
አዲስ አበባ፡– ለተከታታይ ዓመታት የተካሄዱት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንጀራ እየበሉበት መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ላለፉት 6 ተከታታይ ዓመታት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች እንጀራ እየበሉበት ነው። ከችግኝ ጣቢያ ጀምሮ ችግኞች ጥቅም እስኪሰጡ ድረስ ባለው ሂደት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች አረንጓዴ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ሥራ ፈጠራን በተግባር እየሠራች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለዜጎች ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገር በቀል እሳቤ ከመሆን ባለፈ ባለቤቱና ተጠቃሚው ሕዝቡ መሆኑን ጠቁመው፤ በእዚህም በመርሃ ግብሩ በመታገዝ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ነው ያሉት።
ዛሬ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዓለም አንዴ በጎርፍ፤ ሌላ ጊዜ በድርቅ ፣ ሲፈልግ በኃይለኛ ወበቅና አውሎ ንፋስ እየተጨነቀ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራን መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ ነቅታና ፈጥና ምላሽ እየሰጠች ያለች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ በምግብ ራስን ለመቻል፣ የውሃ ሀብትንና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነት እንደሚያስገኝና፣ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት የግሪን ሀውስ ጋዝን ለመቀነስ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
ሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተሞችን ከማስዋብ ባለፈ በዙሪያቸው የሚገኙና የተበከሉ ወንዞችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው የተናገሩት።
እንደ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገለጻ፤ሁላችንም ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ይኖርብናል። አረንጓዴ ዐሻራን ነገን ዛሬ ላይ ሆነን ለምለምና አረንጓዴ ማድረግ የምንችልበትን ዕድል በእጃችን እንዳለ እንመለከትበታለን። እያደር ውጤቱ የሚታይ ስለሆነ ችግኝ በመትከል ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል።
“እኔ በግሌ ጓጉቼ ከምጠበቃቸው ወቅቶች አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ ነው ”ያሉት ሚኒስትሯ፤በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች ችግኞች ሲተከሉ በተጠና መልኩ ነው። በአንድ በኩል ምግብ እንዲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ደን ሽፋንን ለማሳደግ ነው። በእዚህም እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ አፕል ያሉ በርካታ የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው እየተተከሉ የሚገኙት። እነዚህ ችግኞች አድገው ጥቅም መስጠት ሲጀምሩ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ጉዳዮቻችንም ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በተያያዘም የከርሰ ምድር የሚጠብቁና የገጸ ምድር የውሃ ሀብታችን እንዲጨምር የሚያደርጉ መሆናቸውን አመልክተው፤ በኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ባሕል ወደ መሆን የተሸጋገረ ነው፤ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ቦታ፣ ሁኔታ፣ ጾታና ዕድሜ ሳይገድበው በመልካም ፈቃዱ እየሠራ ያለው ሥራ ነው። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በሂደቱ የሚገኙ ጥቅሞችን አሟጦ መጠቀም ከተቻለ ነገ የምንመኛትን ኢትዮጵያ ዛሬ መሥራት እንችላለን ነው ያሉት።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራም ህብረተሰቡ ብዙ ውትወታና ቅስቀሳ ሳይፈልግ ከግቢው ጀምሮ በአካባቢው ላይ ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ይኖርብናል ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤በተለይ ወጣቶችና ሴቶች በሂደቱ ብዙ የሥራ ዕድል ስለሚፈጠር በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ዘንድሮ ለ7ተኛ ዙር በመላ ሀገሪቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።
በጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም