ንግድ ቢሮው 99 በመቶ የሚሆነውን አገልግሎቱን በኦንላይን እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፡በ2017 በጀት ዓመት 99 በመቶ የሚሆነውን አገልግሎቱን በኦንላይን መስጠት መቻሉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮው አስታወቀ። በበጀት ዓመቱም 36ሺህ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ ሕገወጥ አካሄዶችን በተጨባጭ መቀነስ መቻሉንም ገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ቢሮው በተለያዩ የትኩረት መስኮች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል። እነዚህም ለንግድ ዘርፍ ማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት፣ አቅርቦትና ፍላጎት እንዲጣጣም ማድረግ እና ሕግን የሚተላለፉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት፤ በ2017 በጀት ዓመት በተለይ በሦስቱም የትኩረት መስኮች ተቋሙ ስኬት አስመዝግቧል። በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ደንበኞች 99 በመቶ የሚሆነውን የቢሮውን አገልግሎት በዲጂታል ፎርማት እየተሰጠ ነው። በዚህም የደንበኛ እርካታን መጨመር መቻሉን በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ማረጋገጥ ተችሏል።

ከዚህ በፊት የዲጂታል አገልግሎት በወረዳ እና በክፍለ ከተማ ላይ ወጥ በሆነ መንገድ ሲሠራበት እንዳልቆየ የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ በአሁኑ ጊዜም 16 አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚሰጡ ናቸው። ይኸውም የንግድ ማኅበረሰቡ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ለመቆጠብ አስችሏል ብለዋል።

አቅርቦት ጋር በተያያዘ መንግሥት በ219 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት እና አምስቱ ገበያ ማኅበራት የሚያቀርባቸው የፍጆታ እቃዎች እና ለምግብነት የሚውሉ አሉ የሚሉት ወይዘሮ ሀቢባ፤ ሌላኛው አቅራቢ ተብሎ የሚቀመጠው የነጋዴው ማኅበረሰብ ነው። በዚህም በመንግሥት የሚቀርበው 23 በመቶ ሲሆን ቀሪው 77 በመቶ በነፃ ገበያው የሚቀርብ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሮ ሀቢባ ገለጻ፤ የ2017 በጀት ዓመት በአቅርቦት ዙሪያ ምንም ዓይነት እጥረት ያልተፈጠረበት ነው። ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የተወሰኑ የዋጋ ጭማሪዎች ቢኖሩም በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ መረጋጋት ታይቷል። ንግድ ቢሮም በመንግሥት የሚቀርቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን የማውጣት ሥራ ይሠራል። በዚህም በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ እና በአምስቱ የንግድ ማዕከላት ላይ ዋጋ ተመን የማውጣት ሥራ በመሠራቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ለማኅበረሰቡ እንዲቀርብ ማድረግ ተችሏል።

በነፃ ገበያው ላይም ምርት እንዳይጠፋ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ ተሠርቷል ያሉት ኃላፊዋ፤ ከዚህም ውስጥ ነጋዴዎች ምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ተመን እንዲለጥፉ በማድረግ ማኅበረሰቡ አማራጩን እንዲወስድ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በአቅርቦቱም ላይ በ2017 የምንም ዓይነት የምርት እጥረት ሳይፈጠር መጠናቀቁ የቢሮው ስኬት መሆኑንም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በሦስተኛው የቢሮው ትኩረት መስክ በሆነው የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ ቢሮው 36ሺህ 800 ነጋዴዎች ላይ የሕግ መተላለፍ በመገኘቱ ርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።

አዲስ አበባ ላይ የንግድ አሻጥር እንደሚበዛ የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ በአዲስ አበባ ውስጥ 500ሺህ ነጋዴ አለ። ከእነዚያም ውስጥ የጸና የንግድ ፈቃድ ኖሯቸው በየዓመቱ የሚያድሱ ነጋዴዎች ቁጥር 481ሺህ ናቸው። 330ሺህ የሚሆኑት ነጋዴዎች ላይ በር በበር ክትትል ተደርጎባቸዋል። 36ሺህ 800 ነጋዴዎች ላይ የሕግ መተላለፍ በመገኘቱ ርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል።

ርምጃ የተወሰደባቸው ነጋዴዎችም አብዛኞቹ የፈጸሙት የሕግ ጥሰት ምርትን ማሸሽ እና መከዘን መሆኑን አንስተው፤ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የዋጋ ንረት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል። ሌሎቹም እንዲሁ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ሚዛን መስረቅ፣ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው መሥራት እና አለማደስ የሚሉትም እንደሚገኙበትም አብራርተዋል።

በዚህም ርምጃ 90 በመቶ የሚሆነውን የምርት ማሸሽ እና ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ መሥራት የሚባለውን የሕግ መተላለፍ መቀነስ መቻሉን ጠቁመው፤ የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ማሻሻያ ሰሞን ቢሮውን በእጅጉ ሲፈትን የነበረውን የምርት ማሸሽ አካሄድ በተጨባጭ በሚታይ መልኩ ለመቀነስ መቻሉን ነው የተናገሩት።

ብዙ ጊዜ ሕገወጥ ነጋዴዎች ምርት የሚያሸሹት በሸገር ከተማ አካባቢ መሆኑን ገልጸው፤ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት በመሥራት በየወሩ የመጋዘን ፍተሻን በማድረግ ሕገ ወጦችን የመከላከል ሥራ መሠራቱንም የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ አመልክተዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You