
– 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ በመጪው ጳጉሜን በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፡- 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ የተሳካና የአፍሪካን መጻኢ ዕድሎች የሚያመላክት እንዲሆን ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተመልክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደውን 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን ስኬታማ ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ ትናንት ከዓለም አቀፍ ፋውንዴሽኖች፣ ለጋሽ ተቋማትና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን በመድረኩ እንደገለጹት፤ 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ የተሳካና የአፍሪካን መጻኢ ዕድሎችን የሚያመላክት እንዲሆን የዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን፣ ለጋሽ ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
ኢትዮጵያ የዓለም ስጋት ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምላሽ ለመስጠት፣ የአረንጓዴ ዐሻራና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮችን ጨምሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚከሰት የአየር ብክለትን ለመከላከል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር እንዲገቡ በፖሊሲ ጭምር የተደገፈ ሥራን እየሠራች መሆኗን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሚካሔደው ጉባኤ ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ ደረጃ የሚሠሩ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ሥራዎች ለዓለም የሚተዋወቅበት ይሆናልም ብለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚከሰቱ አደጋዎች መፍትሔ ለመስጠት በምታከናውነው ተግባራትም በዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት በተለይም በፋይናንስ ልትደገፍ እንደሚገባ አቶ ስዩም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የምታዘጋጀው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴን ማዕከል ያደረጉ ርምጃዎች” በሚል መሪ ሃሳብ ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ ሀብት ማሰባሰብና የተለያዩ ግብአቶች የሚሰበሰቡበትን መደላድል መፍጠር የመድረኩ ዋና ዓላማ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በፖሊሲ የታገዙ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷን ገልጸው፤ ይህንን ተሞክሮዋን በጉባኤው እንደምታጋራ አመላክተዋል።
ለአፍሪካውያን ሕልውና አስጊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመምከር ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ የጉባኤው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ዝቅተኛ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቅት ቢኖራትም ከተጽዕኖው ማምለጥ ባለመቻሏ አማራጭ መፍትሔ ላይ ለመምከር ያግዛል ብለዋል።
ድርቅ፣ጎርፍ፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የሰደድ እሳት እና ሌሎች ችግሮች በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት አህጉሪቱን ሰለባ እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመው፤ አደጋውን ለመቀልበስና ተጽእኖን ለመቋቋም በአፍሪካ ደረጃ የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጉባኤው በሀገራት መሪዎች ደረጃ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ 25 ሺህ የሚደርሱ እንግዶች በእዚህ ጉባኤ እንደሚታደሙ ገልጸዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም