
አዲስ አበባ፡- የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እና በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር መጀመሩን ገለፀ፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉዓለም ደስታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ተቋሙ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉባዔ ላይ በገባው ቃል መሠረት፤ እኤአ እስከ 2027 ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ ከሆነው ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ባሻገር 100 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቃል ገብቷል፡፡
በመሆኑም ሰባተኛውን ዙር እረንጓዴ ዐሻራ ምክንያት በማድረግ እንደተቋም ሀገር በቀል እና የተለያዩ ችግኞችን የመትክል መርሃግብር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጋር የሚሠሩ ባለ ድርሻ አካላት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የዓለም የምግብ ድርጅት ተወካዮች እና ስደተኞች እንዲሁም ሀገር በቀል እና የዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች አረንጓዴ ዐሻራቸውን ማኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በተያዘው ዓመት አምስት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን በመግለፅ፤ በማስጀመሪያው ዕለትም በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች የመትከል መርሃግብሩ ተከናውኗል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ማስጠለሏን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ ኢንሼቲቮች ስደተኞችኝ በብዛት ለምትቀበል ሀገር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ሲሉ አመላክተዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የአሜሪካ እና የካናዳ ኤምባሲ ተወካዮች እንዲሁም ዓለምአቀፍ የምግብ ፕሮግራም ኃላፊዎች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆና፤ ለስደተኞችም የተለያየ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የምግብ ስርጭት እና አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ አመንሲሳ ቱፋ በበኩላቸው፤ ይህ የዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁለተኛው ዙር በቅርቡ ይቀጥላል ያሉ ሲሆን፤ ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ በማድረግ ፤ አረንጓዴ ዐሻራን ለማስቀጠል እንሠራለን ብለዋል፡፡
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም