
አዲስ አበባ፡- የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በሀገራዊ ጉዳዮች በመደገፍም፣ በመንቀፍና አማራጭ መንገድ በማሳየትም ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር 22ኛውን ሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ኮንፍረንስ ባካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የኢትዮጵያን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሊያስተካክሉ የሚችሉ ርምጃዎች እየወሰደና አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመደገፍም፣ በመንቀፍና አማራጭ መንገድ በማሳየትም ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
በሀገሪቱ ከፍተኛ የመልማትና የመበልጸግ ፍላጎትም መኖሩን ጠቁመው፤ ለዚህም ሀገራዊ ራዕይን የሚደግፉ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ በተለይም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎችን በመደገፍም፣ በመንቀፍም ይሁን አማራጭ መንገድ በማሳየት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ማሻሻያው ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል። በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መምጣት ኢትዮጵያን ከአፍሪካም የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በተጨማሪ ባለፉት ጊዜያት የዋጋ ግሽበትን ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መቀነስ መቻሉን አመልክተው፤ በቀጣይም ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነና ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርት በማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ማህበሩ በየሶስት ወሩ ማክሮ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ውይይት ያደርጋል። ከዚህ ቀደምም ያለፈውን ሰባት ዓመታት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሪፖርት አቅርበናል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ካደረገ በኋላ በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፖርት አቅርበናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ ቀንሶ የገቢ ንግድ ጨምሮ ነበር። በሁለተኛው ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ ጨምሮ የገቢ ንግድ ቀንሷል። ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያው በረዥም ጊዜ የሚጠበቀውን ለውጥ ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
ዘንድሮ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በመንግሥት በኩል በስምንት ነጥብ አራት በመቶ በዓለም ባንክ በኩል ሰባት ነጥብ አራት በመቶ ማደጉ ተገልጿል። ውጤቱ የትኛውም ቢሆን አበረታች ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው። እንደ ሀገር የብድር መጠንም መቀነስም አንዱ የኢኮኖሚው ማሻሻያ ለውጥ ማስመዝገቡን ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት 26 በመቶ የነበረው ግሽበትም ዘንድሮ ወደ 15 በመቶ ዝቅ ብሏል። በቀጣይም ወደ ነጠላ አሀዝ ይወርዳል ብለን እንጠብቃለን። አንድ ኢኮኖሚ ጥሩ የሚባለው ግሸበት ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ሲሆን ነው። ከዚህ በታችም ከወረደ አምራቾችን ስለማያነቃቃ የሚመከር አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም