ዓባይ ግንድ ተሸክሞ መዞሩ አክትሟል

ዜና ሀተታ

ዳግማዊ ዓድዋ በመባል ለኢትዮጵያ ዳግም ኩራት የሆነው እና የኢትዮጵያን ልጆች ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ አድርጎ ያስተሳሰረው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጎረቤት ሀገራትን እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ተጽዕኖ ተቋቁሞ በምረቃ ዋዜማው ላይ ደርሷል። ከጉሊት ቸርቻሪዋ እስከ ባለሀብቱ፤ ከተማሪው እስከ ፕሮፌሰሩ ግድቡ የእኔ ነው በሚል ስሜት ያለውን አዋጥቷል። ግድቡም ተገንብቷል።

‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ የሁሉም ድጋፍና ትብብር ከግብ ደርሶ ዓባይም ግንድ እና አፈር ማጋዙን ትቶ ከቤቱ ሊያድር፤ የዓባይንም ልጆች ዳግም ውሃ ላይጠማቸው ተከትሯል። ዓባይ የትውልድ ሀገሩን፣ አድባሩን እና ያኮረፈውን ሕዝብ ሊክስ መስከረም ወር ላይ ሪቫን ተቆርጦለት ወደ ሥራ ሊገባ ቀጠሮ ተይዞለታል። በዚህም ሀገሬው ከወዲሁ ደስታውን በመግለጽ ላይ ይገኛል።

ሥራ ፈጣሪው አቶ አክሊሉ መሰለ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ ነዋሪ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በግሉ እና አጠቃላይ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ከ240 ሺህ ብር በላይ ቦንድ ለህዳሴ ግድቡ ገዝቷል። ዛሬ ላይ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ እና የሚመረቅበት ቀን ሲቆረጥ በሕይወት ኖሮ ለመስማት በመብቃቱ መደሰቱን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይገልጻል።

ደቡብ አፍሪካ፤ በአፍሪካ አህጉር ካሉ ሀገራት የተሻለ ሀብት ሊኖራት የቻለው በወርቅና በፕላቲኒየም ሀብቷ ነው የሚለው አቶ አክሊሉ፤ ኢትዮጵያም ካላት የተፈጥሮ ሀብት አንዱ የውሃ ሀብቷ ነው። ህዳሴ ግድቡን አጠናቃ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ብትሸጥ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ስለሚፈጥርላት የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ነው ብዬ አስበዋለሁ ይላል።

የህዳሴ ግድቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስተሳሰረ እና አንድነትን ያጠናከረ ነው። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም አንድ በመሆን ለብሄራዊ ጥቅም ህዳሴ ግድቡ ላይ ተረባርበዋል። የግድቡ ስኬታማ መሆንም ሁሉንም ያስደሰተ ነው ሲል ይናገራል።

“የህዳሴ ግድቡ እንዲገነባ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ  የሚችለውን አዋጥቷል። እኔም እንደአቅሜ በተለያዩ ጊዜያት የቻልኩትን አዋጥቻለሁ።” የሚሉት በማእከላዊ እትዮጵያ ክልል የካንባታ ዞን ነዋሪው አቶ ሻሜቦ ኢሊሎ፤ ህዳሴ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንጻር ዝግይቷል የሚል ሃሳብ ቢኖራቸውም፤ አሁን ግን ለመመረቅ ከጫፍ መድረሱ እጅግ በጣም እንዳስደሰታቸው ይገልጻሉ።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያላት የኤሌክትሪክ ኃይል በቂ አይደለም። እናም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በበቂ ሁኔታ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ፤ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ያለ ኃይል ችግር ለማጠናቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ።

አቶ ሻሜቦ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በቂ ኃይል ከማግኘቷም በላይ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ገቢ እንድታገኝ የማድረግ እድል ስላለው አጠቃላይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ህዳሴ ግድቡን በመገንባት ሂደት የነበሩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ መቻሉ፤ ከስኬት እንዳደረሰው በመግለጽ፤ በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ጫናዎችን ተቋቁሞ በማለፍ የሚክስ መሆኑን እና እንደ ሕዝብ ደግሞ ዋጋ መክፈልን ያስተምራል። አሁንም ጫናዎችን ተቋቁመን ለስኬት  እንደመብቃታችን ሁሉ፤ ለወደፊትም ተቋቁመን ማለፍ ይኖርብናል ይላሉ።

ወደፊት ከአጠቃቀም ጋር ተያይዞ ህዳሴ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደመሆኑ መጀመሪያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ መዳረስ አለበት። ከዚህ ባለፈ የሚተርፈውን ኤሌክትሪክ ኃይል ሽጦ በሚገኘው ገቢ መንገድ፣ ውሃና ሌሎች ግድቦችንም መገንባት ይገባል ሲሉም ያመላክታሉ።

ህዳሴ ግደቡ ለበርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋ እና እንደ ሀገር ደግሞ ኩራት ነው የሚለው በአማራ ክልል የደብረ ሲና ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ ፍቅሩ ዘውዱ ነው።

እሱ እንደሚለው፤ ያለፉት አባቶች ለሀገራቸው በመዋጋት እና ሀገራቸውን ከወራሪ ኃይል በመከላከል የጀግንነት ታሪክ አስቀምጠው አልፈዋል። ልክ እንደዚያው ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ከላይ እስከታች ተሳትፎ ያደረገበት ስለሆነ ግድቡ ትውልድ የሠራው አዲስ ታሪክ ነው ይላል።

“የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሲጀመር እኔ ትምህርቴን ትቼ የግል ሥራ መሥራት የጀመርኩበት ጊዜ ነበር፤ አሁን ላይ በሥራዬ ስኬታማ በመሆን በርካታ ሠራተኞችን ቀጥሬ እያሠራሁ፤ በካፒታልም በማደግ ደረጃዬን ያሻሻሉኩበት ጊዜ ነው። በተመሳሳይ ደግሞ ህዳሴ ግድቡም ተጠናቆ ለምርቃት የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ፤ የሁለቱ መገጣጠም አስደስቶኛል”። ሲል ስሜቱን አያይዞ ይገልጻል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You