
አዲሰ አበባ፡– በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራ እና የሰው ሠራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አበሩ ጠና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በዘንድሮም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ። ለዚህም በቂ የቦታ እና ሌሎች ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ማኅበረሰቡ በተለይም አርሶ አደሩ ፈጣን እድገት ያላቸው የውጭ ሀገር የዛፍ ዝርያዎች መትከል ላይ ትኩረት ያደርግ እንደነበር አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜ የሀገር በቀል ችግኞችን በብዛት የመትከል አፈፃፀም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
እነዚህ ሀገር በቀል የችግኝ ዝርያዎች የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል እና በማስተካከል ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ የአርሶ አደሩ ምርታማነትም እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል።
በአረጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለደን እና የተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማኅበረሰቡ ችግኞችን የመትከል ባህልና የባለቤትነት ስሜት እያደገ በመምጣቱ አፈፃፀሙ እየተሻሻለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ተራሮችን፣ የተራቆቱ መሬቶችን እና ሌሎችን በሀገር በቀል ዛፎች መሸፈን የውሃ ሀብታችንን ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው ያሉት አቶ አበሩ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ወደ 40 ቢሊዮን የተለያዩ ጥቅም ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የተጎሳቆሉ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ አዋጅ የአየር ንብረትን ለውጥን ከመከላከል እና የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከማድረግ እንዲሁም የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር የማይተካ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች በመፈጠሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ደን አደር ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው። ምንም እንኳን የደን ልማት የአጠቃላይ ኢኮኖሚ ድርሻ አራት በመቶ ነው ቢባልም ተቋሙ 14 በመቶ የአጠቃላይ ኢኮኖሚ ድርሻ አለው ብሎ እንደሚያምን ነው ያስረዱት።
በአጠቃላይ መርሐ ግብሩ እስካሁን በተከናወነው ሥራ የተራቆቱ መሬቶችን ከማገገም፣ የደን ሽፋን ከመጨመር፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር እንዲሁም በተፈጥሮ ደን ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
በርካታ አጋር አካላት ከኢትዮጵያ ጋር በደን ልማት እና አረንጓዴ ዐሻራ ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ፀጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም