የመጪው ትውልድ ሕልውና – ባሕር በር

አፍሪካ ካሏት 54 ሀገራት 38ቱ የባሕር በር ሲኖራቸው ሀገራችንን ጨምሮ 16 ሀገራት ለደኅንነት፣ ለሕልውናና ለምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ የሆነው የባሕር በር የላቸውም። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያላት የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ብቻ ናት።

የባሕር በር የሌላት ሀገራችን የባሕር በር እንድታጣ የተደረገው በተለያዩ አካላት ሴራ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ የሚያስቆጭ ነው። ይህን የተገነዘበው መንግሥትና ሕዝብም በዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የጀመሩት እንቅስቃሴ አጠናክረው የሚቀጥሉት ይሆናል።

ከመንግሥት ጋር ተቃርነው በተቃውሞ ጎራ ያሉ ፖለቲከኞችም ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ሂደቱን ሊደግፉ ይገባል። በተለይ አሁን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እያደረገችው ካለው እንቅስቃሴ አንጻር የባሕር በር ወሳኝና የሕልውና ጉዳይ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ የዘርፉ ምሑራን ይገልጻሉ።

የሥራ አመራር ባለሙያ አቶ ተሾመ ዘውዴ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር በአንድ ወቅት በነበረ የአመራር ታሪካዊ ስህተት ምክንያት አጥታለች። ይህንን ስህተት ለማረም የአሁኑ ትውልድ እየሠራ ነው። ይህም ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የባሕር በር ጉዳይ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥያቄ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ተሾመ፤ የዓባይ ግድብን በሰላማዊ መንገድ ጫፍ ላይ ማድረስ እንደተቻለው ሁሉ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

መንግሥት ባከናወነው የዲፕሎማሲ ሥራ ከሶማሌላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙን አስታውሰው፤ አሁንም በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከአጋር ሀገራት ጋር ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አሠራርን ተከትላ የባሕር በር ለማግኘት መሥራት አለባት። ይህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ ምላሽ ማግኘት እንደሚችል ገልጸው፤ ሕጉም ባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው እንደሚደነግግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ይህንን የቀጣናው ሀገራትና ሊረዱና ለጉዳዩ ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል። ይህንንም መንግሥት በተለያዩ አማራጮች በንግግር ለዓለም መግለጥ አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ተከትሎ ከግብፅ በኩል የሚነዛው መሠረተ ቢስ መረጃ ለግብፅ ባልተሰጠ መብት ላይ የተንጸባረቀና ተገቢነት የሌለው ፕሮፖጋንዳ መሆኑን አንስተው፤ በርካታ ኃያላን ሀገራት ከረጅም ርቀት ባሕር ተሻግረው ለጥቅማቸው በሚሻኮቱበት የቀይ ባሕር ቀጣና በቅርብ ርቀት የምትገኘው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስጠብቅ ሁሉም በባለቤትነት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአካባቢና የልማት ባለሙያ አቶ ያለምሰው አደላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልገኛል ብላ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረበችው ጥያቄ ከአስፈላጊነቱ አንፃር ጥያቄው የዘገየ እንጂ የፈጠነ ነው የሚባል አይደለም። የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ ታሪካዊ ጠላቶች ታትረው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የማይፈልጉበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆን ነው። ይህንን መንግሥት በዲፕሎማሲው መመከት አለበት። ሌላው ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን የጉዳዩን ጠቀሜታ መረዳትና ማወቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ በመሆኗ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተጋልጣለች። ለምሳሌ፣ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል። ለኪራይና ለመጓጓዣም ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ያለምሰው ገለፃ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ንግድ የሚሰጥ ዋጋ ለማስጠበቅ የባሕር በር አንደኛ አስፈላጊ ነው። ይህ እንደ ወቅታዊ ነገር ለኢትዮጵያ የገበያ ተደራሽነት ይረዳል። የባሕር መዳረሻ አንዱ የኢኮኖሚ እድገት ምንጭ ነው። የባሕር በርን መቆጣጠር የባሕር ኃይል ደግሞ ደኅንነት ለመጠበቅና ስጋትን ለማስወገድ ስለሚያስችል የባሕር በር ለኢትዮጵያ የእስትንፋስ ያህል ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የፖለቲካ፣ የደኅንነትና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ያላት ሀገር ያደርጋታል ብለዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ፤ የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መልማት መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰላም መሆንና መልማት ለቀጣናው ዕድገት በጎ ሚና እንደሚጫወትም ጨምረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላም እና ልማት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ ጎረቤቶቿ ሊረዱ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሠራች እንደምትገኝም ተናግረዋል። የባሕር በር ጉዳይ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

የባሕር በር አለመኖር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት እና ይህም በንግድ ሕጎች አማካኝነት ምላሽ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በቀናነት እንዲረዱትና ጥያቄው ከመልማት እና ከማደግ ካለ ጽኑ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባቸው አንስተዋል።

በቀይ ባሕር ቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆን እንዳትችል የሚያደርጉ ሴራዎችን ሰብሮ መውጣት እና በሰላማዊ ጥረት የባሕር በር ባለቤትነትን ማሳካት እንደሚገባ ምሑራን ይገልጻሉ።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You