
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት ሚያዝያ ወር አገልግሎት መስጠት የጀመረው የየካ ቁጥር ሁለት ሾላ የፓርኪንግ አገልግሎት በቀን በአማካይ ከ600 እስከ 800 ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የፓርኪንግ እና የመንገድ ትራፊክ መሠረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ጌታቸው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የየካ ቁጥር ሁለት ሾላ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ዘመናዊና በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ 50 መኪኖችን መያዝ የሚችል ባለ ሰባት ወለል ህንጻ ነው። በዘንድሮው 2017 ዓ.ም ሚያዝያ ወር አገልግሎት መስጠት የጀመረው የየካ ቁጥር ሁለት ሾላ የፓርኪንግ አገልግሎት በቀን በአማካይ ከ600 እስከ 800 ተሸከርካሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህንጻው ለአገልግሎት ክፍት ከሆነበት የሚያዝያ ወር ጀምሮ፤ እስከ አሁን ከ10 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ መቻሉን አመልክተው፤ በቀን ውስጥ ከ600 እስከ 800 ተሽከርካሪዎች አገልግሎቱን እያገኙ እንዳሉ ተናግረዋል።
በገበያ ወይም በዓል ወቅት እና በአዘቦት ቀን የሚኖረው የተሸከርካሪ ብዛት ቁጥር የሚለያይ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ህንጻው የበዓል ቀናት እና የእረፍት ቀናትን ጨምሮ ከጠዋት አንድ ሰዓት እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ከ30 ለአገልግሎት ከፍት እንደሆነና፤ ለአንድ ተሽከርካሪ በሰዓት 40 ብር የአገልግሎት ክፍያ የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
አንዳንድ ጊዜ ከፓርኪንግ ውጭ ባሉ ቦታዎች መኪኖች ሲቆሙ የሚቆዩበት ሰዓት ከግምት ሳይገባ ለፓርኪንግ ከሚጠየቀው ክፍያ በላይ የተጋነነ ክፍያ እንደሚጠየቁ አስታውሰው፤ የሾላ ፓርኪንግ በአንጻሩ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀና ክፍያውም ተመጣጣኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሾላ ፓርኪንግ ከመግቢያው ጀምሮ በካሜራ ዕይታ ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ከፍት የማቆሚያ ቦታዎች መረጃ መስጫ ቦርዶች ያሉት፣ ማንኛውም የሚገባ ተሽከርካሪ የሚመዘገብበት፣ አነስተኛ እና ከፍተኛ እሳት አደጋ መከላከያዎች ያሉት እና በቂ የውሃ አገልግሎት ያለው በአጠቃላይ ዘመናዊ ፓርኪንግ አገልግሎት ሊይዛቸው የሚገባውን መስፈርት (ስታንዳርድ) ያሟላ እንደሆነ አቶ ቢንያም ተናግረዋል።
በህንጻው መኪናዎች ብልሽት ቢገጥማቸው ለጥገና የሚወርዱበት ሊፍት እና ለአሽከርካሪዎች ክፍት የሆነ አሳንሰር የተገጠመለት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህንን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማከናወን የሚችሉ በቂ ስልጠና ያገኙ ሠራተኞች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ይህም የሾላ ገበያ በሚገኝበት አቅራቢያ በመሆኑ፤ በቂ የግብይት ሰዓት እንዲኖር አስችሏል። የትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ እንዳይፈጠር እና ሸማቾች የግብይት መኪናቸውን አቁመው በእርጋታ እንዲገበያዩ ለማድረግ ረድቷል ብለዋል።
ፓርኪንጉ ከመኪና ማቆም በተጨማሪ የተሸከርካሪ እጥበት አገልግሎትን እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ይህም በአካባቢው ለሚገኙ የተደራጁ 20 ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ከተገነባው ይህ የየካ ቁጥር ሁለት የሾላ ፓርኪንግ አገልግሎት ተሞክሮዎችን በመውሰድ በተለያዩ የከተማዋ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ የፓርኪንግ ሥፍራዎች የመገንባቱ ሂደት እየቀጠለ መሆኑን አቶ ቢንያም ተናግረዋል።
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም