የቤንዚን እጥረቱን ለመፍታት የኩፖን አሰራር መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በዚህ ዓመት ለክልሉ የሚቀርበው የቤንዚን ምርት ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ በወር በአማካኝ የ1.2 ሚሊዮን ሊትር ቅናሽ አለው፡፡
ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በክልሉ ከተሞች የቤንዚን እጥረት ተከስቷል፡፡ በዚህም የባጃጅ አሽከርካሪዎችና ሌሎች ተጠቃሚዎች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በባሕር ዳር ከተማ በመዘዋወር ያነጋገራቸው የባጃጅ አሽከርካሪዎች በተከሰተው የቤንዚን እጥረት የተነሳ ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የቤንዚን ነዳጅ ለማግኘትም እስከ ሁለት ቀናት ድረስ ወረፋ ይጠብቃሉ፡፡ ነዳጅ በጨለማ ከማደያዎች እየተጫነ ወደ ሌላ አካባቢ እየተወሰደ ለጓዳ ገበያ መጋለጡም ችግሩን የከፋ እንዳደረገው ነው ተጠቃሚዎች የነገሩን፡፡
በክልሉ ለቤንዚን እጥረት ምክንያቱ የአቅርቦት እጥረት ነው መኖሩን ንግድ ቢሮ ገልጧል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ወደብ ላይ ነዳጅ በወቅቱ እያቀረበ አይደለም፡፡ በ2010 በጀት ዓመት በየወሩ በአማካኝ 5.7 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን ለክልሉ ይቀርብ ነበር፡፡
በተያዘው ዓመት ግን በየወሩ በአማካኝ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህም በ2010 ከቀረበው በየወሩ የ1.2 ሚሊዮን ሊትር
እንደሚቀንስ ነው የገለጹት፡፡
ወደ ክልሉ የገሚገባውን ቤንዚን ከህገ ወጦች ነጻ አድርጎ ሙሉ ለሙሉ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የኩፖን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ቢሮው አስታውቋል፡፡ በአሰራሩም ማደያዎች የተረከቡትን ቤንዚን በመመዝገብ ተጠቃሚዎች ከንግድ ተቋማት ኩፖን በመውሰድ ግዥ እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡
ነዳጁ ተሸጦ ሲያልቅ ከቀሪ ኩፖኑ ጋር በማመሳከር ትክክለኛነቱ እንደሚረጋገጥም ነው የተናገሩት፡፡ ይህንን አሰራር ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል፡፡
በክልሉ የነዳጅ ማቆያ ግዙፍ ማደያዎችን ለማስፋፋት ደግሞ 10 ባለሃብቶች የግንባታ ቦታ ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል ነው የተባለው፡፡
ለክልሉ የሚቀርበው ነዳጅ 20 በመቶው በሱዳን፣ 80 በመቶው ደግሞ በጅቡቲ በኩል ይገባል፡፡ ይህም በክልሉ ውስጥ ባሉ 176 የነዳጅ ማደያዎች ለተጠቃሚዎች ይሰራጫል፡፡