የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር በዓመት 10 ሚሊዮን ጭማሪ አሳየ

ሀዋሳ፡– የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማጎልበት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠቃሚዎች ቁጥር 10 ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ አገልግሎቱ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዋነኛ ግብ ለሁሉም ዜጎች ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ ነው። በዚህ እቅድ የሪፎርም አጀንዳዎች አንዱም የጤና ክብካቤ የፋይናንስ ሥርዓትን በማሻሻል የጤና መድህን ሥርዓትን መተግበር ዋነኛው ነው። የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማጎልበት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠቃሚዎች ቁጥር 10 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በጤናው ዘርፍ ላይ ተጨባጭና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በግልፅ ያጎናጸፉ ውጤቶች መገኘታቸውን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለአብነትም ‹‹ህብረተሰቡን ከህክምና ወጪ ስጋት ከማዳንና ከሞት ከመታደግ ባሻገር በጤና ተቋማት የመጠቀም ባህል በማሳደግና የጤና ተቋማትን የፋይናንስ ጉድለቶችን በመሙላት ረገድ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ውጤት ተመዝግቧል›› ብለዋል። ይህም ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ማሳካት ያስችላል ነው ያሉት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከእለት እለት በሁሉም ረገድ እድገት እያስመዘገበ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት አቶ ተስፋዬ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የተጠቃሚዎች ቁጥር በአስር ሚሊዮን ጭማሪ እንዳሳየ ገልጸዋል።

የባለፈው ዓመት የተጠቃሚዎቹ ቁጥር 53 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮ ይህን ቁጥር 63 ሚሊዮን ደርሷል፣ ይህም አሃዝ ከሀገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ያሳያልም›› ብለዋል። በአንዳንድ ክልሎች በተስተዋሉና በሚስተዋሉ ችግሮች መድረስ ያልተቻለባቸው ወረዳዎች ሲጨመሩ ይህ አሃዝ ይበልጥ እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።

ከከፋይ አባላትም ከ 11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡና ከተናጠል ድጎማ ከ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ገቢ መሆኑን ጠቁመው፣ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ 15 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሆኑንም አስታውቀዋል። በአጠቃላይ በሀገሪቱ በሚገኙ 4ሺህ 387 የመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር ውል በማሰር የጤና መድህን አባላትና ተጠቃሚዎች የጤና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተገኙ ውጤቶች ባሻገር ውስንነቶች ስለመኖራቸው የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ ለአብነትም በሁሉም ክልሎች ጠንካራ የክልል አስፈፃሚ አካል አለመደራጀት፣ እንደ ሀገር ተመሳሳይ መዋጮ ተግባራዊ አለመደረግና የፌዴራል ተቋማት መመስረት አለመቻልን በዋነኝነት ጠቅሰዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በተለይም መረጃዎችን በአግባቡ የማደራጀት፣ ጠንካራ ተቋማትን የመፍጠርና የዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን የመተግበርና የማጎልበት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራባቸው አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር .ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው፣ ወቅቱ የጤና መድህን አገልግሎት ትልቅ ትኩረት ያገኘበት ነው፣ በክልሉ ከአምስት ዓመት በፊት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን 18 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ አሀዝ አሁን ላይ 72 በመቶ ደርሷል›› ብለዋል። ይህም የጤናውን ዘርፍ ከውጭ አካላት ድጋፍ ለማላቀቅና በራስ አቅም ለመቆም እንደ ትልቅ ርምጃ ሊወሰድ የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You