‹ኪን ኢትዮጵያ› የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ቱሪዝም እንዲስፋፋ ያግዛል

– የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ቡድን ወደ ቻይና ሊያቀና ነው

አዲስ አበባ፡- ‹ኪን ኢትዮጵያ› የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ፣ ባህልና እሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ተገለጸ።

በመጪው እሁድ ወደ ቻይና በሚደረግ ጉዞ የሚጀመረውን ‘ኪን ኢትዮጵያ’ የባህልና የጥበብ ጉዞ አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ትናንት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት፤ ኪነ-ጥበብ የሕዝብ ለሕዝብ እና የሀገራትን ግንኙነት በማጠናከር በኩል ጉልህ ሚና አለው። መንግሥትም የዘርፉን እምቅ አቅም ለሀገር ጥቅም ለማዋል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የ‹ኪን ኢትዮጵያ› ቡድን ጉዞም የኢትዮጵያን እምቅ ሀብት ለዓለም በማስተዋወቅ ከሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በግለሰቦች ደረጃ የተለያዩ መሰል ጥረቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የአሁኑ ጉዞ ግን በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ ኦፊሴላዊ ጉዞ መሆኑን ተናግረዋል። ሉኡካን ቡድኑንም የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ እንደሚመሩት ጠቁመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው፤ ጉዞው የኢትዮጵያን ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ይሆናል ብለዋል።

በጉዞው ከ70 በላይ የልኡካን ቡድን አባላት እንዳሉት ጠቅሰው፤ በዝግጅቱ ላይም ከ50 በላይ የብሔርና ብሔረሰቦች የባህል ሙዚቃና ጥበባት መካተታቸውን ጠቅሰዋል።

ልኡካን ቡድኑ ጉዞውን በቻይና ሁለት ከተሞች በሚኖረው ዝግጅት ይጀምራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቀጣይነትም ወደተለያዩ ሀገራት ጉዞ ያደርጋል ብለዋል።

ከ39 ዓመታት በፊት ‹ሕዝብ ለሕዝብ› በሚል የጥበብ ሰዎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ተጉዘው ኢትዮጵያ ትታወቅበት የነበረውን መጥፎ ስዕል ለመለወጥ ጉልህ ሚና ተጫውተው እንደነበር አስታውሰው፤ የኪን ኢትዮጵያ ይህን ጉዞ ዳግም በማስጀመሩ ታሪካዊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ባህል፣ ጥበብና እሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን የሚያዩበትን መልክ በመለወጥ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

በመግለጫው ላይ የተገኘው አርቲስት ካሙዙ ካሣ፤ ቡድኑ ላለፉት አራት ወራት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል።

በመርሃግብሩ ላይም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃዎች፣ አመጋገብና አልባሳትን እንዲሁም ቡናን ጨምሮ የኢትዮጵያን እምቅ ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል።

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ዝግጅቱን እውን በማድረጉ እና በሂደቱ እገዛ ላደረጉ ተቋማት በልኡካን ቡድኑ ስም ምስጋና አቅርቧል።

ሻኩራ ፕሮዳክሽን ተባባሪ አዘጋጅ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ጉዞው “ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የማንሠራራት ብስራት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከናወን ታውቋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You