ኮሚሽኑ በክረምቱ የጎርፍ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ብሎ የለያቸውን አካባቢዎች ገለጸ

አዲስ አበባ፡በኢትዮጵያ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ የተለዩትን አካባቢዎች የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከአዲስ ዘመን የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በአደጋ ስጋት ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቅ መረጃ እና ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፊራኦል በቀለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አሁን የምንገኝበት ወቅት ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ አካባቢዎች ለእርሻ ሥራ ዝናብ የሚያገኙ ቢሆንም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የክረምቱ ወራት ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የሌሎችንም ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ሊያደርስ ይችላል፡፡ ኮሚሽኑም አደጋ ከመድረሱ በፊት ቦታዎችን የመለየትና አደጋ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አዋሽ ወንዝን ተከትሎ የሚኖሩ ከመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ከኦሮሚያ ክልል ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ጀምሮ እስከ ታችኛው አዋሽ አካባቢዎች በተለይም በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ዳር የሚገኙ ወረዳዎች፣  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰች ወረዳ ሆሞራቴ ከተማን ጨምሮ፣ በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ እና ሌሎች በባሮ ወንዝ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉት ወረዳዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ ተለይተዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በዋቤ ሸበሌ ወንዝ ሊጠቁ የሚችሉ የሶማሌ ክልል ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በጣና ሀይቅ አቅራቢያ የሚገኙ አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በእዚህ የክረምት ወቅት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እና ተጎጂ ይሆናሉ ተብሎ መለየቱን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከተሞች በመሉ ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት በየትኛውም ጊዜ በቅፅበታዊ ጎርፍ አደጋ ሊጠቁ እንደሚችሉ አመልክተው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ባልታሰቡ ክስተቶች እና ትናንሽ ወንዞች ምክንያት የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

አደጋውን በወቅቱ በመገንዘብ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላትና ማህበረሰቡ ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ርምጃ እንዲወስዱ የመረጃ ማጋራት ሥራ መሠራቱን ገልጸው፤ በኮሚሽኑም የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው ቦታዎችም ተለይተው ቅድመ የመከላከል ሥራ መሠራቱንም አስገንዝበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ አደጋ የሚደርስ ከሆነ ለ2 ሚሊዮን ዜጎች ለአንድ ወር የሚበቃ 300 ሺህ ኩንታል ምግብ እንዳዘጋጀም ተናግረዋል፡፡ ለሁሉም ስጋት ላለባቸው ክልሎች የምግብ ስርጭት መደረጉን እና ጀልባዎች መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎችና ከተሞች መሉ በሙሉ ከባድ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት በየትኛውም ጊዜ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ ከእዚህ አኳያም ማህበረሰቡ፣ የሚመለከታቸው ተቋማትና የአስተዳደር መዋቅሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና በክትትል ላይ የተመሠረተ ርምጃዎች እንዲወስዱ የኮሚሽኑ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፊራኦል በቀለ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You