
አዲስ አበባ፡– ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት ከ253ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመላው ሀገሪቷ ለዚህ ተግባር ተብሎ ሊታረስ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
በአደጋ ስጋት ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቅ መረጃ እና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፍራኦል በቀለ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን ለሁሉም ክልሎች ለመጠባበቂያ ክምችት እና ለአስቸኳይ ጊዜ ዕለት ደራሽ ርዳታ የሚያስፈልገው የምግብ መጠን 2 ሚሊዮን 025ሺህ 498 ቶን ነው። ይህን የምግብ መጠን ለማቅረብም 253ሺህ 188 ሄክታር መሬት ሊታረስ ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት ለሁሉም ክልሎች ለመጠባበቂያ ክምችት የሚያስፈልገው 500ሺ ቶን እህል ነው። ለአስቸኳይ ጊዜ ዕለት ደራሽ ርዳታ የሚያስፈልገው ደግሞ አንድ ሚሊዮን 525ሺህ 498 ቶን እህል ነው። በድምሩም ለመጠባበቂያ ክምችት እና ለአስቸኳይ ጊዜ ዕለት ደራሽ ርዳታ የሚያስፈልገው የምግብ መጠን ሁለት ሚሊዮን 025ሺህ 498 ቶን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች መሬት አዘጋጅተው እህል ማምረት እንዲጀምሩ መደረጉን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በየክልሎቹ እየዞሩ መመልከታቸውንም አስታውቀዋል። ክልሎቹም በዘንድሮ የክረምት ወራት የእርሻ ሥራውን እያከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎችም ለሚያመርቱት ምርት የእህል ማከማቻ ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህም የመጋዘን ግንባታ ደረጃ (ስታንዳርድ) ወጥቶ ለእያንዳንዱ ወረዳ ተሰጥቶ የማስጀመር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የርዳታ ሰጭዎች ድጋፍ መቼ እንደሚቋረጥ አይታወቅም፤ በዚህም መንግሥት ኅብረተሰቡን እና ተቋማትን ማስተባበር እንዲችል አዋጅ የማፀደቅ ሥራ ተሠርቷል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ይኸውም አጀንዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት በርካታ መድረኮች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ የ2017 በጀት ዓመት ረጂ ድርጅቶች ሲሰጡ የነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመተካት ብርቱ ርምጃ የተካሄደበት ዓመት ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እስካሁን 110 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን እና ከዚህም ከ600 እስከ 700 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መናገራቸው የሚታወስ ነው።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም