የእናቶች ሞት ከአንድ ሺህ ወደ 195 ዝቅ ማድረግ ተችሏል

አዲስ አበባ፡ከመቶ ሺህ እናቶች በአማካይ ለአንድ ሺህ እናቶች ሞት ምክንያት የነበረው ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ የሞት ምጣኔ ወደ 195 ዝቅ ማድረግ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በጤና ሚኒስቴር የሥነ ተዋልዶ ጤና ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሰለሞን ወርቁ እንደተናገሩት፤ ባለፉት 20 ዓመታት በተሠሩ የተቀናጁ ሥራዎች ከመቶ ሺህ እናቶች በአማካይ ለአንድ ሺህ እናቶች ሞት ምክንያት የነበረው ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ የሞት ምጣኔ ወደ 195 ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ጽንስ ማቋረጥ ሲባል ቀድሞ ደኅንነቱ የተጠበቀ የጽንስ ማቋረጫ መንገድ ማሰብ ተገቢ ነው ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ በተለይ ለወጣቶች በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰጠው ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የቤተሰብ አገልግሎት መረጃን በቂ ማድረግ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በሕጋዊ መንገድ ጽንስ ማቋረጥ ባለመፈቀዱ በርካታ እናቶችና ልጃገረዶችን ለሞት መዳረጉን አብራርተዋል።

አይ ፓስ ኢትዮጵያ (IPAS Ethiopia) የቤተሰብ ጤና አገልግሎት ላይ እንዲሁም ደኅንነቱ የተጠበቀ የጽንስ ማስወረድ አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በሕጋዊ መንገድ ጽንስ ማቋረጥ አለመደገፍ ጽንስ ማቋረጥን አይከላከልም፤ይባስ ብሎም ደኅንነቱ ያልተረጋገጠ ውርጃን እንደሚያባብስ ገልጸው፤ ውርጃን በጥንቃቄ መመልከት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ዶክተር ሰለሞን፤ የተስተካከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ተግባራዊ ባለመደረጉ በኢትዮጵያ እናቶች እና ልጃገረዶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደነበርም ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የእናቶች ሞት ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዝ እንደነበር አስታውሰዋል።

አይ ፓስ ኢትዮጵያ (IPAS Ethiopia) ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ ደስታ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች አጠቃላይ ከእናቶች ሞት 32 በመቶ ይይዝ የነበረው ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ ወደ አራት በመቶ በታች እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዓለምም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእናቶች ሞት ከፍተኛ ነበር ያሉት ዶክተር ደመቀ፤ ይሁን እንጂ አሁን ላይ በተደረጉ የተለያዩ ድጋፎችና ሥራዎች ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ደመቀ ገለጻ፤ ከድጋፉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ እንዲተገበር ለማስቻል የወጣው የሕግ ማዕቀፍ አተገባበሩ ውጤታማ ስለነበር ከሀገሪቱ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ማሳያ መሆን ችሏል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥም በሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶች በመሞታቸው ምክንያት በርካታ ሕጻናት ወላጅ አልባ እያደረገ እንደነበር ገልጸው፤ ከዚህ በተጨማሪም ልጃገረዶች ያሰቡበት ግብ እንዳይደርሱ እየገታቸው እንደነበር አውስተዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተሠሩ ሥራዎች የመጣው አመርቂ ውጤት መንግሥትና የተለያዩ አጋር ተቋማት በተቀናጀ መልኩ በጋራ በመሥራታቸው መሆኑን ተጠቁሟል።

አይ ፓስ ኢትዮጵያ (IPAS Ethiopia) ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ ተግባራዊ መሆን የጀመረበትን 20ኛ ዓመት ማክበሩ ታውቋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You