‹‹ከእግር ኳስ ደጋፊዎች 50 ሺህ 315 ብር ተሰብስቧል፤ የተሰበሰበው ገንዘብ በማረሚያ ቤት ከፍተኛ የአካል እና የስነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰበት ለአቶ ዮሀንስ ጋሻው እና ለተፈናቃዮች የሚውል ነው፡፡›› የባሕርዳር ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማሕበር
የባሕር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር በባሕር ዳር አለማቀፍ ስታዲዮም ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉና በማረሚያ ቤት ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እርዳታ የሚሆን ገንዘብ አሰባስቧል፡፡
አብዛኛውን ድርሻ ከባሕር ዳር ከነማ ደጋፊዎች የተገኘ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ቡና እና ከባሕርዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች 50 ሺህ 315 ብር ተሰብስቧል፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ በማረሚያ ቤት ከፍተኛ የአካል እና የስነልቦና ጉዳት ለደረሰበት አቶ ዮሀንስ ጋሻው የሚውል እንደሆነ ነው ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው፡፡
የባሕር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ሂሳብ ሹም አቶ ቢኒያም ላቀው አንደነገሩን አቶ ዮሀንስ አፋጣኝ ህክምና ስለሚያስፈልጋቸው እና ከፍተኛ የህክምና ወጪ ስለተጠየቁ ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖችም እርዳታ ይደረጋል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ቢኒያም ገለፃ እስካሁን ገንዘብ ሲሰበሰብ በክለቡ ደጋፊዎች ላይ ብቻ የታጠረ ነበር፡፡ አሁን ግን የተፈናቃይ እና የተጎጅዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ከክለቡ፣ከከተማ አስተዳደሩ፣ከባለሃብቶች እና ሌሎች የክለብ ደጋፊዎችን በማስተባበር ለሌሎች ወገኖችም እርዳታውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጦልናል፡፡ ከባሕር ዳር አለማቀፍ ስታዲዮም የመግቢያ ትኬት ሽያጭ የተወሰነ ለሰብዓዊ እርዳታ እንዲለቀቅ እንጠይቃለን ብሏል፡፡
ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ጋር በጋራ በመሆን በቀጣይ በሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ድጋፍ ላይ ስፖርቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ መታሰቡን የዘገበው አብመድ ነው፡፡