ዘመኑን የዋጀ ቱሪዝም – ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ››

ዜና ሐተታ

በእንግሊዝኛ ፊደላት ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› ብለው ሲገቡ ‹‹ምድረ ቀደምት›› የሚለው የኢትዮጵያ መለያ ይመጣል። የዓለም ሰንደቅ ዓላማዎች ከድረ ገጹ አናት ላይ ይታያሉ። ድረ ገጹ በተንቀሳቃሽ ምስል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የቅርስ መዝገብ (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸውን ታሪካዊ ቅርሶች እና የኢትዮጵያን ውብ ተፈጥሮዎች ያሳያል። ከሥር በትልቅ የአማርኛ ፊደላት ተገጣጥመው የእንግሊዝኛ ቃል የሚመስሉበት ‹‹ኢትዮጵያ›› ተጽፏል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹እንኳን ወደ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ መጣችሁ›› ካለ በኋላ በትልቅ ሰሌዳ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹ኢትዮጵያ ለምን የብዙ ነገር ቀደምት ሆነች?›› ይላል። ከሥሩ መግለጫዎች ተሰጥተዋል።

ይህ የበይነ መረብ መዝገብ ከትናንት በስቲያ በቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በይፋ የተመረቀ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ የዲጂታል ሥርዓት ነው። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች እና ውብ ተፈጥሮዎችን ከሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በቀኝ በኩል ካለው አናቱ ላይ ሦስት አግዳሚ መስመሮች ይታያሉ። እርሱን በመጫን የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአቅጣጫ፣ በልዩ ቦታ፣ በአይነት እና በስማቸው ይጠቁማል። አጠቃላይ የቱሪዝም መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ መረጃ ይሰጣል። ይህ ‹‹ቪዚት ኢትዮጵያ›› የበይነ መረብ ሥርዓት ነው።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽንና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የዲጂታል አማራጭ ከዚህ በፊትም የነበረ ቢሆንም በተበታተነ መንገድ ነው። ይሄኛው ግን የተደራጀ መረጃ ብቻ ሳይሆን ለጉብኚዎች መልስም የሚሰጥ አሠራር ያለው ነው። አስጎብኚ ድርጅቶች የራሳቸው ድረ ገጾች የነበራቸው ቢሆንም፤ ይሄኛውን ለየት የሚያደርገው ሁሉንም በአንድ ቋት የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

አስጎብኚዎቹ የራሳቸው መለያ እና የምሥጢር ቁጥር ስለሚኖራቸው በዋናው ድረ ገጽ ገብተው በአሠራሩ መሠረት በዲጂታል ሥርዓት ሥራቸውን ይሠራሉ። ይህ አሠራር የቱሪዝም መረጃዎችም የተደራጁ እንዲሆኑ ያደርጋል። ለጎብኚዎችም በመንግሥት የሚደገፍ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዲጂታል ሥርዓቱ የጎብኚዎችን ፍላጎት ለማሟላት የተሠራ ባለ ብዙ አማራጭ ዘመናዊ አሠራር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግሥት ሀሚድ በማስጀመሪያ መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ስለሆነ ዘመናዊ አሠራሮችን መከተል ይገባል። ይህን በመገንዘብም መንግሥት የተለያያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ነው። የቱሪስት መዳረሻዎችን መለየትና ማሳወቅ፣ የቱሪዝም አገልግሎቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታል ሥርዓት መዘርጋት አስፈልጎታል። ይህን በመረዳትም የኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር የዲጂታል ሥርዓቱን ለመሥራት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፈው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ታውቋል።

በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ሲፈልጉ የሚጠቀሙት እና ሳይፈልጉ የሚተውት አማራጭ ብቻ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ጉብኚዎች ባሉበት ሆነው የተሟላ መረጃ ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የዲጂታል ግብይቱ በመረጃ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ክፍያዎች በዲጂታል እንዲሆኑ፣ ጉብኚዎችም የሚጎበኙትን እያዩት እንዲሆን ያደርጋል። የቱሪዝም ዘርፉንም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርገዋል። በዲጂታል ሥርዓት መሆኑ የኢትዮጵያ ቅርሶች፣ ባህሎችና ውብ ተፈጥሮዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል።

‹‹ተቋማችን የሀገራችንን ቁልፍ መሠረተ ልማት ከማስጠበቅ ተልዕኮው በተጨማሪ አቅም ባልተፈጠረባቸው ዘርፎች ላይም ይሠራል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የዲጂታል ሥርዓት መተግበሪያዎችን በማልማት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ይሠራል ብለዋል። የቪዚት ኢትዮጵያ የዲጂታል ሥርዓት ተጠቃሚውን ማዕከል ያደረገ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፤ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላትንም በአንድ ሥፍራ የሚያገናኝ ነው። ኢትዮጵያ የጀመረችውን ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ጉዞ ለማሳለጥ ማሳያ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በመክፈቻ መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ እንዲትጠቀም ሲሠራ ቆይቷል፤ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት የግድ ይላል። የቱሪዝም ልማት ከዘመን ጋር አብሮ መሄድ ካልቻለ እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ማግኘት አይቻልም ነው ያሉት።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እና የቱሪዝም አገልግሎቶችን ለመሸጥና የተሳለጠ ግብይት ለማካሄድ የዲጂታል ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የዲጂታል ሥርዓቱ ጎብኚዎች ባስተዋሉት ነገር ላይ ግብረ መልስ እንዲሰጡና በጎብኚዎች ዓይን ጥንካሬን ለማወቅ ያግዛል፤ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የዲጂታል ሥርዓቱ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፤ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በተመለከተ ለጎብኚዎች ወቅታዊ እና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ለመስጠት ነው። በሌላ በኩል በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተዋንያንን በአንድ የዲጂታል ሥፍራ ውስጥ ማሰባሰብ ነው። በቅድመ ጉብኝት፣ በጉብኝት ወቅት እና ከጉብኝት በኋላ ያሉ መረጃዎች በተደራጀ መንገድ እንዲሰደሩ ያደርጋል ብለዋል።

በዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You