባር የተረጋገጡትን የሴቶች መብቶችና ጥቅሞች የሚንዱና የሚጎዱ በመሆኑ ልክ እንዳለፈው አኩሪ ታሪካችሁ ትክክለኛ መስመር በመሰለፍ ተገቢ ትግል ማካሄድ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን።” ብለዋል።
ትክክለኛውን መስመር በመያዝ ህዝቡን በማሰለፍ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።