በአማራ ክልል ከ9 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ለንብ ማነብ ተስማሚ የሆነ የአየር ፀባይ እና የመልክዓ ምድር አቀማመጥ እንዳለው ይነገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ 1ሚሊዮን 4መቶ 38 ባህላዊ፣የሽግግር እና ዘመናዊ ቀፎ ህብረ ንብ ወይም ደግሞ የንብ መንጋ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የኤጀንሲው የንብና የሀር ልማት ባለሙያ አቶ ሙሀመድ ጌታሁን ለአብመድ እንደተናገሩት ከዘርፉ 25ሺህ ቶን የማር ምርት በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
እስከ ህዳር 30/2011ዓ.ም ድረስ 9ሺህ 1መቶ 89 ቶን የማር ምርት መገኘቱን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ከዘመናዊ ቀፎ 2ሺህ 2 መቶ 40 ቶን ፣ከሽግግር ቀፎ 1ሺህ 91 ቶን እና ከባህላዊ ቀፎዎች 5ሺህ 8መቶ 58 ቶን ነው የተገኘው፡፡
ምርቱ ከፍጆታ አልፎ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ከሱዳን፣ጀርመን እና ኖርወይ ሀገራት ጋር ግንኙነት እየተፈጠረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አብዛኛዎቹ ህብረ ንቦች በባህላዊ ቀፎ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ ከአጠቃላዩ የክልሉ የንብ ሀብት 1ሚሊዮን 321ሺህ 173 የሚሆነው ህብረ ንብ በባህላዊ ቀፎ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡
በተያያዘም ከባህላዊና ከሽግግር ቀፎዎች 2መቶ 84 ቶን የተጣራ ሰም በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አስካሁን 63 ቶን ሰም እንደተገኘ ኤጀንሰው ገልፃል፡፡
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ጥራት ያለው የማር ምርት ለማምረት ምን እየተሰራ ነው በማለት አብመድ ላነሳው ጥያቄም ‹‹ የክልሉ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ለንብ ማነብ ያለውን አመችነት ተጠቅሞ ዘርፉን ለማሳደግ ኤጀንሲው እየሰራ ነው፡፡›› ሲሉ ባለሞያው አብራርተዋል፡