በሶማሌ ክልል ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመታደግ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው

ጅግጅጋ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎችን ለመታደግ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ የሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ገለጸ። ክልሉ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አቅምን ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ያሲን ሼህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የሶማሌ ክልል በተደጋጋሚ የጎርፍ፣ የድርቅ እና ሌሎች ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ይከሰታል። እነዚህን ክስተቶች ለመከላከልም የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር በሀብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የክረምት ወቅትን ተከትሎ የሚጥለው ዝናብ በሦስት ወረዳዎች ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት የሚያስከትል ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል መተንበዩን አንስተው፤ በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የተለያዩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ማከናወኑን ገልጸው፤ በቅድመ መከላከል ሥራው ሕዝብን ያሳተፉ የጎርፍ አደጋ መከላከል ሥራዎች ባሻገር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው፤ በጎርፍ ስጋት ውስጥ ያሉትን አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማሰራጨትን ጨምሮ የጎርፍ መከላከያ መዋቅሮችን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል። ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ በማድረግ፣ በክልሉ የጎርፍ ግብረኃይል ተከታታይነት ያለው መረጃ ልውውጥ እንዲኖር መደረጉን አብራርተዋል።

ማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ንቁ ሆኖ እንዲጠብቅ ግንዛቤ በመፍጠር ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ተሞክሯል ያሉት ኃላፊው፤ አደጋው ቢፈጠር በወቅቱ ወደ ከፍተኛ ቦታ ማኅበረሰቡን ማንቀሳቀስና በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ በመፍጠር፤ በወቅቱ ተደራሽ ለመሆን በንቃትና በቅርበት የስጋት አካባቢዎች ላይ ክትትል እየተደረገም እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የኅብረተሰቡን የጎርፍ እና የድርቅ ተጋላጭነት በዘላቂነት ለመቀነስ ለቅድመ መከላከል ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም አምናለሁ ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም በክልሉ በአንዳንድ ዞኖችን የአደጋ ተጋላጭነት መሠረት በማድረግ የድርቅ እና ጎርፍ ስጋት ቅነሳ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በተለይም በፋፈን፣ ጀረርና ሸበሌ ዞኖች ኅብረተሰቡን በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በጤና ተቋማት ግንባታ፣ በመስኖ ልማትና በውሃ ማጠራቀሚያ ግንባታ በማሳተፍ ከአደጋ ስጋት እንዲወጡ ተደርጓል። በአካባቢው የነበረውን ድርቅና ጎርፍ አደጋ ታሳቢ በማድረግ በተሠራው የውሃ ማጠራቀሚያ /ቢርካ/ እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በቀያቸው ሆነው ማልማት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ አቶ በሽር ዓረብ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነትና አስቻይ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ክልሉ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አቅምን ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል ለችግሩ ምላሽ የሚሰጥ በቴክኖሎጂና በወቅታዊ መረጃ የታገዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዘርጋት አይተኬ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

አካታች፣ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ገቢራዊ ለማድረግ፤ ሁሉን አቀፍ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You