የሸማቾች ማህበራት ጥራት ያለው ምርት በተሻለ ዋጋ እያቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ 154 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው ምርት በተሻለ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ገለፀ።

ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ልእልቲ ግደይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ኑሮ ውድነትን ለማስተካከል መንግሥት የሚደጉማቸው 154 የህብረት ሥራ ማህበራት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የማህበረሰብ ክፍሎች ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ነው፤ ይህም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን በመግዛት ተጠቃሚ እንደሆን እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከምርት አቅርቦትና ጥራት አንፃር ተገልጋዩ በተግባር አይቶ እና ቀምሶ የሚመሰክረው ሥራ መሠራቱን በመጥቀስ፤ ጤፍ ነጋዴ ከሚሸጠው ዋጋ የ2 ሺህ ሁለት መቶ ብር ቅናሽ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ዘይት፣ እንቁላል፣ ጥራጥሬ እና የፋብሪካ ምርቶች ጥራታቸው ተጠብቆ ዋጋቸውም ከሌላው በተሻለ መልኩ በማዘጋጀት እንዲሁም በፊት ይታይ የነበረው የተጎሳቆለ የማህበራቱ ሱቅ በአዲስ መልክ በማዘመን፤ ከተማዋን እና ማበረሰቡን በሚመጥን መልኩ መሠራቱን አመልክተዋል።

ስኳር ከዚህ ቀደም በህብረት ሥራ ማህበራት ሲሰራጭ እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ላይ ማኪባ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ሲስተም በመጠቀም ፤ ለተፈቀደለት ሰው ቤት ድረስ በመሄድ ወደ ማህበረሰቡ የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ ይህም በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ህብረት ሥራ ማህበራት ሰፊውን የከተማዋ ማህበረሰብ የሚያገለግሉ እና ከፍተኛ ሀብት የሚያስተዳድሩ ናቸው ያሉት ኮምሽነሯ፤ በተለይ በዝቅተኛው የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ቅርብ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በማህበራቱ የነበረውን ቅሬታ ሊጠግን በሚችል መልኩ በአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ የሚታይ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ተደራሽ እየሆኑ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በተለይ ለሌብነት እና ለብልሹ አሠራሮች ተጋላጭ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉ ሲሆን፤ ማህበራቱ በጠንካራ አመራሮች እና ወጣቶች እንዲሁም ሴቶች እና የተማሩ ሰዎች እየተመሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ማህበራቱ በሠሩት ውጤታማ ሥራዎች ምክንያት የሸማቾች ቁጥር መጨመሩን በመጥቀስ፤ የተሻለ ገቢ ያለው እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ እየሆነ ነው፤ የተጠቃሚው መጨመር የማህበራቱን ካፒታል እንደሚያሳድገው እና፤ ይህም በቀጣይ ለህብረተሰቡ ከዚህ የበለጠ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በ2016 ዓ.ም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ እና ምሬት ይቀርብባቸው የነበሩ 16 ተቋማት ወደ ሪፎርም ሥራ ገብተዋል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ከእነዚህ መካከል የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የፋና ቦሌ ህብረት ሥራ ማህበር ቦርድ ሰበሳቢ አቶ አብርሃም ደጉ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በአገልግሎት፣ በአቅርቦት እና በሪፎርም አደረጃጀት ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው፤ በማህበሩ በቀን እስከ 3 ሺህ ደምበኞች ይስተናገዳሉ።

ማዕከሉ አብዛኛውን ጊዜ የግብርና ምርቶችን እንደሚያቀርብ የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ ህብረተሰቡ ጤፍ፣ ምስር፣ አተር፣ ሽሮና ሌሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማህበሩ እንደሚገዛ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ማህበሩ የሆቴል እና የሬስቶራንት አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ቁርስ፣ ምሳና እራት በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባል፤ ንፁህ የጤፍ እንጀራ በየዓይነት ወጥ በ120 ብር ቫትን ጨምሮ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የሸማች ማህበሩ በሚያቀርባቸው የስጋ ምርቶች በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያገኝ በመግለፅ፤ በማዕከሉ የስፖርት፣ የአዳራሽ እና የፓርኪንግ አገልግሎቶች ይሰጣል ብለዋል። የሸማች ማህበሩም 500 ሠራተኞች እንዳሉት አመልክተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You