የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ፤ ከዓለም ህዝቦች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንዳለባቸው ያመለክታል። ከነዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት እንደኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚገኙና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ይገለጻል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ህዝብ መካከል 17 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ወይም 15 ሚሊዮን ሰዎች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፤ በአገራችን ይሄን ያህል ቁጥር ያላቸው አካል ጉዳተኞች ይኑሩ እንጂ፤ በአገሪቱ የሚከናወኑና የተከናወኑ አብዛኛዎቹ መሰረተ ልማቶች ሲታሰቡም ይሁን ሲከናወኑ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ባለማድረጋቸው አካል ጉዳተኞች ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለከፋ አደጋ እና እንግልት ይዳረጋሉ።
ይሄንን የአካል ጉዳተኞችን ድካም እና እንግልት በሚያስተምሩበት ኮሌጅ የታዘቡት አቶ ዘካሪያስ ሲሳይ፤ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ ያለማንም ሰው እገዛና ድጋፍ በፈቀዱት ጊዜ ወደፈለጉት ቦታ መድረስ የሚያስችላቸው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ አውቶማቲክ ዊልቼር ሰርተዋል። እኛም የዚህን የፈጠራ ስራ ባለቤት የሆኑትን አቶ ዘካሪያስን ለዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን እንግዳ ልናደርጋቸው ወደናል።
አቶ ዘካሪያስ ሲሳይ በሐረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኤሌክትሪካል ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፤ ይሄንን የፈጠራ ስራ ለመስራት ያነሳሳቸው በኮሌጁ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ሶስት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ሲቸገሩ በማየታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳብራሩት፤ በኮሌጁ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሶስት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ነበሩ። እነዚህ ተማሪዎች ወደ ኮሌጁ ለትምህርት በሚመጡበት ወቅትና በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ሲዘዋወሩ ደረጃ ለመውረድ፤ ዳገት ለመውጣት፤ እንዲሁም መንገዱ ኮረኮንች ከሆነ በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበትን ዊልቼር ተጠቅመው ለማንቀሳቀስ ሲቸገሩና ሌሎች ሰዎች ዊልቼሩን በመግፋት እንዲተባበሯቸው እርዳታቸውን ሲማጸኑ እንዳስተዋሉ ይናገራሉ።
በተጨማሪም፤ እነዚህ ተማሪዎች እንደ ማንኛውም ተማሪ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ እንደልባቸው ተዘዋውረው፤ የተግባር ትምህርት በሚሰጡባቸው ክፍሎች እና ቤተ መጻሕፍት ገብተው ትምህርታቸውን ለመከታተል ሲቸገሩ በማየታቸው ልባቸው የተነካው አቶ ዘካሪያስ፤ “ለምን እነዚህ ልጆች የሰዎችን ርዳታ ሳይሹና እነርሱም ከፍተኛ ያለድካም በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዊልቼር አልሰራም?” በሚል ቁጭት የፈጠራ ስራውን ለመስራት በ2008 ዓ.ም ቆርጠው እንደተነሱ ገልጸዋል።
አቶ ዘካሪያስ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይሄንን የፈጠራ ስራ በብቃት መስራት የሚያስችላቸውን መረጃ ከኢንተርኔትና ከተለያዩ መጻህፍት ከሰበሰቡ በኋላ ፕሮፖዛል ነድፈው ለኮሌጁ አቀረቡ። ኮሌጁም ያቀረቡትን ፕሮፖዛል ተመልክቶ ወደ ተግባር እንዲቀየር ይሁንታ ሰጣቸው። በ2009 ዓ.ም የፈጠራ ስራውን ከጽንስ ሃሳብ ወደ ተግባር ማሸጋገር እንደጀመሩ ይናገራሉ።
በዚህም አካል ጉዳተኞችን በቀላሉ ያለሰው እገዛ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ አውቶማቲክ ዊልቼር እንደሰሩ የሚናገሩት መምህሩ፤ ዊልቼሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በማይኖርበት ወቅትና ቦታ በባትሪ ድንጋይ እና በፀሐይ ብርሃን መስራት መቻሉ ቴክኖሎጂውን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ለመጠቀም ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ገለጻ፤ የፈጠራ ስራውን የመካኒካል ክፍል ፕላስቲክ፤ ነጭ ፒቢሲ (ማይካ)፤ ጣውላ እና ስፖንጅ በመጠቀም የሰሩ ሲሆን፤ የኤሌክትሪካል ክፍሉን ደግሞ ሁለት ኢሲ ሞተር (በሶላር፤ በባትሪ ድንጋይና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ሞተር) በመጠቀም ለመስራት ችለዋል።
የፈጠራ ስራው ከተለመደው ዊልቼር በምን እንደሚለይ አቶ ዘካሪያስ እንዳስረዱት፤ አካል ጉዳተኞች በተለመደው ዊልቼር ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በእጃቸው እየገፉ ወይም ሌላ ሰው እየገፋላቸው ነው። ስለዚህ የተለመደው ዊልቼር በሰው ኃይል ወይም ግፊት የሚንቀሳቀስ ነው። ነገር ግን፤ ይህ ዊልቼር በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፤ አካል ጉዳተኞች በእጃቸው ሳይገፉ ወይም የሌላን ሰው ርዳታ ሳይሹ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ያስችላቸዋል።
ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ቴክኖሎጂውን በቀላሉ መጠቀም እንዲችል ተደርጎ የተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የፈጠራ ባለሙያው፤ አንድ አካል ጉዳተኛ ከዊልቼሩ ፊት ለፊት የተገጠመውን “ጀስቲክ” በቀላሉ በመነካካት ወደፈለገው አቅጣጫ መጓዝ ይችላል። ጀስቲኩንም በመነካካት ሲፈልግ ወደፊት፤ ወደኋላ፤ ወደ ግራና ወደቀኝ ማዞርና ማቆም ይችላል። በመሆኑም፤ አካል ጉዳተኛው በእጁ ሳይገፋና የሌሎች እርዳታ ሳያስፈልገው በዳገትም ይሁን በቁልቁለት፤ እንዲሁም ኮረኮንች በበዛበት መንገድ ሳይቸገር በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የፈጠራ ስራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ፤ የፈጠራ ስራው አካል ጉዳተኞች ጊዜና ጉልበታቸውን ቆጥበው፤ ያለማንም ሰው እገዛ ራሳቸውን ችለው ከቦታ ቦታ በቀላሉ ተንቀሳቅሰው፤ የፈለጉበት ቦታ በወቅቱ ደርሰው ስራቸውን ማከናወን የሚያስችላቸው ግኝት መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም፤ ይህ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ዊልቼር ከውጪ አገር ከ50 ሺህ ብር በላይ በሚገመት ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ የጠቆሙት መምህሩ፤ የፈጠራ ስራው ከውጪ የሚገባውን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራውን ዊልቼር በአገር ውስጥ በማምረት ለአካል ጉዳተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ከማስቻሉ ባሻገር፤ የውጪ ምንዛሬን በማስቀረት የራሱን ምጣኔ ሀብታዊ አስተዋጽፆ ለአገር እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፤ ይሄንን የኤሌክትሪክ ዊልቼር የሚያመርት ካምፓኒ በአገር ውስጥ በማቋቋም፤ በተለይ በኤሌክትሪካልና መካኒካል የትምህርት ዘርፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።
ቴክኖሎጂውን በብሉቱዝና በሪሞት ማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ሶፍትዌሮችን በመግጠም የፈጠራ ስራውን ለማዘመን እንዳሰቡ የገለጹት አቶ ዘካሪያስ፤ የፈጠራ ስራውን ለመስራት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችንና ሞተሮችን እንደልብ በአገር ውስጥ ገበያ አለማግኝት፤ የበጀትና የጊዜ እጥረት፤ የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ሰዎችን የሚያበረታቱና የሚደግፍ አካላትና ተቋማት አለመኖሩ እንቅፋት እንደሆነባቸውና ከዚህ በተሻለ ቴክኖሎጂውን አዘምኖና አሻሽሎ ለመስራት እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 16 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን የሚናገሩት መምህሩ፤ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የፈጠራ ስራውን ሰርተው አጠናቅቀው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዘጠነኛው አገራዊ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ ተሳትፈዋል። በዚህ ውድድርም በፈጠራ ስራቸው ሶስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስድስት ሺህ ብር ድጋፍና የማበረታቻ የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ የክልሉ መንግስት ለፈጠራ ስራ በሰጠው ትኩረት፣ የሚያስተምሩበትም ኮሌጅ ለፈጠራ ስራው ባደረገላቸው ድጋፍ እና በእርሳቸው ጥረት የፈጠራ ስራቸው እውን መሆኑን የሚናገሩት የፈጠራው ባለቤት፤ የሀረሪ ክልል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲና ኮሌጁ ለሰሩት የፈጠራ ስራ የገንዘብና የማበረታቻ የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ነግረውናል።
አጠቃላይ የፈጠራና የዕውቀት ሽግግርን አስመልክቶም፤ በኮሌጁ ውስጥ አዋጭና ለማህበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በኮሌጁ ባለሙያዎችና አስተዳደር ከተለዩ በኋላ፤ ቴክኖሎጂውን የመቅዳት ተግባር በኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች ይከናወናል። ቴክኖሎጂው ተቀድቶ ወደ አገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ከተለወጠ በኋላም፤ የኮሌጁ ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ክፍል ቴክኖሎጂዎችን ደረጃ በደረጃ እየለየ ቴክኖሎጂውን ቀምሮ ለገበያ በማቅረብ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርግበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል።
በመሆኑም፤ ኮሌጁ በ2012 በጀት ዓመት ሊቀዱ የሚገባቸውና የተቀዱ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት አምርቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ መደረግ የሚገባቸውን ቴክኖሎጂዎችን በባለሙያዎች እየለየ መሆኑን ጠቁመው፤ የቴክኖሎጂ ልየታው ካለቀ በኋላ፤ በጀት ተመድቦ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ተለይተው፤ አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ቴክኖሎጂዎችን አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ይደረጋል። ይህ የፈጠራ ስራም ለአካል ጉዳተኞች ካለው የጎላ ፋይዳ አንጻር በቅድሚያ ተመርቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የፈጠራ ስራውም ለገበያ ሲቀርብ 16 ሺህ ብር ዋጋ የተተመነለት ሲሆን፤ ነገር ግን ይሄንን ገንዘብ ከፍለው ለመግዛት አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች በአካል ጉዳተኞችና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በተመጣጣኝ ዋጋ ለድርጅቶቹ የሚቀርብበትንና ድርጅቶቹም በጅምላ ሲገዙ የዋጋ ቅናሽ የሚደረግበትን መንገድ እንደሚመቻች የፈጠራ ባለቤቱ አስገንዝበዋል።
“መምህር የህብረተሰቡን ቁልፍ ችግሮች በመለየት ለችግሮቹ ዓይነተኛ መፍትሄ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ይጠበቅበታል” የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ ወጣቶች የአገሩንና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ በወጣትነት ዘመናቸው ትኩረት ሰጥተው በመስራት የራሳቸውን አሻራ ጥለው ማለፍ ይገባቸዋል፤” ሲሉ በተለይ በተለያየ የስራ ኃላፊነት ላይ ላሉ ወጣቶች ምክራቸውን ጀባ ብለዋል።
የፈጠራ ባለሙያው ከዚህ በተጨማሪ፤ በገጠር አካባቢ የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ከጉድጓድ ውሃ ማውጣት የሚያስችል፤ በስራ ላይ ያለን ማሺን ወይም ሞተር በሪሞት መቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር እና ገበሬዎች እህል ከወቁ በኋላ በቀላሉ ጊዜና ድካማቸውን ቆጥበው እህሉን ለማፈስና ወደ ጎተራ ለማጓጓዝ የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት፤ በ2011 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት ባዘጋጀው የመላው የቴክኒክና ሙያ መምህራን የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ በመሳተፍም ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011
ሶሎሞን በየነ